የዮሐንስ ወንጌል 9
9
ኢየሱስ ዕውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ማዳኑ
1ኢየሱስ በመንገድ ሲያልፍ ዕውር ሆኖ የተወለደ ሰው አየ። 2ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን “መምህር ሆይ፥ ይህ ሰው ዕውር ሆኖ የተወለደው በማን ኃጢአት ነው? በራሱ ኃጢአት ነውን ወይስ በወላጆቹ?” ሲሉ ጠየቁት።
3ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ይህ ሰው ዕውር ሆኖ የተወለደው በእርሱ ወይም በወላጆቹ ኃጢአት ምክንያት አይደለም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ እንዲገለጥ ነው። 4ቀን ሆኖ ሳለ የላከኝን ሥራ መሥራት አለብኝ፤ ማንም ሰው ሊሠራ የማይችልበት ሌሊት ይመጣል። 5በዓለም ላይ ሳለሁ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ።” #ማቴ. 5፥14፤ ዮሐ. 8፥12።
6ይህን ከተናገረ በኋላ በመሬት ላይ እንትፍ አለና በምራቁ ዐፈር ለወሰ፤ በጭቃውም የዕውሩን ዐይኖች ቀባና፥ 7“ሄደህ በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ” አለው። (ሰሊሆም “የተላከ” ማለት ነው።) ስለዚህ ሰውየው ሄዶ ታጠበና እያየ ተመለሰ።
8ጐረቤቶቹና ቀድሞ ሲለምን ያዩት የነበሩ ሰዎች፥ “ይህ ሰው ያ ተቀምጦ ይለምን የነበረው አይደለምን?” አሉ። 9አንዳንዶች “አዎ፥ እርሱ ነው!” አሉ፤ ሌሎች ደግሞ “እርሱን ይመስላል እንጂ እርሱ አይደለም!” አሉ። እርሱ ግን “እኔው ነኝ!” አለ። 10ሰዎቹም “ታዲያ፥ ዐይኖችህ እንዴት ተከፈቱ?” አሉት። 11እርሱም “ኢየሱስ የተባለ ሰው ጭቃ ለውሶ ዐይኖቼን ቀባና ‘ወደ ሰሊሆም ሄደህ ታጠብ’ አለኝ፤ እኔም ሄጄ ታጠብኩና ለማየት ቻልኩ” ሲል መለሰ። 12እነርሱም “ሰውየው አሁን የት አለ?” አሉት። እርሱም “የት እንዳለ እኔ አላውቅም” አላቸው።
13ከዚህ በኋላ ሰዎቹ ዕውር የነበረውን ሰው ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት። 14ኢየሱስ ጭቃ ለውሶ የሰውዬውን ዐይኖች እንዲበሩ ያደረገው በሰንበት ቀን ነበር፤ 15ፈሪሳውያን “እንዴት ማየት ቻልክ?” ብለው ሰውየውን እንደገና ጠየቁት። እርሱም “ዐይኖቼ ላይ ጭቃ አደረገልኝና ታጠብኩ፤ ከዚያም በኋላ ማየት ቻልኩ” አለ።
16በዚህ ጊዜ ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ፥ “ይህ ሰው ሰንበትን ስለማያከብር ከእግዚአብሔር አይደለም” አሉ። ሌሎች ግን “ታዲያ፥ ኃጢአተኛ የሆነ ሰው እነዚህን ተአምራት እንዴት ማድረግ ይችላል?” አሉ። በዚህ ምክንያት በመካከላቸው መለያየት ሆነ።
17ስለዚህ ዕውር የነበረውን ሰው፥ “አንተስ ዐይኖችህን አበራልኝ ስለምትለው ስለዚያ ሰው ምን ትላለህ?” ሲሉ ደግመው ጠየቁት። እርሱም “ነቢይ ነው!” አለ። 18ይህ ሰው ዕውር እንደ ነበረና ዐይኖቹም በኋላ እንዴት እንደ ተከፈቱ ወላጆቹን ጠርተው እስከ ጠየቁአቸው ድረስ የአይሁድ ባለ ሥልጣኖች አላመኑም ነበር። 19ስለዚህ ወላጆቹን፥ “ዕውር ሆኖ ተወለደ የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነውን? አሁንስ እንዴት ማየት ቻለ?” ሲሉ ጠየቁአቸው።
