መጽሐፈ መሳፍንት 3
3
ሳይባረሩ በምድሪቱ ላይ የቀሩ ሕዝቦች
1በከነዓን ምድር ጦርነት ያልተለማመዱ እስራኤላውያንን ለመፈተን እግዚአብሔር በምድሪቱ የተዋቸው ሕዝቦች እነዚህ ናቸው። 2ይህንንም ማድረጉ ቀድሞ የጦርነት ልምድ ያልነበራቸውን የእስራኤልን ትውልድ የጦርነት ስልት ለማስተማር ብሎ ብቻ ነው። 3በምድሪቱ ላይ የቀሩትም፥ አምስቱ የፍልስጥኤማውያን መሪዎች፥ ከነዓናውያን በሙሉ፥ ሲዶናውያንና ከባዓልሔርሞን ተራራ አንሥቶ እስከ ሐማት ድረስ በሊባኖስ ተራራዎች የሚኖሩት ሒዋውያን ነበሩ። 4እነርሱም እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት ለቀድሞ አባቶቻቸው የሰጣቸውን ትእዛዞች እስራኤላውያን ያከብሩ ወይም አያከብሩ እንደ ሆነ ለማወቅ ለእስራኤል መፈተኛዎች ነበሩ። 5በዚህም ዐይነት የእስራኤል ሕዝብ በከነዓናውያን፥ በሒታውያን፥ በአሞራውያን፥ በፈሪዛውያን፥ በሒዋውያንና በኢያቡሳውያን መካከል ኖሩ። 6የእነርሱን ሴቶች ልጆች አገቡ፤ እነርሱም ሴቶች ልጆቻቸውን ለወንዶች ልጆቻቸው ሰጡ፤ አማልክታቸውንም አመለኩ።
ዖትኒኤል
7የእስራኤል ሕዝብ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረጉ፤ አምላካቸውን እግዚአብሔርንም ትተው በዓልና አሼራን አመለኩ፤ 8ከዚህም የተነሣ የእግዚአብሔር ቊጣ በእስራኤል ሕዝብ ላይ ነደደ፤ ለመስጴጦምያው ንጉሥ ለኩሻን ፊሽዓታይም አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም ለኩሻን ሪሽዓታይም ስምንት ዓመት ተገዙለት፤ 9ከዚህ በኋላ እስራኤላውያን ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እግዚአብሔርም የሚያድናቸውን አዳኝ የካሌብ ታናሽ ወንድም ልጅ የሆነውን የቄኔዝን ልጅ ዖትኒኤልን አስነሣቸው። 10የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ ዐደረ፤ በእስራኤልም ላይ መሪ ሆነ፤ ለጦርነት በወጣ ጊዜ እግዚአብሔር የመስጴጦምያውን ንጉሥ ኩሻን ፊሽዓታይምን አሳልፎ ሰጠው፤ እርሱም ኩሻን ሪሽዓታይምን ድል አደረገው። 11በምድሪቱም ላይ ለአርባ ዓመት ያኽል ሰላም ሰፍኖ ከቈየ በኋላ የቄኔዝ ልጅ ዖትኒኤል ሞተ።
ኤሁድ
12የእስራኤል ሕዝብ እንደገና በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረጉ፤ በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር የሞአቡን ንጉሥ ዔግሎንን ከእስራኤል ይበልጥ የበረታ እንዲሆን አደረገው። 13ዔግሎንም ዐሞናውያንንና ዐማሌቃውያንን አስተባብሮ እስራኤልን ወጋ፤ የተምር ዛፍ የሞላባትንም የኢያሪኮን ከተማ በቊጥጥራቸው ሥር አደረጉ። 14የእስራኤል ሕዝብ ለዐሥራ ስምንት ዓመት ለሞአብ ንጉሥ ለዔግሎን ተገዢዎች ሆኑ።
