YouVersion Logo
Search Icon

የሉቃስ ወንጌል 12

12
ኢየሱስ ከግብዝነት ማስጠንቀቁ
(ማቴ. 10፥26-27)
1በዚያን ጊዜ በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ ከብዛታቸውም የተነሣ እርስ በርሳቸው እየተጋፉ ይረጋገጡ ነበር፤ ኢየሱስም በቅድሚያ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ይል ጀመር፤ “ከፈሪሳውያን እርሾ ማለትም ከግብዝነታቸው ተጠንቀቁ ማለት ነው። #ማቴ. 16፥6፤ ማር. 8፥15። 2የተሸፈነ ነገር ሳይገለጥ አይቀርም፤ የተሰወረውም ሳይታወቅ አይቀርም። #ማር. 4፥22፤ ሉቃ. 8፥17። 3ስለዚህ በጨለማ የተናገራችሁት ሁሉ በብርሃን ይሰማል፤ በዝግ ቤት ውስጥ በሹክሹክታ በጆሮ የተናገራችሁትም በሰገነት ላይ በይፋ ይነገራል።
ማንን መፍራት እንደሚገባ
(ማቴ. 10፥28-31)
4“ለእናንተ ለወዳጆቼ እንዲህ እላችኋለሁ፤ ሥጋን ከመግደል በቀር ሌላ ምንም ማድረግ የማይችሉትን አትፍሩ፤ 5ነገር ግን ማንን መፍራት እንደሚገባችሁ እነግራችኋለሁ፤ ይኸውም ከገደለ በኋላ ወደ ገሃነም ለመጣል ሥልጣን ያለውን እግዚአብሔርን ነው፤ አዎ፥ እርሱን ብቻ ፍሩ እላችኋለሁ!
6“አምስት ድንቢጦች በዐሥር ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱ አንድዋ እንኳ በእግዚአብሔር ፊት የተረሳች አይደለችም። 7የእናንተማ የራሳችሁ ጠጒር እንኳ በሙሉ የተቈጠረ ነው፤ ስለዚህ አትፍሩ! እናንተ ከብዙ ድንቢጦች ትበልጣላችሁ።”
ስለ ክርስቶስ መመስከር
(ማቴ. 10፥32-3312፥3210፥19-20)
8ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ሳያፍር በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ እኔም ደግሞ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት እመሰክርለታለሁ እላችኋለሁ። 9በሰው ፊት የሚክደኝን እኔም ደግሞ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት እክደዋለሁ።
10“በሰው ልጅ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ቢኖር በደሉ ይቅር ይባልለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ቢኖር ግን በደሉ ይቅር አይባልለትም። #ማቴ. 12፥32፤ ማር. 3፥29።
11“ሰዎች በየምኲራቡ ሲወስዱአችሁ፥ በገዢዎችና በባለሥልጣኖች ፊት ለፍርድ ሲያቀርቡአችሁ ‘ምን እንመልሳለን? እንዴትስ እንናገራለን?’ ብላችሁ አትጨነቁ። 12ልትናገሩት የሚገባችሁን በዚያን ሰዓት መንፈስ ቅዱስ ይነግራችኋል።”
የሀብታሙ ሰው ሞኝነት
13ከሕዝቡም መካከል አንድ ሰው ኢየሱስን፦ “መምህር ሆይ፥ አባታችን ያወረሰንን ርስት እንዲያካፍለኝ እባክህ ለወንድሜ ንገረው” አለው።