20ወላጆቹም እንዲህ ሲሉ መለሱ፦ “ይህ ሰው ልጃችን መሆኑንና ዕውር ሆኖ መወለዱን እናውቃለን፤ 21ነገር ግን አሁን እንዴት እንደሚያይና ዐይኖቹንም ማን እንደአበራለት አናውቅም፤ እርሱን ጠይቁት፤ እርሱ በዕድሜው ሙሉ ሰው ስለ ሆነ ስለ ራሱ መናገር ይችላል።” 22ወላጆቹ ይህን ያሉት ኢየሱስን “መሲሕ ነው” የሚል ሰው ቢኖር የአይሁድ ባለሥልጣኖች ከምኲራብ ሊያስወጡት ተስማምተው ስለ ነበረ እነርሱን በመፍራት ነበር። 23ስለዚህ ወላጆቹ፥ “እርሱ በዕድሜው ሙሉ ሰው ነው፤ እርሱን ጠይቁት” አሉ።
24በዚህ ምክንያት ዕውር የነበረውን ሰው እንደገና ጠርተው “አንተ እውነቱን በመናገር እግዚአብሔርን አክብር፤ ይህ ሰው ኃጢአተኛ መሆኑን እኛ እናውቃለን” አሉት።
25ዕውር የነበረውም ሰው፥ “እርሱ ኃጢአተኛ መሆኑን እኔ አላውቅም፤ አንድ ነገር ዐውቃለሁ፤ ይኸውም እኔ ዕውር እንደ ነበርኩና አሁን ማየት እንደ ቻልኩ ብቻ ነው” ሲል መለሰ። 26እነርሱም “ምን አደረገልህ? ዐይኖችህንስ ያዳነው እንዴት ነው?” አሉት። 27እርሱም “አስቀድሜ ነገርኳችሁ፤ እናንተ ግን መስማት አልፈለጋችሁም፤ ታዲያ፥ ስለምን እንደገና መስማት ትፈልጋላችሁ? እናንተም የእርሱ ደቀ መዛሙርት መሆን ትፈልጋላችሁን?” አላቸው። 28እነርሱም እንዲህ እያሉ ሰደቡት፦ “የእርሱስ ደቀ መዝሙር አንተ ነህ፤ እኛ ግን የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን፤ 29እግዚአብሔር ሙሴን እንዳነጋገረው እናውቃለን፤ ይህ ሰው ግን ከየት እንደ ሆነ አናውቅም።”
30ሰውየውም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ይህ ሰው ከየት እንደ ሆነ አለማወቃችሁ ያስደንቃል! ነገር ግን ዐይኖቼን የአበራ እርሱ ነው። 31እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን እንደማይሰማ የታወቀ ነው፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን የሚያመልክና ፈቃዱንም የሚፈጽም ሰው ሲኖር እርሱን እግዚአብሔር ይሰማዋል። 32ዕውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ዐይኖች ያበራ አለ ሲባል ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ተሰምቶ አይታወቅም። 33ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ኖሮ ምንም ለማድረግ ባልቻለም ነበር።”
34እነርሱም “ሁለንተናህ በኃጢአት ተወርሶ የተወለድክ! አንተ እኛን ልታስተምር ነውን?” አሉና ከምኲራብ አስወጡት።
የልብ ዕውርነት
35ሰውየውን ከምኲራብ እንዳስወጡት ኢየሱስ ሰማ፤ ባገኘውም ጊዜ “በሰው ልጅ ታምናለህን?” አለው። 36እርሱም “ጌታ ሆይ! በእርሱ እንዳምን እርሱ ማን ነው?” አለ። 37ኢየሱስ “ከዚህ በፊት አይተኸዋል፤ አሁንም የሚያነጋግርህ እርሱ ነው” አለው። 38እርሱም “ጌታ ሆይ! አምናለሁ” ብሎ ሰገደለት። 39ኢየሱስም “የማያዩ እንዲያዩ፥ የሚያዩም እንዲታወሩ እኔ ወደዚህ ዓለም ለፍርድ መጥቼአለሁ” አለ። 40በዚያን ጊዜ በኢየሱስ አጠገብ የነበሩ ፈሪሳውያን ይህን ሰምተው “ታዲያ፥ እኛም ዕውሮች መሆናችን ነውን?” አሉት። 41ኢየሱስም “ዕውሮች ብትሆኑማ ኖሮ ኃጢአት ባልሆነባችሁም ነበር፤ አሁን ግን እናያለን ስለምትሉ፥ ኃጢአተኞች ሆናችሁ ትቀራላችሁ” አላቸው።
Currently Selected:
የዮሐንስ ወንጌል 9: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997