ትንቢተ ኤርምያስ 25
25
ከሰሜን የመጣ ጠላት
1የኢዮስያስ ልጅ ኢዮአቄም በይሁዳ በነገሠ በአራተኛው ዓመት እግዚአብሔር ስለ ይሁዳ ሕዝብ ተናገረኝ፤ ይህም የሆነው የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት ነበር፤ #2ነገ. 24፥1፤ 2ዜ.መ. 36፥5-7፤ ዳን. 1፥1-2። 2ስለዚህ ለይሁዳና ለኢየሩሳሌም ሕዝብ እንዲህ አልኳቸው፥ 3“የዓሞን ልጅ ኢዮስያስ በይሁዳ ከነገሠ ከዐሥራ ሦስተኛው ዓመት ጀምሮ እግዚአብሔር እስከ ዛሬ ድረስ ለኻያ ሦስት ዓመት ሲናገረኝ ቈይቶአል፤ የእርሱንም ቃል ለእናንተ ከመናገር ከቶ አልቦዘንኩም፤ እናንተ ግን ልብ ብላችሁ አላስተዋላችሁም፤ 4እግዚአብሔር በተከታታይ አገልጋዮቹን ነቢያቱን ቢልክላችሁም እናንተ ልብ ብላችሁ አላዳመጣችሁም፤ 5እነርሱም ‘እግዚአብሔር ለእናንተና ለቀድሞ አባቶቻችሁ በሰጣት በዚህች ምድር ለዘለዓለም መኖር ትችሉ ዘንድ ከመጥፎ አኗኗራችሁና ከክፉ ሥራችሁ ተመለሱ፤ 6ሌሎች አማልክትን አትከተሉ፥ አታገልግሉአቸው፤ አትስገዱላቸውም፤ በእጃችሁ ለሠራችኋቸው ጣዖቶች በመስገድ እግዚአብሔርን ለቊጣ አታነሣሡ፤ ይህን ትእዛዝ ብትጠብቁ እርሱ አይቀጣችሁም።’ 7እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘እኔን አልሰማችሁኝም፥ እጃችሁ በሠራው ጣዖት አስቆጣችሁኝ።’
8“አናዳምጥም ከማለታችሁም የተነሣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። 9‘እነሆ በስተሰሜን ወዳሉት ነገዶችና አገልጋዬ ወደ ሆነው ወደ ባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር መልእክተኛ እልካለሁ፤ ይሁዳንና በውስጥዋ የሚኖሩትን፥ እንዲሁም በጐረቤት ያሉትን ሕዝቦች ይወጉ ዘንድ አመጣቸዋለሁ፤ ይህችን አገር ከነጐረቤቶችዋ አጠፋለሁ፤ ለማየት የሚያስፈሩና መሳለቂያ እስኪሆኑ ድረስ ለዘለዓለም ፍርስራሽ ሆነው እንዲቀሩ አደርጋቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። 10የደስታና የሐሤት ድምፅ፥ የሠርግ ዘፈንም ድምፅ እንዳይኖር፥ ማንም ሰው እህል እንዳይፈጭ፥ ወይም በሌሊት መብራት እንዳያበራ አደርጋለሁ። #ኤር. 7፥34፤ 16፥9፤ ራዕ. 18፥22-23። 11ምድሪቱ በሙሉ ፍርስራሽና ባድማ ትሆናለች፤ እነዚህ ሕዝቦችም ለሰባ ዓመት ለባቢሎን ንጉሥ ይገዛሉ። #2ዜ.መ. 36፥21፤ ኤር. 29፥10፤ ዳን. 9፥2። 12ከዚህም በኋላ ሰባው ዓመት ሲፈጸም ባቢሎንን፥ ሕዝብዋንና ንጉሥዋን በበደላቸው ምክንያት እቀጣቸዋለሁ፤ የባቢሎንም ምድር ለዘለዓለም ባድማ ሆና እንድትቀር አደርጋለሁ፤ 13በኤርምያስ አማካይነት በሕዝብ ሁሉ ላይ አመጣለሁ ያልኩትን፥ ማለትም በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን መቅሠፍቶች ሁሉ በላይዋ ላይ በማውረድ ባቢሎንን እቀጣለሁ። 14ባቢሎናውያን ስላደረጉትም ክፋት ሁሉ ቅጣታቸውን እንዲያገኙ አደርጋለሁ፤ ብዙ ሕዝቦችና ታላላቅ ነገሥታት ባሪያ አድርገው ይገዙአቸዋል።’ ”
እግዚአብሔር በአሕዛብ ላይ የሚያመጣው ፍርድ
15የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “ይህን በቊጣዬ ወይን የተሞላ ጽዋ ከእጄ ውሰድ እኔ ወደምልክህ ሕዝቦች ሄደህ ከእርሱ እንዲጠጡ አድርግ። 16ከጽዋውም በጠጡ ጊዜ በእነርሱ ላይ ከምልከው ጦርነት የተነሣ ኅሊናቸውን ስተው ይንገዳገዳሉ።”
17ስለዚህ ጽዋውን ከእግዚአብሔር እጅ ወሰድኩና እግዚአብሔር ወደ ላከኝ ሕዝቦች ሁሉ ሄጄ እንዲጠጡት አደረግሁ፤ 18የኢየሩሳሌምና የይሁዳ ከተሞች ሕዝብ ከነገሥታቱና ከመኳንንቱ ጋር ከዚህ ጽዋ እንዲጠጡ ተደረገ፤ ከዚህም የተነሣ እነዚህ ስፍራዎች ለማየት እጅግ የሚያስፈራ በረሓ መሳደቢያና መራገሚያ ቦታዎች ይሆናሉ።
19-26ከጽዋው መጠጣት የሚገባቸው ሌሎች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፦
የግብጽ ንጉሥ ከባለሟሎቹና ከመኳንንቱ ሁሉ ጋር፥
