YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ኢሳይያስ 55

55
የእግዚአብሔር የምሕረት ጥሪ
1እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ ወደ ውሃው ኑ!
የምትገዙበት ገንዘብ የሌላችሁ ኑና ገዝታችሁ ብሉ!
ኑና ያለ ገንዘብና ያለ ዋጋ ወተትና የወይን ጠጅን ግዙ። #ራዕ. 21፥6፤ 22፥17።
2ለማይጠቅም ምግብ ገንዘባችሁን ለምን ታወጣላችሁ?
ለማያጠግብ ነገር ጒልበታችሁን ለምን ታባክናላችሁ?
አሁንም በጥንቃቄ አድምጡኝና መልካም የሆነውን ምግብ ብሉ፤
በምርጥ ምግብም ራሳችሁን አስደስቱ።
3“ጆሮአችሁን አዘንብላችሁ ወደ እኔ ቅረቡ፤
በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ቃሌን አድምጡ፤
ዳዊትን እንደ ወደድኩት
እናንተን በታማኝነት ለመውደድ
ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን እገባለሁ። #ሐ.ሥ. 13፥34።
4እነሆ እርሱን ለሕዝቦች ምስክር፥
መሪና አለቃ አድርጌዋለሁ።
5እኔ የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔር አምላክህ ስላከበርኩህ
እነሆ፥ የማታውቃቸውን ሕዝቦች ትጠራለህ፤
የማያውቁህም ሕዝቦች ወደ አንተ ይፈጥናሉ።”
6በሚገኝበት ጊዜ እግዚአብሔርን ፈልጉት፤
በሚቀርብበትም ጊዜ ጥሩት።
7ክፉዎች አካሄዳቸውን፥
ኃጢአተኞች ክፉ ሐሳባቸውን ይተዉ፤
ምሕረቱ ብዙ ስለ ሆነ ይቅር ይላቸው ዘንድ
ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ይመለሱ።
8እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“ሐሳቤ እንደ ሐሳባችሁ፥
መንገዴም እንደ መንገዳችሁ አይደለም።
9ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥
መንገዴ ከመንገዳችሁ፥
ሐሳቤም ከሐሳባችሁ እጅግ ከፍ ያለ ነው።
10“ዝናብና ደቃቅ በረዶ ከሰማይ ወርደው
ምድርን በማርካት ፍሬ እንድታፈራ እንደሚያደርጓትና
ለዘሪው ዘርን፥ ለበላተኛውም ምግብን ሳይሰጡ
ወደ ሰማይ እንደማይመለሱ፥ #2ቆሮ. 9፥10።
11ከእኔ አንደበት የሚወጣውም ቃል እንደዚሁ ነው።
እርሱ የላክሁትን ጉዳይ ሳያከናውንና
ተልእኮውን ሳይፈጽም ወደ እኔ አይመለስም።
12“እናንተም ከባቢሎን በደስታ ወጥታችሁ፥
በሰላም ወደ ሀገራችሁ እንድትመለሱ ትደረጋላችሁ፤
ተራራዎችና ኰረብቶች በፊታችሁ በመዘመር ይፈነድቃሉ፤
የሜዳ ዛፎችም በእጆቻቸው ያጨበጭባሉ።
13በእሾኽ ፈንታ ዝግባ በኲርንችትም ፈንታ ባርሰነት ይበቅላል፤
እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ለመታሰቢያና
ለዘለዓለምም የማይጠፋ ምልክት ይሆናል።”

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in