ትንቢተ ዮናስ 4
4
የዮናስ ብስጭትና የእግዚአብሔር ምሕረት
1ዮናስ በዚህ ነገር ስላልተደሰተ ተበሳጨ፤ 2እንዲህም ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፦ “እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ይህን እንደምታደርግ ገና በአገሬ ሳለሁ ተናግሬ አልነበረምን? ከፊትህ ኰብልዬ ወደ ተርሴስ ለመሄድ ያቀድኩትም በዚህ ምክንያት ነበር፤ አንተ ቸርና ይቅር ባይ፥ ታጋሽና ምሕረትህ የበዛ፥ በዘለዓለማዊ ፍቅር የተመላህ፥ ቊጣህን መልሰህ ምሕረት የምታደርግ አምላክ መሆንህን ዐውቅ ነበር። #ዘፀ. 34፥6። 3አሁንም ጌታ ሆይ! እባክህ ግደለኝ፤ ከመኖር ይልቅ መሞት ይሻለኛል።” #1ነገ. 19፥4።
4እግዚአብሔርም “ይህን ያኽል ልትቈጣ ይገባሃልን?” አለው።
5ዮናስም ከከተማይቱ ወጥቶ ከከተማይቱም በስተ ምሥራቅ በኩል ዳስ በመሥራት ከጥላው ሥር ተቀመጠ፤ በዚያም ሆኖ በነነዌ ላይ የሚደርሰውን ነገር ይጠባበቅ ነበር። 6ጥላ በማግኘት ከፀሐይ ግለት እንዲድን እግዚአብሔር አምላክ አንድ የቅል ተክል አብቅሎ ቅጠሎችዋ ከዮናስ ራስ በላይ እንዲሆኑ አደረገ፤ ዮናስም ከቅሉ ሐረግ ጥላ በማግኘቱ እጅግ ተደሰተ። 7ነገር ግን በማግስቱ ጠዋት እግዚአብሔር አንድ ትል አዘጋጀ፤ ትልዋም ቅሊቱን በላች፤ እርሷም ደረቀች። 8ፀሐይ ከወጣ በኋላ እግዚአብሔር የሚያቃጥል የምሥራቅ ነፋስ ላከ፤ የፀሐዩም ሐሩር ራሱን ስላቃጠለው ዮናስ ተዝለፈለፈ፤ ሞትንም በመመኘት “ከመኖር ይልቅ መሞት ይሻለኛል” አለ።
9እግዚአብሔርም “ስለዚህች ቅል ልትበሳጭ ይገባሃልን?” አለው። ዮናስም “በእርግጥ መበሳጨት ይገባኛል፤ እንዲያውም በንዴት እስከምሞት ድረስ መበሳጨት አለብኝ!” አለ።
10እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፦ “አንተ በአንድ ቀን በቅላ፥ በአንድ ቀን ለደረቀች፥ እንዲያውም ላልደከምክባትና ላላሳደግሃት ተክል ይህን ያኽል አዝነሃል! 11ነነዌ ክፉና ደጉን የማይለዩ ከአንድ መቶ ኻያ ሺህ ሕዝብ በላይ የሚኖሩባት ከተማ ነች፤ ብዙ እንስሶችም አሉባት፤ ታዲያ እኔ ለዚህች ታላቂቱ ከተማ አልራራምን?”
Currently Selected:
ትንቢተ ዮናስ 4: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997