የግብጽ ሕዝብና በግብጽ የሚኖሩ መጻተኞች ሁሉ፥
በዑፅ ምድር የሚኖሩ ነገሥታት ሁሉ፥
በፍልስጥኤማውያን ከተሞች፥ በአስቀሎና፥ በጋዛ፥
በዔቅሮንና በአሽዶድ፥ በሌሎች ቦታዎችም የሚኖሩ
የኤዶም፥ የሞአብና የዐሞን ሕዝቦች ሁሉ፥
የጢሮስና የሲዶና ነገሥታት ሁሉ፥
በሜዲትራኒያን ባሕር ዙሪያ በሚገኙ አገሮች ያሉ ነገሥታት ሁሉ፥
የደዳን፥ የቴማና የቡዝ ከተሞች ሁሉ፥
የግንባራቸውን ግራና ቀኝ ጠጒር የሚላጩ ሕዝቦች ሁሉ፥
የዐረብ አገር ነገሥታት ሁሉ፥
በበረሓ የሚኖሩ ነገዶች ነገሥታት ሁሉ፥
የዘምሪ፥ የዔላምና የሜዶን ነገሥታት ሁሉ፥
ሌሎችም በስተሰሜን በኩል በሩቅና በቅርብ ያሉ ነገሥታት ሁሉ በየተራቸው።
በምድር ላይ የሚኖሩት ሕዝብ ሁሉ፥ ከዚህ ጽዋ ይጠጣሉ፤ በመጨረሻም የባቢሎን ንጉሥ ከዚህ ጽዋ መጠጣት ይኖርበታል።
27ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የእስራኤል አምላክ እኔ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ከማመጣው ጦርነት የተነሣ ሰክረው እስከሚያስመልሳቸውና ወድቀውም መነሣት እስኪሳናቸው ድረስ እንዲጠጡ የማዛቸው መሆኔን ለሕዝቡ ንገር፤ 28ጽዋውን ከእጅህ ተቀብለው ለመጠጣት እምቢ የሚሉ ከሆነ፥ ‘ከዚህ ጽዋ መጠጣት እንዳለባችሁ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር አዞአል’ ብለህ ንገራቸው። 29እነሆ፥ ጥፋትን የስሜ መጠሪያ በሆነችው ከተማ እጀምራለሁ፤ ታዲያ ከቅጣት የሚያመልጡ ይመስላቸዋልን? እኔ በምድር በሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ ላይ ጦርነትን ስለማመጣ ከቶ ከቅጣት የሚያመልጡ የሉም፤ እኔ የሠራዊት አምላክ ይህን ተናግሬአለሁ።
30“ኤርምያስ ሆይ! አንተም እኔ የነገርኩህን ቃል ሁሉ ማወጅ አለብህ፤ እነዚህን ሕዝቦች እንዲህ በላቸው፦
‘እግዚአብሔር ከሰማይ ከፍተኛ ድምፅ ያሰማል፤
ከቅዱስ መኖሪያውም ነጐድጓድ ያሰማል፤
በምድሩም ላይ ከፍተኛ ድምፅ ያሰማል፤
ወይን እንደሚጨምቁ በከፍተኛ ድምፅ ይናገራል፤
በምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ከፍተኛ ድምፅ ያሰማል።
31እግዚአብሔር ሕዝቡን በሚገሥጽበት ጊዜ
የሚያሰማው ድምፅ
እስከ ምድር ዳርቻ ይደርሳል፤
በሕዝቦች ሁሉ ላይ ይፈርዳል፤
ክፉዎችንም በሞት ይቀጣል፤’
እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአል።”
32የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እነሆ በሕዝቦች ሁሉ ላይ በየተራ ጥፋት ይመጣል፤ በምድር ዳርቻዎች ሁሉ ላይ ታላቅ ዐውሎ ነፋስ ይነሣል። 33በዚያን ቀን እግዚአብሔር በሞት የሚቀጣቸው ሰዎች ሬሳ ከምድር ዳርቻ እስከ ምድር ዳርቻ ይረፈረፋል፤ የሚያለቅስላቸውም ሆነ ሰብስቦ የሚቀብራቸው አያገኙም፤ ስለዚህ እንደ ጥራጊ በሜዳ ላይ ተጥለው ይቀራሉ።
34“እናንተ መሪዎች አልቅሱ፤ እናንተ የሕዝብ ጠባቂዎች ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ‘ዋይ፥ ዋይ!’ በሉ፤ በዐመድ ላይ እየተንከባለላችሁ እዘኑ፤ ሁላችሁም የምትታረዱበት ጊዜ ደርሶአል፤ ውድ የሆነ የሸክላ ዕቃ ሲወድቅ ተሰብሮ እንደሚበታተን፥ እናንተም ትበታተናላችሁ። 35መሪዎቹ መሸሻ የላቸውም፤ የሕዝቡም ጠባቂዎች ማምለጥ አይችሉም። 36እረኞቹ ይጮኻሉ፤ እግዚአብሔር የመንጋዎቻቸውን መሰማሪያ ስላጠፋ የመንጋዎቹ ባለቤቶች ምርር ብለው ያለቅሳሉ። 37በእግዚአብሔር ኀይለኛ ቊጣ ምክንያትም ሰላማዊው መኖሪያቸው ፈራርሶአል። 38በጨቋኞች ሰይፍና በእግዚአብሔር ኀይለኛ ቊጣ ምክንያት ምድሪቱ ባድማ ስለ ሆነች ደቦል አንበሳ መኖሪያውን ጥሎ እንደሚሸሽ እነርሱም ይሸሻሉ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 25: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997