YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ኢሳይያስ 45

45
እግዚአብሔር ቂሮስን ለንጉሥነት እንደ መረጠው
1ሕዝቦች በሥልጣኑ ሥር እንዲገዙ ለማድረግ፥
ነገሥታትን ከሥልጣን እንዲያወርድ፥
የከተሞችን ቅጽር በሮች ይከፍትለት ዘንድ
ቀኝ እጁን ለያዘውና ቀብቶ ላነገሠው ንጉሥ
ቂሮስን እግዚአብሔር እንዲህ ይለዋል፦
2“እኔ በፊትህ እሄዳለሁ፤
ተራራዎችን ዝቅ አድርጌ እደለድላለሁ፤
በነሐስ የተሠሩ በሮችንና የብረት መወርወሪያዎችን እሰብራለሁ።
3በጨለማና በድብቅ ቦታ የተከማቸውን ሀብት እሰጥሃለሁ።
በዚህም በስምህ የምጠራህ የእስራኤል አምላክ
እግዚአብሔር እኔ እንደ ሆንኩ ታውቃለህ።
4የመረጥኳቸውን የያዕቆብን ልጆች እስራኤላውያንን እንድትረዳ፥
አንተ እኔን ባታውቀኝም እንኳ በስምህ ጠርቼሃለሁ፤
የማዕርግ ስምም ሰጥቼሃለሁ።
5“እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፤
አንተ እኔን ባታውቀኝም እንኳ ብርታትን እሰጥሃለሁ።
6ይህንንም የማደርገው መላው ዓለም
እኔ ብቻ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩና
ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ ያውቅ ዘንድ ነው።
7እኔ ጨለማንና ብርሃንን እፈጥራለሁ፤
ደኅንነትንና ወዮታን አመጣለሁ፤
እኔ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ አደርጋለሁ።
8እናንተ ከላይ ያላችሁ ሰማያት! ጽድቅን እንደ ዝናብ አውርዱ፤
ደመናም ያርከፍክፈው፤
ምድር ትከፈት፤ ደኅንነትም ያቈጥቊጥ፤
እኔ እግዚአብሔር የፈጠርኩት ስለ ሆነ ጽድቅም ከእርሱ ጋር ይብቀል።”
እግዚአብሔር የፍጥረትና የታሪክ ባለቤት መሆኑ
9ከሠሪው ጋር ለሚከራከር ወዮለት!
እርሱ እኮ ከሸክላ ዕቃዎች እንደ አንዱ ነው፤
አንድ የሸክላ ሥራ ሸክላ ሠሪውን
“ምንድን ነው የምታደርገው? እጀታውስ የት አለ?”
ብሎ ሊጠይቅ ይችላልን? #ሮም 9፥20።
10ወይስ ልጅ ወላጆቹን
“ለምን እንዲህ አድርጋችሁ ወለዳችሁኝ?”
ብሎ ሊጠይቅ ይችላልን?
11ቅዱስ የእስራኤል አምላክና፥
ፈጣሪ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“ስለ ልጆቼ ልትጠይቁኝና
ወይም ስለ እጆቼ ሥራ ምን ማድረግ እንደሚገባኝ
ልታዙኝ ትደፍራላችሁን?
