YouVersion Logo
Search Icon

የሉቃስ ወንጌል 23

23
ኢየሱስ ወደ ጲላጦስ መወሰዱ
(ማቴ. 27፥1-211-14ማር. 15፥1-5ዮሐ. 18፥28-38)
1በዚያ ተሰብስበው የነበሩት ሰዎች ሁሉ ተነሥተው ኢየሱስን ወሰዱትና በጲላጦስ ፊት አቀረቡት፤ 2እንዲህ እያሉም ይከሱት ጀመር፤ “ይህ ሰው ሕዝባችንን ሲያስት አገኘነው፤ ለሮም ንጉሠ ነገሥት ግብር እንዳይከፈል ይከለክላል፤ ደግሞ ‘እኔ ንጉሥ መሲሕ ነኝ’ እያለ ይናገራል።”
3ጲላጦስም “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ሲል ኢየሱስን ጠየቀው።
ኢየሱስም “አንተ እንዳልከው ነው” አለው።
4በዚያን ጊዜ ጲላጦስ ለካህናት አለቆችና ለሕዝቡም “በዚህ ሰው ምንም በደል አላገኘሁበትም” አለ።
5እነርሱ ግን “ይህ ሰው ከገሊላ ጀምሮ እስከዚህ ድረስ፥ በይሁዳ ምድር ሁሉ እያስተማረ ሕዝቡን ለሁከት ያነሣሣል” እያሉ በጥብቅ ከሰሱት።
ኢየሱስ በሄሮድስ ፊት መቅረቡ
6ጲላጦስም ገሊላ የሚለውን ቃል በሰማ ጊዜ፥ “ይህ የገሊላ ሰው ነውን?” ብሎ ጠየቀ። 7ኢየሱስ የመጣው ከሄሮድስ ግዛት መሆኑን ጲላጦስ ባወቀ ጊዜ ወደ ሄሮድስ ላከው፤ ሄሮድስም በዚያን ጊዜ በኢየሩሳሌም ነበር። 8ሄሮድስ ኢየሱስን ባየ ጊዜ እጅግ ደስ አለው፤ ስለ ኢየሱስ ይሰማ ነበርና ሊያየው ብዙ ጊዜ ይመኝ ነበር፤ እንዲሁም ኢየሱስ ተአምር ሲያደርግ ለማየት ተስፋ ያደርግ ነበር። 9ስለዚህ ሄሮድስ ኢየሱስን ብዙ ጥያቄ ጠየቀው፤ ኢየሱስ ግን ምንም አልመለሰለትም። 10የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን እዚያ ቆመው በብርቱ ይከሱት ነበር። 11ሄሮድስም ከጭፍሮቹ ጋር ሆኖ በንቀት አፌዘበት፤ ጌጠኛ ልብስ አልብሶም ወደ ጲላጦስ መልሶ ላከው። 12በዚያን ቀን ሄሮድስና ጲላጦስ ወዳጆች ሆኑ፤ ከዚያ በፊት ግን ጠበኞች ነበሩ።
ኢየሱስ የሞት ፍርድ እንደተፈረደበት
(ማቴ. 27፥15-26ማር. 15፥6-15ዮሐ. 18፥39-4019፥1-16)
13ከዚህ በኋላ ጲላጦስ የካህናት አለቆችን፥ የሕዝብ መሪዎችንና ሕዝቡንም ጭምር በአንድነት ጠራ፤ 14እንዲህም አላቸው፤ “ ‘ሕዝቡን ለሁከት ያነሣሣል’ ብላችሁ ይህን ሰው ወደ እኔ አመጣችሁት፤ እኔም እነሆ፥ በፊታችሁ መርምሬው ካቀረባችሁበት ክስ ሁሉ በዚህ ሰው ላይ ምንም በደል አላገኘሁበትም። 15እንዲሁም ሄሮድስ ምንም በደል ስላላገኘበት ወደ እኛ መልሶ ልኮታል፤ እንግዲህ ይህ ሰው ለሞት የሚያደርሰው ምንም ነገር አላደረገም። 16ስለዚህ ገርፌ እለቀዋለሁ።” 17[በየዓመቱ በፋሲካ በዓል ጲላጦስ አንድ እስረኛ ለሕዝቡ ይፈታላቸው ነበር] #23፥17 አንዳንድ የብራና ጽሑፎች ቊ፥ 17 ይጨምራሉ ቃሉም በማር. 15፥6 ያለውን ይመስላል።
18ስለዚህ ሕዝቡ ሁሉ “ይህን ሰው አስወግደው! በርባንን ግን ፍታልን!” እያሉ በአንድ ድምፅ ጮኹ። 19በርባን በከተማ ውስጥ ብጥብጥ በማስነሣትና ሰውን በመግደል ምክንያት በወህኒ ቤት የታሰረ ሰው ነበር።
