ኦሪት ዘሌዋውያን 7
7
የበደል ስርየት መሥዋዕት
1“እጅግ የተቀደሰ ስለ ሆነው የበደል ስርየት መሥዋዕት አቀራረብ የተሰጠው መመሪያ ይህ ነው፤ 2መሥዋዕት ሆኖ የቀረበው እንስሳ፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርቡት እንስሶች በሚታረዱበት ስፍራ ይታረድ፤ ደሙም በመሠዊያው ጐን በአራቱም ማእዘን ይረጭ። 3ስቡ ሁሉ ተገፎ፥ ይኸውም የላቱ ስብ፥ የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነው ስብ፥ 4ኲላሊቶቹና በእነርሱ ላይ የሚገኘው ስብ፥ እንዲሁም እንደ መረብ ሆኖ ጉበቱን ከሚሸፍነው ስብ ምርጥ የሆነው ክፍል ተወስዶ በመሠዊያው ላይ መሥዋዕት ሆኖ ይቅረብ፤ 5በመሠዊያውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ ካህኑ ለእግዚአብሔር መባ አድርጎ በእሳት ያቃጥለው፤ ይህም የበደል መሥዋዕት ነው። 6ከካህናት ወገን የሆነ ወንድ ሁሉ የመሥዋዕቱን ሥጋ ይብላ፤ ነገር ግን ያ መሥዋዕት እጅግ የተቀደሰ ስለ ሆነ በተቀደሰ ስፍራ ይብላው።
7“ስለ ኃጢአት ስርየት በሚቀርበው መሥዋዕትና ስለ በደል ስርየት በሚቀርበው መሥዋዕት መካከል ለሁለቱም የሚሠራ አንድ ዐይነት ሕግ አለ፤ ይኸውም የእንስሳው ሥጋ መሥዋዕቱን ለሚያቀርበው ካህን ምግብ እንዲሆን ይሰጣል፤ 8ለሚቃጠል መሥዋዕት የቀረበው እንስሳ፥ ቆዳው ተገፎ መሥዋዕቱን ላቀረበው ካህን ይሰጠዋል፤ 9በእቶን የተጋገረው የእህል መባ ሁሉ፥ ወይም በመቀቀያ የበሰለውና በምጣድ የተጋገረው መሥዋዕት አድርጎ ላቀረበው ካህን ይሰጣል፤ 10በዘይት የተለወሰም ቢሆን ወይም ደረቅ ያልበሰለው የእህል መባ ግን ትውልዳቸው ከአሮን ወገን ለሆነው ካህናት ሁሉ ይሰጥ፤ እርሱንም እኩል ይካፈሉት።
የበደል መሥዋዕት
11“ለእግዚአብሔር ስለሚቀርበው የአንድነት መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው፤ 12አንድ ሰው ይህን መባ ለእግዚአብሔር የምስጋና መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ቢፈልግ፥ ከሚሠዋው እንስሳ ጋር እርሾ ያልነካው በዘይት ተለውሶ የተጋገረ ዳቦ፥ እርሾ ያልገባበት በስሱ ተጋግሮ ዘይት የተቀባ ዳቦ፥ በላመ ዱቄት በዘይት ተለውሶ የተጋገረ ዳቦ ያቅርብ። 13ከአንድነት መሥዋዕት በተጨማሪ ለመባ የሚሆን በእርሾ ተቦክቶ የተጋገረ ኅብስት ያቅርብ። 14ከእያንዳንዱ የኅብስት ዐይነት አንዱን ክፍል ለእግዚአብሔር የተለየ መባ አድርጎ ያቀርባል፤ ያም መባ የእንስሳውን ደም ወስዶ በመሠዊያው ጐን የኅብረት መሥዋዕት አድርጎ ለረጨው ካህን ድርሻ ይሁን፤ 15የእንስሳውም ሥጋ በዚያው በተሠዋበት ቀን መበላት አለበት፤ ከዚያ ተርፎ የሚያድር ምንም ነገር አይኑር።
16“አንድ ሰው የሚያቀርበው የአንድነት መሥዋዕት ስእለት ስለ ተፈጸመለት ወይም የበጎ ፈቃድ ስጦታ ቢሆን ሁሉም በዚያው በቀረበበት ዕለት ይበላ፤ ከዚያም የተረፈ ቢኖር በማግስቱ ይበላ። 17ከመሥዋዕቱ ተርፎ እስከ ሦስት ቀን የቈየው ሥጋ ግን በእሳት ይቃጠል፤ 18ከተረፈው ሥጋ ምንም ያኽል በሦስተኛው ቀን ቢበላ የዚያን ሰው መሥዋዕት እግዚአብሔር አይቀበልለትም፤ መሥዋዕቱም እንደ ቀረበ ሆኖ አይቈጠርለትም፤ እንዲያውም እንደ ረከሰ ሆኖ ይቈጠራል፤ እርሱንም የበላ ሰው የበደሉን ፍዳ ይቀበላል። 19ንጹሕ የሆነውን ሥጋ ማንኛውም የረከሰ ነገር ቢነካው መቃጠል እንጂ መበላት የለበትም፤
“ንጹሕ የሆነ ሰው ይህን ንጹሕ የሆነውን ሥጋ ይብላ፤ 20ነገር ግን አንድ ሰው ንጹሕ ሳይሆን የአንድነቱን መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ ከእግዚአብሔር ሕዝብ መለየት አለበት፤ 21ማንም ሰው ንጹሕ ያልሆነው ከሰው ወይም ከእንስሶች የሚወጣ ማንኛውንም ርኩስ ነገር ነክቶ ይህን የአንድነት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ ያ ሰው ከእግዚአብሔር ሕዝብ ይለይ። ”
22እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 23“ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ የቀንድ ከብት፥ የበግና፥ የፍየልን ስብ የሚበላ አይኑር፤ 24ሞቶ የተገኘ እንስሳ ወይም አውሬ የገደለው እንስሳ ስቡ ለሌላ አገልግሎት ይዋል እንጂ ማንም ሰው አይብላው። 25የሚቃጠል መሥዋዕት ሆኖ ለእግዚአብሔር የቀረበውን እንስሳ ስብ የሚበላ ሰው ከእግዚአብሔር ሕዝብ ይለይ፤ 26እንዲሁም እስራኤላውያን የትም ቦታ ቢኖሩ በሚኖሩበት ስፍራ ሁሉ የወፍም ሆነ የእንስሳ ደም አይብሉ፤ 27ማንኛውንም ደም የሚበላ ሰው ሁሉ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ይለይ።” #ዘፍ. 9፥4፤ ዘሌ. 17፥10-14፤ 19፥26፤ ዘዳ. 12፥16፤ 23፥16-23።
28እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 29“ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ በላቸው፤ ማንም ሰው የአንድነት መሥዋዕት ቢያቀርብ ከእርሱ ከፍሎ ለእግዚአብሔር የተለየ መባ ያምጣ፤ 30እርሱንም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቅርብ፤ የእንስሳውንም ስብ ከፍርምባው ጋር በመወዝወዝ ለእግዚአብሔር ልዩ መባ አድርጎ ያቅርብ። 31ካህኑ ስቡን በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው፤ ፍርምባው ግን ለካህናቱ ይሰጥ፤ 32ከአንድነቱ መሥዋዕት በቀኝ በኩል ያለው ወርች ድርሻው ሆኖ ለካህኑ ይሰጥ፤ 33የቀኙ ወርች የአንድነቱን መሥዋዕት ደምና ስብ ለሚያቀርበው ካህን ድርሻ ይሁን፤ 34ከእስራኤላውያን የአንድነት መሥዋዕት መካከል የተወዘወዘውን ፍርንባና የሚቀርበውን ወርች ከእስራኤላውያን እንደሚቀርብላቸው ቋሚ ድርሻ አድርጌ ለካህኑ ለአሮንና ለልጆቹ ሰጥቻቸዋለሁ። 35ይህም እግዚአብሔር አሮንንና ልጆቹን ካህናት አድርጎ በሾመበት ቀን ለእግዚአብሔር ከቀረበው ከሚቃጠል መሥዋዕት ለካህናት ድርሻ ሆኖ የተለየ ነው፤ 36በዚያን ቀን እግዚአብሔር ይህን የመሥዋዕት ክፍል ለካህናቱ እንዲሰጡአቸው የእስራኤልን ሕዝብ አዘዘ፤ ይህም በሚመጡት ዘመናት ሁሉ የካህናቱ ድርሻ እንዲሆን ቋሚ ሥርዓት አደረገው።”
37እንግዲህ ስለሚቃጠል መሥዋዕት፥ ስለ እህል መባ፥ ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት፥ ስለ በደል ማስተስረያ መሥዋዕት ስለ ክህነት ሹመት መሥዋዕትና የአንድነት መሥዋዕት የሚፈጸሙትም የሥርዓት መመሪያዎች እነዚሁ ናቸው። 38በዚያም በረሓ በሆነው በሲና ተራራ እስራኤላውያን መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ባዘዛቸው በዚያ ቀን እግዚአብሔር ለሙሴ እነዚህን ትእዛዞች ሰጠው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 7: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997