YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ኤርምያስ 15

15
በይሁዳ ሕዝብ ላይ የሚደርስ ፍርድ
1ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “ሙሴና ሳሙኤል እንኳ በፊቴ ቆመው ቢማልዱ ለዚህ ሕዝብ ምሕረት አላደርግም፤ ስለዚህ ከፊቴ ወዲያ እንዲሄዱ አድርግ። #ዘፀ. 32፥11-14፤ ዘኍ. 14፥13-19፤ 1ሳሙ. 7፥5-9። 2‘ታዲያ ወዴት እንሂድ?’ ብለው ቢጠይቁህ፥ ከዚህ በፊት እንዲህ ብዬ የነገርኳቸውን አስታውሳቸው፤
‘በመቅሠፍት እንዲሞቱ የተፈረደባቸው በመቅሠፍት ይሞታሉ!
በጦርነት እንዲሞቱ የተፈረደባቸው በጦርነት ይሞታሉ!
በራብ እንዲሞቱ የተፈረደባቸውም በራብ ይሞታሉ።
ተማርከው እንዲታሰሩ የተፈረደባቸው ወደ ምርኮ ይሂዱ።’ #ራዕ. 13፥10።
3እኔ እግዚአብሔር አራት ክፉ ነገሮች እንዲደርሱባቸው ወስኛለሁ፤ ስለዚህ
በጦርነት ይሞታሉ፤
ሬሳቸውን ውሾች ይጐትቱታል፤
ወፎች ሥጋቸውን ይበሉታል፤
የተረፈውን አራዊት ይግጡታል፤
4የሕዝቅያስ ልጅ ምናሴ በይሁዳ በነገሠበት ዘመን በኢየሩሳሌም ስለ ፈጸመው ክፋት ሁሉ በእነርሱ ላይ ከሚደርሰው ነገር የተነሣ የዓለም ሕዝብ እንዲሠቀቅ አደርጋለሁ።” #2ነገ. 21፥1-16፤ 2ዜ.መ. 33፥1-9።
5እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ! ማን ይራራላችኋል?
የሚያዝንላችሁስ ማን ነው?
ለአንድ አፍታ ቆም ብሎ ስለ ሁኔታችሁስ የሚጠይቅ ማን ነው?
6እናንተ እኮ እኔን ትታችሁኛል፤
እናንተ ወደ ኋላ ተመልሳችኋል፤
ከእንግዲህ ወዲያ ምሕረት አላደርግም፤
እጄን ዘርግቼ አደቃችኋለሁ።
7ገለባ በነፋስ እንደሚበተን፥
በምድሪቱ ውስጥ ባሉት ከተሞች ሁሉ በተንኳችሁ፤
ከክፉ ሥራችሁም ካለመመለሳችሁ የተነሣ፥
እናንተን ሕዝቤን አጠፋኋችሁ፤
ልጆቻችሁ ሁሉ እንዲገደሉ አደረግሁ።
8በምድራችሁ ላይ የሚገኙት ባሎቻቸው የሞቱባቸው ሴቶች
ብዛታቸው ከባሕር አሸዋ የሚበልጥ ሆኖአል፤
በእኩለ ቀን በወጣቶች እናቶች ላይ
ሞትን አመጣለሁ
በእነርሱም ላይ ሽብርንና ጭንቀትን በቅጽበት አመጣለሁ።
9ሰባት ልጆችዋን ያጣችው እናት፥
በታላቅ ተስፋ መቊረጥ ከእስትንፋስዋ ጋር እየታገለች ነው፤
የቀኑ ብርሃን ወደ ጨለማ ተለውጦባታል፤
ውርደትና ኀፍረት ደርሰውባታል፤
ገና በሕይወት ያላችሁትንም ጠላቶቻችሁ
እንዲገድሉአችሁ አደርጋለሁ፤
እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
ኤርምያስ ብሶቱን ለእግዚአብሔር እንደ ገለጠ
10እናቴ ሆይ፥ ወዮልኝ! ለምን ወለድሽኝ? ዕድል ፈንታዬ ከአገሪቱ ሕዝብ ሁሉ ጋር መከራከርና መነታረክ ሆኗል፤ እኔ ገንዘብ ለማንም አላበደርኩም ወይም ከማንም አልተበደርኩም፤ ሆኖም ሰው ሁሉ ይረግመኛል።
11ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “በእርግጥ ለመልካም ዓላማ እታደግሃለሁ፤ በችግርና በመከራ ጊዜ ጠላቶችህ አንተን እንዲለማመጡ አደርጋለሁ። #15፥11 አንዳንድ ትርጒሞች “እግዚአብሔር ሆይ! ስለደኅንነታቸው በሚገባ ሳላገለግልህ ቀርቼ ከሆነ፥ ችግርና መከራ በደረሰባቸው ጊዜ ስለ ጠላቶቼ አንተን ሳልማልድ ቀርቼ ከሆነ፥ ርግማናቸው ሁሉ ይድረስብኝ!” የሚል በዚህ ቊጥር ይጨምራሉ። 12የይሁዳ ሕዝብ ሆይ! ከነሐስ ጋር የተቀላቀለን ብረት ለመስበር እንደማትችሉ ሁሉ በሰሜን በኩል ከጠላት የተቃጣውን አደጋ ልታሸንፉ አትችሉም።”
13እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “በመላ ሀገሪቱ በፈጸማችሁት ኃጢአት ምክንያት ሀብታችሁንና ንብረታችሁን ያለ አንዳች ማካካሻ ለጠላት አሳልፌ እሰጣለሁ። 14ቊጣዬ ሊጠፋ እንደማይችል እሳት ነው። ስለዚህ በባዕድ ሀገር የጠላቶቻችሁ ባሪያዎች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ።”
15እኔም እንዲህ አልኩ፦ “እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እባክህ አስታውሰኝ፤ እርዳኝም፤ አሳዳጆቼን ተበቀልልኝ፤ ከትዕግሥትህ ብዛት የተነሣ እንድጠፋ አታድርገኝ፤ ይህም ስድብ የደረሰብኝ በአንተ ምክንያት ነው። 16የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! እኔ በስምህ ተጠርቼአለሁ፤ ቃልህ ወደ እኔ በመጣ ጊዜ በሙሉ ተቀብዬዋለሁ፤ ልቤንም በደስታና በሐሴት ሞላው። 17ከሚፈነጥዙ ሰዎች ጋር አልተወዳጀሁም፤ ከእነርሱም ጋር አልተደሰትኩም፤ ቊጣህ በእኔ ላይ ስለ ሆነ ብቻዬን ተቀመጥኩ። 18ሕመሜ የማይድነው፥ ቊስሌስ የማይጠገነውና የማይፈወሰው ለምንድን ነው? በበጋ ወራት እንደሚደርቅ ጅረት ተስፋ ታስቈርጠኛለህን?”
19እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰልኝ፦ “ወደ እኔ በንስሓ ብትመለስ፥ እቀበልሃለሁ፤ እንደገናም አገልጋይ ትሆነኛለህ፤ ከንቱ ቃል መናገርህን ትተህ ቁም ነገር ያለውን መልእክት ብታስተላልፍ፥ እንደገና የእኔ ነቢይ ትሆናለህ፤ ሕዝቡ ወደ አንተ ይመጣሉ እንጂ አንተ ወደ እነርሱ አትሄድም። 20እነርሱን መቋቋም እንድትችል እንደ ነሐስ ግንብ አበረታሃለሁ፤ አንተን ለማዳንና ለመታደግ ከአንተ ጋር ስለ ሆንኩ አደጋ ቢጥሉብህም እንኳ አያሸንፉህም። 21ከክፉዎች አድንሃለሁ፤ ከጨካኞችም እጅ እታደግሃለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in