15ከዚህ በኋላ የእስራኤል ሕዝብ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እግዚአብሔርም ከብንያም ነገድ ግራኝ የነበረውን የጌራን ልጅ ኤሁድን አዳኝ አድርጎ አስነሣቸው፤ የእስራኤል ሕዝብ ኤሁድን ግብር አስይዘው ወደ ሞአብ ንጉሥ ወደ ዔግሎን ላኩት። #3፥15 ኤሁድ፦ በግዕዙና በ 1954 ዓ.ም. በታተመው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ “ናዖድ” ይባላል። 16ኤሁድ ኀምሳ ሳንቲ ሜትር የሚያኽል ርዝመት ያለው በሁለት በኩል ስለ ታም የሆነ ሰይፍ ለራሱ አሠራ፤ እርሱንም በቀኝ ጭኑ በኩል በልብሱ ውስጥ ታጠቀው፤ 17ከዚያን በኋላ ሰውነቱ በጣም ወፍራም ለነበረው ለዔግሎን ግብሩን ይዞ ሄደ። 18ኤሁድ ግብሩን ለንጉሡ ካቀረበ በኋላ ግብሩን ተሸክመው የነበሩትን ሰዎች ወደ ቤታቸው ተመልሰው እንዲሄዱ አደረገ፤ 19ኤሁድ ራሱ ግን በጌልገላ አጠገብ ወዳሉት ተጠርበው ወደ ተተከሉ የጣዖት ድንጋዮች ዞር ብሎ ቈየ፤ ወደ ዔግሎንም ተመልሶ “ንጉሥ ሆይ! በግል ለአንተ የምነግርህ አንድ ምሥጢር አለኝ” አለው። እርሱም “ዝም በል” አለው።
ስለዚህም ንጉሡ ባለሟሎቹን “እስቲ አንድ ጊዜ ውጪ ቈዩልን!” አላቸው፥ እነርሱም በሙሉ ወጡ።
20በዚያን ጊዜ ንጉሡ በጣራው ላይ ባለው ነፋሻ ክፍል ለብቻው ተቀምጦ ሳለ፥ ኤሁድ ወደ እርሱ ቀረብ ብሎ “ከእግዚአብሔር ለአንተ የተላከ መልእክት አለኝ” አለው፤ ንጉሡም ብድግ ብሎ ቆመ። 21ኤሁድም ሰይፉን ከቀኝ ጭኑ በግራ እጁ መዞ በንጉሡ ሆድ ውስጥ ሻጠ፤ 22እጀታው ሳይቀር ሰይፉ በሙሉ ወደ ሆድ ዕቃው ገባ፤ እስከ ጀርባውም ዘለቀ፤ ሞራውም ሰይፉን ሸፈነው፤ ኤሁድም ሰይፉን ከንጉሡ ሆድ አላወጣውም። 23ከዚያን በኋላ ኤሁድ ወደ ውጪ ወጣ፤ በሮቹንም ዘግቶ ቈለፈበት። 24ኤሁድ ከሄደ በኋላ የንጉሡ አገልጋዮች መጥተው በሮቹ እንደ ተቈለፉ አዩ፤ ነገር ግን ንጉሡ ከውስጥ በኩል በመጸዳዳት የዘገየ መሰላቸው፤ 25መቈየት የሚገባቸውን ያኽል በውጪ ቈዩ፤ ነገር ግን አሁንም በሩ እንዳልተከፈተ ባዩ ጊዜ ቊልፉን ወስደው በሩን ከፈቱ፤ እዚያም ጌታቸው ሞቶ በወለል ላይ መዘርጋቱን ተመለከቱ።
26እነርሱ እዚያው ቆመው በሚጠባበቁበት ጊዜ ኤሁድ ርቆ ሄዶ ነበር፤ ተጠርበው የተተከሉ የጣዖት ድንጋዮችን አልፎ ወደ ሰዒራ አመለጠ፤ 27እዚያም ወደ ኮረብታማው ወደ ኤፍሬም አገር እንደ ደረሰ በኤፍሬም ተራራማው አገር የክተት እምቢልታ ነፋ፤ የእስራኤልም ሕዝብ በእርሱ መሪነት ተከትለውት ወረዱ። 28እንዲህም አላቸው “እኔን ተከተሉኝ! እግዚአብሔር በጠላቶቻችሁ በሞአባውያን ላይ ድልን ያጐናጽፋችኋል።” ስለዚህም እነርሱ ኤሁድን ተከትለው ወረዱ፥ ሞአባውያን የዮርዳኖስን ወንዝ የሚሻገሩበትን ስፍራ ያዙ፤ አንድ ሰው እንኳ በዚያ አልፎ እንዲሄድ አላደረጉም፤ 29በዚያን ቀን ብቻ ወደ ዐሥር ሺህ የሚያኽሉ ምርጥ የሆኑ የሞአባውያን ወታደሮችን ገደሉ፤ ከእነርሱ መካከል ማንም ያመለጠ አልነበረም። 30በዚያን ቀን ሞአባውያን በእስራኤላውያን ድል ተመቱ፤ በምድሪቱም ላይ ሰማኒያ ዓመት ሙሉ ሰላም ሆነ።
ሻምጋር
31ከዚያም ቀጥሎ የነበረው መሪ የዐናት ልጅ ሻምጋር ነበር፤ እርሱም ስድስት መቶ ፍልስጥኤማውያንን በበሬ ቀንድ በመግደል፥ የእስራኤልን ሕዝብ አዳነ።
Currently Selected:
መጽሐፈ መሳፍንት 3: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997