20ጲላጦስ ኢየሱስን ፈቶ ሊለቀው ፈልጎ እንደገና ለሕዝቡ ተናገረ። 21ሕዝቡ ግን “ስቀለው! ስቀለው!” እያለ ጮኸ።
22ጲላጦስም ሦስተኛ ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ሰው ያደረገው በደል ከቶ ምንድን ነው? እኔ ለሞት የሚያደርስ ምንም ነገር አላገኘሁበትም፤ ስለዚህ ገርፌ እለቀዋለሁ።”
23እነርሱ ግን ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “ስቀለው!” እያሉ ጮኹ፤ የሕዝቡና የካህናት አለቆች ድምፅ አየለ። 24በዚህም ምክንያት የጠየቁት እንዲደረግላቸው ጲላጦስ ፈረደ። 25ብጥብጥ በማስነሣትና ሰው በመግደል ታስሮ የነበረውን በርባንን በጥያቄአቸው መሠረት ለቀቀው፤ ኢየሱስን ግን እንደ ፍላጎታቸው አሳልፎ ሰጣቸው።
የኢየሱስ መሰቀል
(ማቴ. 27፥32-44ማር. 15፥21-32ዮሐ. 19፥17-27)
26ስለዚህ ኢየሱስን ወሰዱት፤ ይዘውት ሲሄዱ ሳሉም የቀሬና ሰው የሆነውን ስምዖንን ከገጠር ወደ ከተማ ሲገባ አገኙት፤ እርሱን ይዘው የኢየሱስን መስቀል አሸከሙትና ኢየሱስን እንዲከተል አደረጉት።
27ብዙ ሰዎችም ኢየሱስን ይከተሉ ነበር፤ ከእነርሱም መካከል ደረታቸውን እየደቁ የሚያለቅሱለት ሴቶች ነበሩ። 28ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ መለስ ብሎ፥ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የኢየሩሳሌም ሴቶች፥ ስለ ራሳችሁና ስለ ልጆቻችሁ አልቅሱ እንጂ ስለ እኔ አታልቅሱ! 29‘መኻኖች የሆኑ ሴቶች፥ ያልወለዱ ማሕፀኖችና ያላጠቡ ጡቶች እንዴት የታደሉ ናቸው!’ የሚባሉበት ቀኖች ይመጣሉ። 30በዚያን ጊዜ ሰዎች ተራራዎችን፥ ‘በላያችን ውደቁ!’ ኮረብቶችንም፥ ‘ሸሽጉን!’ ማለት ይጀምራሉ። #ሆሴዕ 10፥8፤ ራዕ. 6፥16። 31እንግዲህ ይህ ሁሉ ነገር በእርጥብ እንጨት ላይ የሚደረግ ከሆነ በደረቅ እንጨት ላይማ ምን ይደረግ ይሆን?” 32እንዲሁም ሁለት ወንጀለኞችን ከኢየሱስ ጋር ሊገድሉአቸው ይዘው ሄዱ። 33ቀራንዮ ወይም የራስ ቅል ወደ ተባለ ስፍራም በደረሱ ጊዜ በዚያ ኢየሱስን ሰቀሉት፤ እንዲሁም ሁለቱን ወንጀለኞች በኢየሱስ ግራና ቀኝ ሰቀሉአቸው። 34ከዚህ በኋላ ኢየሱስ፦ “አባት ሆይ! የሚያደርጉትን ስለማያውቁ ይቅር በላቸው!” አለ። ወታደሮቹም ዕጣ ተጣጥለው የኢየሱስን ልብስ ተከፋፈሉ። #መዝ. 22፥18። 35ሕዝቡ ቆሞ ይመለከት ነበር፤ የአይሁድ አለቆችም “ሌሎችንስ አዳነ እንግዲህ እርሱ የተመረጠው የእግዚአብሔር መሲሕ ከሆነ እስቲ ራሱን ያድን!” እያሉ ያፌዙበት ነበር። #መዝ. 22፥7።
36ወታደሮቹም እንዲሁ አፌዙበት፤ ወደ እርሱም ቀርበው ሆምጣጤ ሰጡት። #መዝ. 69፥21። 37እንዲሁም “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ከሆንክ እስቲ ራስህን አድን!” ይሉት ነበር።
38“ይህ የአይሁድ ንጉሥ ነው” የሚል ጽሑፍም በኢየሱስ ራስጌ በመስቀሉ ላይ አኖሩ።
ከኢየሱስ ጋር የተሰቀሉት ሁለት ወንጀለኞች