14ኢየሱስ ግን፥ “አንተ ሰው፥ በእናንተ መካከል ፈራጅ እንድሆንና ርስት እንዳካፍል ማን ሾመኝ?” ሲል መለሰለት። 15ቀጥሎ ለሁሉም እንዲህ አላቸው፤ “የሰው ሕይወት በሀብቱ ብዛት አይደለም፤ ስለዚህ ተጠንቀቁ፤ ከስስትም ተጠበቁ።”
16ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ይህን ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “እርሻው ብዙ ሰብል ያስገኘለት አንድ ሀብታም ሰው ነበር፤ 17እርሱም በሐሳቡ፥ ‘ይህን ሁሉ እህል የማከማችበት ስፍራ ስለሌለኝ ምን ላድርግ?’ እያለ ያሰላስል ነበር። 18እንዲህም አለ፦ ‘የማደርገው ይህ ነው፤ ጐተራዎቼን ሁሉ አፈርስና ሌሎች ትልልቅ ጐተራዎች እሠራለሁ፤ በዚያ እህሌንና ንብረቴን ሁሉ ሰብስቤ አከማቻለሁ። 19ከዚህም በኋላ ራሴን፦ እነሆ፥ ለብዙ ዓመት የሚበቃህ ብዙ ሀብት አለህ፤ እንግዲህ ዕረፍት በማድረግ ተዝናና! ብላ! ጠጣ! ደስ ይበልህ! እለዋለሁ’ አለ። 20እግዚአብሔር ግን ‘አንተ ሞኝ፥ ዛሬ በዚህች ሌሊት ነፍስህ ከአንተ ትወሰዳለች፤ ታዲያ ይህ ያከማቸኸው ሀብት ሁሉ ለማን ይሆናል?’ አለው።
21“ለራሱ በምድር ላይ ሀብትን የሚያከማች፥ በእግዚአብሔር ፊት ግን ድኻ የሆነ ሰው እንዲሁ ይሆናል።”
እምነትን በእግዚአብሔር ላይ ማድረግ
(ማቴ. 6፥25-34)
22ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፤ “ስለዚህ ለሕወታችሁ ‘ምን እንበላለን? ለሰውነታችሁም ምን እንለብሳለን?’ በማለት ስለ ኑሮአችሁ አትጨነቁ እላችኋለሁ። 23ከምግብ ሕይወት፥ ከልብስም ሰውነት ይበልጣል። 24እስቲ ቊራዎችን ተመልከቱ! እነርሱ አይዘሩም ወይም አያጭዱም፤ የእህል ማከማቻ ቦታ ወይም ጐተራ የላቸውም፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ይመግባቸዋል፤ እናንተማ ከወፎች የቱን ያኽል ትበልጣላችሁ! 25ለመሆኑ ከእናንተ መካከል በመጨነቅ በዕድሜው ላይ አንድ ቀን መጨመር የሚችል ማን ነው? #12፥25 በዕድሜው ላይ አንድ ቀን፦ በአንዳንድ ትርጒም በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ የሚል ይገኛል። 26እንግዲህ ይህን ትንሹን ነገር እንኳ ማድረግ የማትችሉ ከሆናችሁ፥ ስለምን በሌላው ነገር ትጨነቃላችሁ? 27የአሸንድዬ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ እስቲ ተመልከቱ፤ እነርሱ በሥራ አይደክሙም፤ አይፈትሉም፤ ይሁን እንጂ ሰሎሞን እንኳ በዚያ ሁሉ ክብሩ ከእነርሱ እንደ አንዲቱ ያጌጠ ልብስ አለበሰም። #1ነገ. 10፥4-7፤ 2ዜ.መ. 9፥3-6። 28ታዲያ፥ እግዚአብሔር ዛሬ ታይቶ ነገ በእሳት ውስጥ የሚጣለውን የሜዳ ሣር እንዲህ አስጊጦ የሚያለብሰው ከሆነ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁም!
