YouVersion Logo
Search Icon

የሉቃስ ወንጌል 5

5
ኢየሱስ የመጀመሪያዎቹን ደቀ መዛሙርት መጥራቱ
(ማቴ. 4፥18-22ማር. 1፥16-20)
1አንድ ቀን ኢየሱስ በጌንሳሬጥ ባሕር ዳር ቆሞ ሳለ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ቀርበው የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ይጋፉ ነበር። 2እርሱ በባሕሩ ዳር ተጠግተው የቆሙትን ሁለት ጀልባዎች አየ፤ ዓሣ አጥማጆቹ ግን ከጀልባዎቹ ወርደው መረቦቻቸውን ያጥቡ ነበር። 3ኢየሱስ ከጀልባዎቹ ወደ አንዲቱ፥ የስምዖን ወደሆነችው ገባ። ስምዖንንም “ይህችን ጀልባ ከምድር ወደ ባሕሩ እስቲ ጥቂት ፈቀቅ አድርግልኝ” አለው። ከዚህም በኋላ በጀልባዋ ላይ ተቀምጦ ሕዝቡን ያስተምር ጀመር። #ማቴ. 13፥1-2፤ ማር. 3፥9-10፤ 4፥1።
4ንግግሩንም ከጨረሰ በኋላ ስምዖንን፦ “ጀልባዋን ወደ ጥልቁ ባሕር ራቅ አድርገህ አንተና ጓደኞችህ ዓሣ ለማጥመድ መረባችሁን ጣሉ፤” አለው።
5ስምዖንም “መምህር ሆይ! ሌሊቱን ሙሉ ስንደክም አድረን ምንም አልያዝንም፤ አንተ ካልክ ግን፥ እነሆ! መረቡን እንጥላለን፤” አለው። #ዮሐ. 21፥3። 6መረቡን በጣሉ ጊዜ መረቡ እስኪቀደድ ድረስ እጅግ ብዙ ዓሣ ያዙ። #ዮሐ. 21፥6። 7ስለዚህ በሌላይቱ ጀልባ ላይ የነበሩት ጓደኞቻቸው መጥተው እንዲያግዙአቸው በጥቅሻ ጠሩአቸው፤ እነርሱም መጥተው ሁለቱ ጀልባዎች ሊሰምጡ ጥቂት እስኪቀራቸው ድረስ በዓሣ ሞሉአቸው። 8ስምዖን ጴጥሮስ ይህን ባየ ጊዜ በኢየሱስ ፊት ተንበርክኮ፥ “ጌታ ሆይ፥ እኔ ኃጢአተኛ ስለ ሆንኩ ወደ እኔ አትቅረብ!” አለው።
9ይህንንም ያለበት ምክንያት እርሱና አብረውት የነበሩት ጓደኞቹ ሁሉ ከያዙት ዓሣ ብዛት የተነሣ እጅግ ተገርመው ስለ ነበር ነው። 10እንዲሁም የስምዖን ጓደኞች የሆኑት የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስም ተገርመው ነበር። ኢየሱስ ስምዖንን፦ “አይዞህ አትፍራ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሰዎችን የምታጠምድ ትሆናለህ፤” አለው።
11እነርሱም ጀልባዎቹን ወደ ምድር ካስጠጉ በኋላ ሁሉን ነገር ትተው የኢየሱስ ተከታዮች ሆኑ።
ኢየሱስ ለምጻሙን ሰው ማንጻቱ
(ማቴ. 8፥1-4ማር. 1፥40-45)
12አንድ ቀን ኢየሱስ በአንዲት ከተማ ውስጥ ሳለ ገላውን ለምጽ #5፥12 ለምጽ፦ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አገላለጥ ቃሉ በሰው ላይ የሚታይ ልዩ ዐይነት ተላላፊ የቆዳ በሽታን ያመለክታል (ዘሌ 13 ተመልከት)። የወረሰው አንድ ሰው ወደ እርሱ መጣ፤ ኢየሱስን ባየው ጊዜ በግንባሩ ተደፍቶ ጌታ ሆይ፥ “ብትፈቅድስ ልታነጻኝ ትችላለህ፤” ሲል ለመነው።
13ኢየሱስም እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና “ፈቅጃለሁ ንጻ!” አለው። ሰውዬውም ወዲያውኑ ከለምጹ ነጻ። 14ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ ሲል አዘዘው፤ “ይህን ነገር ለማንም አትናገር፤ ነገር ግን በቀጥታ ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ለሕዝብ ምስክር እንዲሆን ስለ መንጻትህ ሙሴ ያዘዘውን መሥዋዕት አቅርብ።” #ዘሌ. 14፥1-32።
15የኢየሱስ ዝና ግን ከምንጊዜውም ይበልጥ ተሰማ፤ ብዙ ሰዎችም እርሱን ለመስማትና ከበሽታቸውም ለመዳን ፈልገው ይሰበሰቡ ነበር። 16እርሱ ግን በየጊዜው ብቻውን ወደ በረሓ እየሄደ ይጸልይ ነበር።
ኢየሱስ ሽባውን ሰው መፈወሱ
(ማቴ. 9፥1-8ማር. 2፥1-12)
17አንድ ቀን ኢየሱስ ሲያስተምር ሳለ ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን በአጠገቡ ተቀምጠው ነበር፤ እነርሱ ከገሊላና ከይሁዳ መንደሮች ሁሉ እንዲሁም ከኢየሩሳሌም ከተማ የመጡ ነበሩ። ኢየሱስ በሽተኞችን የሚፈውስበት የጌታ ኀይል ከእርሱ ጋር ነበረ። 18እነሆ፥ አንድ ሽባ ሰው በአልጋ የተሸከሙ ሰዎች ወደ ኢየሱስ መጡ፤ ኢየሱስ ወደ ነበረበት ቤትም አግብተው በፊቱ ሊያኖሩት ፈልገው ነበር፤ 19ነገር ግን ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ሽባውን ወደ ቤት ማግባት አቃታቸው፤ ስለዚህ ወደ ጣራ ላይ ይዘውት ወጡ፤ ጣራውንም ከፍተው በመካከሉ አውርደው ሽባውን ከነአልጋው በኢየሱስ ፊት አኖሩት። 20ኢየሱስ እምነታቸውን ባየ ጊዜ ሽባውን፥ “አንተ ሰው! ኃጢአትህ ተደምስሶልሃል፤” አለው።
21የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን “በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ይህ ማነው? ኃጢአትን የሚደመስስ እግዚአብሔር ብቻ ነው እንጂ ሌላ ማነው?” እያሉ ያስቡ ነበር።
22ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “በልባችሁ ስለምን ይህን ታስባላችሁ? 23ለመሆኑ ‘ኃጢአትህ ይቅር ተብሎልሃል፥’ ከማለትና ‘ተነሥተህ ሂድ!’ ከማለት የትኛው ይቀላል? 24ነገር ግን የሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ለመደምሰስ ሥልጣን እንዳለው ማወቅ አለባችሁ” ብሎ ሽባውን ሰው፦ “አንተ ሰው ተነሥ፤ አልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ!” አለው።
25ሽባውም በሰዎቹ ፊት ወዲያው ተነሣና፥ ተኝቶበት የነበረውን አልጋ ተሸክሞ፥ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ወደ ቤቱ ሄደ። 26በዚያም የነበሩ ሰዎች ሁሉ እጅግ ተገርመው፥ በመፍራት፥ “ዛሬ ድንቅ ነገር አየን፤” እያሉ እግዚአብሔርን አመሰገኑ።
ኢየሱስ ማቴዎስ የተባለውን ሌዊን መጥራቱ
(ማቴ. 9፥9-13ማር. 2፥13-17)
27ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ ሲሄድ ሌዊ የተባለውን ቀራጭ በቀረጥ መቀበያ ስፍራ ተቀምጦ አየውና “ተከተለኝ” አለው። 28ሌዊም ብድግ አለና ሁሉን ነገር ትቶ ተከተለው።
29ከዚህም በኋላ ሌዊ በቤቱ ለኢየሱስ ክብር ትልቅ ግብዣ አደረገ፤ በግብዣውም ላይ ብዙ ቀራጮችና ሌሎችም ብዙ ሰዎች ተገኝተው ነበር። 30ፈሪሳውያንና ወገኖቻቸው የሆኑ የሕግ መምህራን “ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር የምትበሉትና የምትጠጡት ስለምንድን ነው?” ብለው በኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ላይ አጒረመረሙ። #ሉቃ. 15፥1-2።
31ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “በሽተኞች እንጂ ጤነኞች ሐኪም አያስፈልጋቸውም፤ 32እኔ የመጣሁት ኃጢአተኞችን ወደ ንስሓ ለመጥራት ነው እንጂ ጻድቃንን ለመጥራት አይደለም።”
ስለ ጾም የቀረበ ጥያቄ
(ማቴ. 9፥14-17ማር. 2፥18-22)
33አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስን፦ “የዮሐንስና የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት ብዙ ጊዜ ይጾማሉ፤ ይጸልያሉም፤ የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን ሁልጊዜ የሚበሉትና የሚጠጡት ለምንድን ነው?” በማለት ጠየቁት።
34ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ሙሽራው ከእነርሱ ጋር እያለ ሚዜዎች መጾም ይገባቸዋል ብላችሁ ታስባላችሁን? 35ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፤ በዚያን ጊዜ ይጾማሉ።”
36ቀጥሎም ኢየሱስ፥ እንዲህ ሲል አንድ ምሳሌ ነገራቸው፦ “የአዲስ ልብስ ዕራፊ በአሮጌ ልብስ ላይ የሚጥፍ ማንም የለም፤ ይህን ቢያደርግ ግን አዲሱን ልብስ ይቀደዋል፤ አዲሱም ዕራፊ ለአሮጌው ልብስ አይስማማም፤ 37እንዲሁም በአረጀ የወይን ጠጅ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር ማንም የለም፤ ቢደረግ ግን አዲሱ የወይን ጠጅ አቁማዳውን ያፈነዳዋል፤ የወይን ጠጁም ይፈስሳል፤ አቁማዳውም ከጥቅም ውጪ ይሆናል። 38ስለዚህ አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ማኖር ይገባል፤ 39ብዙ ጊዜ የቈየ ደረቅ የወይን ጠጅ የጠጣ አዲሱን በተሐ የወይን ጠጅ መጠጣት አይፈልግም፤ ‘የቈየው ደረቅ የወይን ጠጅ የተሻለ ነው፥’ ይላልና።”

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in