(ማቴ. 27፥38-44ማር. 15፥27-32)
39ከኢየሱስ ጋር ከተሰቀሉት ወንጀለኞች አንዱ፥ ኢየሱስን፦ “አንተ መሲሕ አይደለህምን? እስቲ በል ራስህንና እኛን አድን!” እያለ ይሰድበው ነበር።
40ሌላው ወንጀለኛ ግን እንዲህ ብሎ ገሠጸው፦ “አንተ በተመሳሳይ ፍርድ ላይ እያለህ እግዚአብሔርን አትፈራምን? 41እኛ ባደረግነው በደል ምክንያት የሚገባንን ቅጣት አግኝተናል፤ ይህ ሰው ግን ምንም ጥፋት አላደረገም።” 42ቀጥሎም ኢየሱስን፦ “ጌታ ሆይ! በመንግሥትህ ስትመጣ አስታውሰኝ!” አለው።
43ኢየሱስም “በእውነት እልሃለሁ፤ ዛሬውኑ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ!” አለው።
የኢየሱስ ሞት
(ማቴ. 27፥45-56ማር. 15፥33-41ዮሐ. 19፥28-30)
44እነሆ፥ ይህ የሆነው ከቀኑ ስድስት ሰዓት ገደማ ነበር፤ ከዚያን ጊዜም ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። 45ፀሐይ ጨለመ፤ የቤተ መቅደስ መጋረጃም ከመካከሉ ተቀዶ ከሁለት ተከፈለ። #ዘፀ. 26፥31-33። 46ኢየሱስም ድምፁን ከፍ አድርጎ፥ “አባት ሆይ! እነሆ! ነፍሴን በእጅህ ዐደራ እሰጣለሁ!” አለ፤ ይህንንም ካለ በኋላ ነፍሱ ከሥጋው ተለየች። #መዝ. 31፥5።
47በዚያ የነበረው መቶ አለቃ፥ የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ፥ “በእርግጥ ይህ ሰው ጻድቅ ኖሮአል!” ብሎ እግዚአብሔርን አከበረ።
48ነገሩን ለመመልከት እዚያ ተሰብስበው የነበሩ ሰዎች ሁሉ የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ በማዘን ደረታቸውን እየመቱ ወደየቤታቸው ተመለሱ። 49ኢየሱስን በቅርብ ያውቁት የነበሩ ሰዎች ሁሉና ከገሊላ ጀምሮ ይከተሉት የነበሩ ሴቶችም በሩቅ ቆመው ይህን ነገር ይመለከቱ ነበር። #ሉቃ. 8፥2-3።
የኢየሱስ መቀበር
(ማቴ. 27፥57-61ማር. 15፥42-47ዮሐ. 19፥38-42)
50የአይሁድ ከተማ በሆነችው በአርማትያስ የሚኖር ዮሴፍ የሚባል ሰው ነበረ፤ እርሱ ጻድቅና ደግ ሰው ነበረ፤ የአይሁድ ሸንጎ አባልም ነበረ። 51ይሁን እንጂ በአይሁድ ምክርና ሤራ አልተባበረም፤ እርሱ የእግዚአብሔርን መንግሥት በተስፋ የሚጠባበቅ ሰው ነበረ። 52ይህ ሰው ወደ ጲላጦስ ፊት ቀርቦ የኢየሱስ አስከሬን እንዲሰጠው ጠየቀ። 53አስከሬኑንም አውርዶ በቀጭን ሐር ልብስ ከፈነው፤ ማንም ሰው ባልተቀበረበት ከአለት ተወቅሮ በተዘጋጀ መቃብር ውስጥ ቀበረው፤ 54ይህንንም ያደረገው ዓርብ ማታ ለሰንበት ዝግጅት በሚደረግበት ጊዜ ነበር።
55ኢየሱስን ተከትለው ከገሊላ የመጡ ሴቶች ከዮሴፍ ጋር ሄደው መቃብሩን አዩ፤ አስከሬኑም እንዴት እንደ ተቀበረ ተመለከቱ። 56ወደ ቤታቸውም ተመልሰው ለአስከሬን የሚሆኑ ጥሩ መዓዛ ያለው ቅመምና ሽቶ አዘጋጁ፤ በሕግ መሠረት በሰንበት ቀን ዐርፈው ዋሉ። #ዘፀ. 20፥10፤ ዘዳ. 5፥14።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in