12ምድርን የፈጠርኩና
ሰውንም ፈጥሬ በእርስዋ እንዲኖር ያደረግኹ እኔ ነኝ፤
ሰማያትን በኀይሌ የዘረጋሁና
ሠራዊቶቻቸውን የምቈጣጠር እኔ ነኝ።”
13የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦
“ቂሮስን ለጽድቅ ሥራ አነሣሥቼዋለሁ፤
መንገዱንም አቀናለታለሁ፤
ከተማዬን ኢየሩሳሌምን እንደገና ይሠራታል፤
በስደት ላይ ያሉ ሕዝቤንም ነጻ ያወጣል፤
ይህንንም የሚያደርገው ማንም ገንዘብ እንዲከፍለው
ወይም ውለታውን እንዲመልስለት አይደለም።”
የሠራዊት አምላክ ይህን ተናግሮአል።
14እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“የግብጽ ሀብትና የኢትዮጵያ ሸቀጥ ለእናንተ ተላልፎ ይሰጣል፤
ቁመታቸው ረጃጅም የሆነ የሳባ ሰዎችም
በሰንሰለት ታስረው በመምጣት ይከተሉአችኋል፤
እጅ ነሥተውም፦ ‘እግዚአብሔር የሚገኘው
በእናንተ ዘንድ ብቻ ነው፤ በሌላ አይደለም፤
ከእርሱም በቀር ሌላ አምላክ የለም’ ይላሉ።”
15አዳኙ የእስራኤል አምላክ ሆይ!
በእውነት የአንተ ሥራ ከሰው ማስተዋል የተሰወረ ነው።
16ጣዖቶችን የሚሠሩ ሁሉ ያፍራሉ፤ ይዋረዳሉ፤
ሁሉም በአንድነት ይዋረዳሉ።
17እናንተ የእስራኤል ሕዝብ ግን ከእግዚአብሔር በሚሰጣችሁ
ዘለዓለማዊ ደኅንነት ትድናላችሁ፤
ለዘለዓለምም ኀፍረትና ውርደት ከቶ አይደርስባችሁም።
18ሰማያትን የፈጠረው እርሱ እግዚአብሔር ነው፤
ለምድር ቅርጽ ሰጥቶ የሠራት፥ የመሠረታትም እርሱ ነው፤
የፈጠራትም መኖሪያ እንድትሆን ነው እንጂ፥
ቅርጽ የሌላትና ባዶ እንድትሆን አይደለም፤
እርሱ፦ “ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም፤
19ጨለማ በሆነ አገር በድብቅ አልተናገርኩም፤
የያዕቆብን ልጆች፦ ‘ቅርጽ በሌለው ቦታ ፈልጉኝ’ አላልኳቸውም፤
እኔ እግዚአብሔር እውነቱን እናገራለሁ፤
ትክክል የሆነውንም ነገር እገልጣለሁ።
20“ከየሀገሩ ከስደት ተርፋችሁ የተመለሳችሁ፥
ተሰብስባችሁ በአንድነት ቅረቡ!
የእንጨት ጣዖቶችን ይዘው የሚዘዋወሩና
ማዳን ወደማይችል ጣዖት የሚጸልዩ
ዕውቀት የሌላቸው ናቸው።
21ጉዳይህን አቅርበህ ገለጻ አድርግ፤
ከብዙ ጊዜ በፊት ይህን የተናገሩ ተሰብስበው ይመካከሩ፤
በጥንት ጊዜ የተናገረው ማነው?
እኔ እግዚአብሔር አልነበርኩምን?
ከእኔ በቀር ጻድቅና አዳኝ አምላክ የለም።
22“ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ ስለሌለ፥
እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ያላችሁ ሁሉ
ወደ እኔ ተመልሳችሁ ደኅንነትን አግኙ።
23የማይለወጥ እውነተኛ የተስፋ ቃል ስሰጥ በራሴ ምዬ ነው።
ስለዚህ ጉልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፤
አንደበትም ሁሉ በእኔ ስም ይምላል። #ሮም 14፥11፤ ፊል. 2፥10-11።
24“ ‘ጽድቅና ኀይል የሚገኘው ከእግዚአብሔር ብቻ ነው’ ብለው ስለ እኔ ይናገራሉ፤
የሚጠሉኝ ሁሉ ወደ እኔ መጥተው በዕፍረት ላይ ይወድቃሉ።
25ነገር ግን የእስራኤል ልጆች ሁሉ
በእኔ በእግዚአብሔር ድልንና ክብርን ያገኛሉ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in