29“ስለዚህ ‘ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን?’ እያላችሁ በማሰብ አትጨነቁ። 30ይህን ለማግኘትማ የዚህ ዓለም ሰዎችም ይጨነቁበታል፤ እናንተ ግን ይህ ሁሉ እንደሚያስፈልጋችሁ የሰማይ አባታችሁ ያውቃል። 31ይልቅስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ፈልጉ፤ እነዚህም ነገሮች ሁሉ ይጨመሩላችኋል።
በምድር ላይ ሀብት ማከማቸት እንደማይገባ
(ማቴ. 6፥19-21)
32“እናንተ እንደ ታናናሽ መንጋ የሆናችሁ ወገኖቼ አትፍሩ፤ የሰማይ አባታችሁ መንግሥትን ሊሰጣችሁ ፈቅዶአል። 33ያላችሁን ሁሉ ሸጣችሁ ገንዘቡን ለድኾች ስጡ፤ የማያረጅ የገንዘብ ቦርሳም አዘጋጅታችሁ ገንዘባችሁን ሌባ በማይደርስበት፥ ብል በማይበላበትና ከቶም በማያልቅበት ቦታ በመንግሥተ ሰማያት አስቀምጡ። 34ገንዘባችሁ ባለበት ቦታ ልባችሁም በዚያው ይሆናል።”
ትጉህ አገልጋይ
35ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ባጭር ታጥቃችሁ ሁልጊዜ ለሥራ ተዘጋጁ፤ መብራታችሁም የበራ ይሁን። #ማቴ. 25፥1-13። 36በዚህም አኳኋን፥ ጌታቸው ከሠርግ ቤት መመለሱን የሚጠባበቁ አገልጋዮችን ምሰሉ፤ እነርሱ ጌታቸው በድንገት መጥቶ በሩን በሚያንኳኳበት ጊዜ ፈጥነው ለመክፈት ዝግጁዎች ናቸው። #ማር. 13፥34-36። 37እነዚያ ጌታቸው ድንገት በመጣ ጊዜ፥ ነቅተው ሲጠብቁ የሚያገኛቸው አገልጋዮች እንዴት የተመሰገኑ ናቸው? በእውነት እላችኋለሁ፤ እርሱ ባጭር ታጥቆ በማእድ ያስቀምጣቸዋል፤ ቀርቦም ያገለግላቸዋል። 38ጌታቸው በእኩለ ሌሊት ወይም ከእኩለሌሊት በኋላ በመጣ ጊዜ ነቅተውና ተግተው ሲጠብቁት የሚያገኛቸው አገልጋዮች የተባረኩ ናቸው። 39ደግሞም ይህን ዕወቁ፤ አንድ ሰው ሌባ የሚመጣበትን ሰዓት ቢያውቅ ኖሮ ሌባው ቤቱን ቆፍሮ እንዲገባ አይተወውም ነበር። #ማቴ. 24፥43-44። 40የሰው ልጅም ባላሰባችሁበት ሰዓት በድንገት ይመጣል፤ ስለዚህ እናንተም ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ።”
የደጉና የክፉው አገልጋይ ምሳሌ
(ማቴ. 24፥45-51)
41ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! ይህን ምሳሌ የምትናገረው ለእኛ ብቻ ነውን? ወይስ ለሁሉም ነው?” ሲል ኢየሱስን ጠየቀው።
42ጌታ ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ታዲያ ቤተሰቦቹን በደንብ እንዲያስተዳድርለትና ለአገልጋዮቹም ምግባቸውን በተመደበው ጊዜ እንዲሰጣቸው ጌታው የሚሾመው ታማኝና ብልኅ መጋቢ ማን ነው? 43ጌታው ከሄደበት ሲመለስ ልክ እንደታዘዘው ሲፈጽም የሚያገኘው አገልጋይ እንዴት የተባረከ ነው! 44በእውነት እላችኋለሁ፤ ጌታው ያን አገልጋይ የንብረቱ ሁሉ ኀላፊ አድርጎ ይሾመዋል። 45ነገር ግን ያ አገልጋይ ‘ጌታዬ ቶሎ አይመጣም፤ ይዘገያል’ ብሎ በማሰብ እየበላ፥ እየጠጣ፥ እየሰከረም ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮችን መምታት ይጀምራል። 46ይሁን እንጂ ጌታው ባልታሰበበት ቀንና ባልተጠበቀበት ሰዓት በድንገት ይመጣል፤ አገልጋዩንም በብርቱ ይቀጣዋል፤ ዕድሉንም ከወስላቶች ጋር እንዲሆን ያደርጋል።
