YouVersion Logo
Search Icon

የያዕቆብ መልእክት 4

4
የዓለምን ክፋት አለመውደድ
1በእናንተ መካከል ያለው ጦርነትና ጠብ ከየት የመጣ ነው? በሰውነታችሁ ውስጥ ከሚዋጋው ከሥጋዊ ምኞታችሁ አይደለምን? 2አንድን ነገር ለማግኘት ትመኛላችሁ፤ ግን አታገኙም፤ ስለዚህ ሰውን ትገድላላችሁ። ስለማትጸልዩም የምትፈልጉትን ነገር አታገኙም። 3ብትጸልዩም የጸሎታችሁን መልስ የማታገኙት የለመናችሁትን ነገር በሥጋዊ ደስታ ላይ ለማዋል በክፉ ሐሳብ ስለምትጸልዩ ነው። 4እናንተ ከዳተኞች! ዓለምን የሚወድ የእግዚአብሔር ጠላት መሆኑን አታውቁምን? እንግዲህ ዓለምን የሚወድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት መሆኑ ነው። 5ደግሞስ ቅዱስ መጽሐፍ “እግዚአብሔር በውስጣችሁ ያሳደረው መንፈስ ለእርሱ ብቻ እንድንሆን በብርቱ ይመኛል” ያለው በከንቱ ነውን? 6ሆኖም መጽሐፍ “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑቶች ግን ጸጋን ይሰጣል” ስለሚል እግዚአብሔር የሚሰጠው ጸጋ ከሁሉም ይበልጣል።
7ስለዚህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙት፤ እርሱም ከእናንተ ይሸሻል። 8ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል፤ እናንተ ኃጢአተኞች! እጆቻችሁን አጽዱ፤ እናንተ ወላዋዮች! ልባችሁን አጥሩ። 9ተጨነቁ፤ እዘኑ፤ አልቅሱ፤ ሳቃችሁ ወደ ለቅሶ፥ ደስታችሁ ወደ ሐዘን ይለወጥ። 10በጌታ ፊት ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ እርሱም ከፍ ያደርጋችኋል።
በሰው ላይ አለመፍረድ
11ወንድሞች ሆይ፥ እርስ በርሳችሁ አትተማሙ፤ ሰውን የሚያማ ወይም በሰው ላይ የሚፈርድ ሕግን ያማል፤ በሕግም ላይ ይፈርዳል፤ በሕግ ላይ ብትፈርድ ደግሞ ፈራጅ መሆንህ ነው እንጂ ሕግን ፈጻሚ አይደለህም። 12ሕግን የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ ሊያድንም ሊያጠፋም የሚችል እርሱ ብቻ ነው፤ ታዲያ፥ በሰው ላይ የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?
ስለ ትምክሕት የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
13እናንተ “ዛሬ ወይም ነገ ወደ እንዲህ ያለ ከተማ ሄደን እዚያ አንድ ዓመት እንቀመጣለን፤ ነግደንም እናተርፋለን” የምትሉ ተጠንቀቁ። 14ነገ የሚሆነውን አታውቁም፤ ሕይወታችሁ ምንድን ነው? ለአንድ አፍታ ታይቶ በኋላ እንደሚጠፋ ጉም ናችሁ። #ምሳ. 27፥1። 15ይልቁንስ እናንተ ማለት የሚገባችሁ “ጌታ ቢፈቅድና ብንኖር ይህን ወይም ያን እናደርጋለን” ነው። 16እናንተ ግን ይህን በማለት ፈንታ በትዕቢታችሁ ትመካላችሁ፤ እንዲህ ያለው ትምክሕት ሁሉ ክፉ ነው።
17እንግዲህ መልካም ነገር ማድረግን እያወቀ የማያደርግ ሰው አለማድረጉ ኃጢአት ይሆንበታል።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy