ትንቢተ ኢሳይያስ 47
47
በባቢሎን ላይ የሚመጣ ፍርድ
1እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“አንቺ በማንም ያልተደፈርሽ የባቢሎን ከተማ ሆይ!
ወርደሽ በዐቧራ ላይ ተቀመጪ፤
ወርደሽ በዙፋን ላይ ሳይሆን፤
በመሬት ላይ ተቀመጪ፤
ከእንግዲህ ወዲያ ቅምጥልና ለስላሳ መባልሽ ይቀራል። #ኢሳ. 13፥1—14፥23፤ ኤር. 50፥1—51፥64።
2እንግዲህ መጅ አንሥተሽ ዱቄት ፍጪ፤
ዐይነ ርግብሽን ግለጪ፤ ካባሽን አውልቂ፤
ቀሚስሽን ከፍ አድርገሽ በተራቈተ ቅልጥም ወንዙን ተሻገሪ።
3ሕዝብ ሁሉ ተራቊተሽ ያዩሻል፤
ኀፍረትሽ ይጋለጣል፤
እኔ ማንንም ሳልምር ሁሉን እበቀላለሁ።”
4አዳኛችን የሠራዊት አምላክ ነው፤
ስሙም የእስራኤል ቅዱስ ነው።
5እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“ባቢሎን ሆይ! በጨለማ ውስጥ ጸጥ ብለሽ ተቀመጪ፤
ከእንግዲህ ወዲህ ‘የመንግሥታት ንግሥት’ ብለው አይጠሩሽም፤
6እኔ በሕዝቤ ላይ ተቈጥቼ ነበር፤
እነርሱንም እንደ ርኩስ ቈጥሬ፥
ለአንቺ አሳልፌ ሰጠኋቸው፤
አንቺ ግን ርኅራኄ አላደረግሽላቸውም፤
በዕድሜ በገፉት ሰዎች ላይ የጭቈና ቀንበር አበዛሽባቸው።
7‘እኔ ለዘለዓለም ንግሥት ሆኜ እኖራለሁ’ አልሽ፤
ስላደረግሽው ድርጊት ምንም አላሰብሽም፤
የተግባርሽም ውጤት ምን እንደሚሆን አላስተዋልሽም።
8“አንቺ በልብሽ ‘እንደ እኔ ያለ ማንም የለም፤
ባልዋ እንደ ሞተባት ሴት ሆኜ አልኖርም፤
ወይም የልጅ ሞት አይደርስብኝም’ ብለሽ
በመዝናናት የተቀመጥሽው ቅምጥሊቱ ሆይ!
ይህን ስሚ፦
9እነዚህ ሁለቱም ነገሮች በቅጽበት በአንድ ቀን በአንቺ ላይ ይደርሳሉ፤
ምንም ያኽል መተትሽ ትልቅ፥ ጥንቈላሽም
ብዙ ቢሆን የልጆችና የባል ሞት
በአንቺ ላይ በሙላት ይደርሳል። #ራዕ. 18፥7-8።
10“በክፋትሽ ተዝናናሽ፤ ‘ማንም አያየኝም’ አልሽ፤
ጥበብሽና ዕውቀትሽ አባከኑሽ፤
በልብሽም ‘ማንም እንደኔ ያለ የለም’ አልሽ።
11በመተትሽ ልታስወግጂ የማትችይው ክፉ ነገር ይመጣብሻል፤
ልትከላከዪ የማትችይው ችግር ይደርስብሻል፤
ምንም ያላሰብሽው ጥፋት በድንገት ያጋጥምሻል።
12እስኪ ከሆነልሽ ከሕፃንነትሽ ጊዜ ጀምሮ
ስትጠቀሚባቸው የኖርሽውን
ያፍዝ አደንግዝ ድግምትና የጥንቈላ መተቶችን አስቀምጪ፤
ምንአልባት ጥቂት ይረዳሽ ይሆናል፤
ወይም ጠላቶችሽን ልታስፈራሪባቸው ትችያለሽ፤
13የተቀበልሻቸው ምክሮች ሁሉ ያደክሙሻል እንጂ
ምንም አይጠቅሙሽም፤
በየወሩ መባቻ ከዋክብትን የሚመለከቱ ኮከብ ቈጣሪዎችሽ ወደፊት ይምጡ፤
በአንቺ ላይ ከሚደርሰውም ችግር ያድኑሽ።
14“እነሆ፥ እነርሱ እንደ ገለባ እሳት ይበላቸዋል፤
ከነበልባሉ ኀይል ራሳቸውን ሊያድኑ አይችሉም፤
ገለባውም ራስን ለማሞቅ ፍም አይኖረውም።
15ከወጣትነትሽ ጀምሮ ከአንቺ ጋር ለመጠንቈል ይመላለሱ
የነበሩት አስማተኞችም ሁሉ እንደዚሁ በተሳሳተ መንገድ ይባክናሉ፤
ስለዚህ አንቺን ማንም ሊያድንሽ አይችልም።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 47: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997