47“የጌታውን ፈቃድ እያወቀ ያልተዘጋጀ፥ ወይም የጌታውን ትእዛዝ ያልፈጸመ አገልጋይ በብርቱ ይቀጣል። 48ነገር ግን የጌታውን ፈቃድ ባለማወቅ፥ ቅጣት የሚያመጣበትን ነገር አድርጎ ቢገኝ ቅጣቱ ይቀልለታል፤ ብዙ ከተሰጠው ሰው ብዙ ይፈለግበታል፤ ብዙ ዐደራም ከተሰጠው ሰው፥ ብዙ ይጠበቅበታል።”
ሁሉን ነገር ትቶ ኢየሱስን መከተል
(ማቴ. 10፥34-36)
49ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እነሆ! እኔ በምድር ላይ እሳት አምጥቻለሁ፤ ታዲያ፥ ቶሎ ቢቀጣጠልልኝ እንዴት በወደድኩ ነበር! 50ነገር ግን እኔ የምጠመቀው የመከራ ጥምቀት አለኝ፤ እርሱም እስኪፈጸም ድረስ ዕረፍት የለኝም። #ማር. 10፥38። 51እኔ በምድር ላይ ሰላምን ያመጣሁ ይመስላችኋልን? እኔስ ያመጣሁት መለያየትን እንጂ ሰላምን አይደለም እላችኋለሁ። 52ከአሁን ጀምሮ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ያሉ አምስት ሰዎች ይለያያሉ፤ ሦስቱ በሁለቱ ላይ፥ ሁለቱም በሦስቱ ላይ ተነሥተው ይጣላሉ። 53አባት በልጁ ላይ፥ ልጅም በአባቱ ላይ፥ እናት በሴት ልጅዋ ላይ፥ ሴት ልጅም በእናትዋ ላይ፥ ዐማት በምራትዋ ላይ፥ ምራትም በዐማትዋ ላይ በመነሣት ይለያያሉ።” #ሚክ. 7፥6።
የጊዜውን ሁኔታ ስለማወቅ
(ማቴ. 16፥2-3)
54ደግሞም ኢየሱስ ለሕዝቡ እንዲህ አለ፦ “ደመና በስተ ምዕራብ በኩል ስታዩ ወዲያውኑ፦ ‘እነሆ! ዛሬ ሊዘንብ ነው!’ ትላላችሁ፤ በእርግጥም ይዘንባል። 55እንዲሁም ነፋስ በስተ ደቡብ በኩል በሚነፍስበት ጊዜ፥ ‘ዛሬ ሙቀት ይሆናል’ ትላላችሁ፤ በእርግጥም ይሆናል። 56እናንተ ግብዞች የምድሩንና የሰማዩን መልክ በመመልከት የሚሆነውን ታውቃላችሁ፤ ታዲያ በዚህ በአሁኑ ዘመን የሚሆነውን ለምን አታውቁም?”
ከባላጋራ ጋር ስለ መስማማት
(ማቴ. 5፥25-26)
57ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ ስለምን እናንተ ራሳችሁ ትክክለኛውን ነገር ዐውቃችሁ አትፈርዱም? 58ባላጋራህ ከሶህ ወደ ፍርድ ቤት በሚወስድህ ጊዜ ገና በመንገድ ሳለህ ከባላጋራህ ጋር ለመስማማት ተጣጣር፤ አለበለዚያ እርሱ ወደ ዳኛ ጐትቶ ይወስድሃል፤ ዳኛውም ለአሳሪው አሳልፎ ይሰጥሃል፤ አሳሪውም ወደ እስር ቤት ያገባሃል። 59መቀጮህን ሁሉ ጨርሰህ ሳትከፍል ከእስር ቤት መውጣት እንደማትችልም እነግርሃለሁ።”

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in