ትንቢተ ኢሳይያስ 17
17
እግዚአብሔር ሶርያንና እስራኤልን እንደሚቀጣ
1ስለ ደማስቆ የተነገረ የእግዚአብሔር ቃል፦ “እነሆ ደማስቆ ከእንግዲህ ወዲህ ከተማነትዋ ቀርቶ የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች፤ 2የሶርያ ከተሞች ሰው የማይኖርባቸው ባድማዎች ይሆናሉ፤ በጎችና ከብቶች በዚያ ይሰማራሉ፤ የሚያስፈራቸውም አይኖርም። 3እስራኤል ያለ መከላከያ ትቀራለች፤ ደማስቆም ነጻነትዋን ትገፈፋለች፤ ከጥፋት የተረፉ እነዚያ ሶርያውያን እንደ እስራኤል ሕዝብ የተዋረዱ ይሆናሉ፤ እኔ የሠራዊት አምላክ ይህን ተናግሬአለሁ። #ኤር. 49፥23-27፤ አሞጽ 1፥3-5፤ ዘካ. 9፥1።
4“በዚያን ቀን የእስራኤል ታላቅነት ይዋረዳል፤ ብልጽግናቸውም ጠፍቶ ይደኸያሉ። 5እስራኤል እህሉ ታጭዶ መከር ከተሰበሰበ በኋላ ባዶውን እንደሚቀር እርሻ ትሆናለች፤ ከመከር በኋላ የተራቈተ የራፋይምን ሸለቆም ትመስላለች። 6እስራኤል በላይኛው ቅርንጫፍ ላይ ሁለት ወይም ሦስት ፍሬዎች ብቻ እንዳሉት፥ እንዲሁም በታችኛው ቅርንጫፉ ላይ አራት ወይም አምስት ፍሬዎች እንደ ቀሩበት የወይራ ዛፍ ትሆናለች፤ ሆኖም ጥቂት ሕዝቦች ይተርፋሉ። እኔ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
7ያም ቀን ሲደርስ ሕዝቡ ርዳታ ለማግኘት ወደ እስራኤል ቅዱስ ወደ ፈጣሪአቸው ይመለሳሉ፤ 8ከዚያን በኋላ በገዛ እጃቸው በሠሩት መሠዊያ መታመናቸው ይቀራል፤ እንዲሁም የእጃቸው ሥራ በሆኑት በአሼራ ምስልና ዕጣን ሊያጥኑባቸው በሠሩአቸው መሠዊያዎች መተማመናቸውን ይተዋሉ።
9በዚያን ጊዜ እስራኤላውያን አደጋ ባደረሱባቸው ጊዜ የሒዋውያንና የአሞራውያን ከተሞች ባድማ እንደ ሆኑት የእናንተም ጠንካራ ከተሞች ባድማዎች ይሆናሉ።
10እስራኤል ሆይ እናንተ እንደ ጽኑ አለት መከላከያ ሆኖ የተቤዣችሁን እግዚአብሔርን ረስታችኋል፤ ስለዚህ ከፍ ያለ ዋጋ ያለው ድንቅና ብርቅ የሆነ ተክል ብትተክሉና 11በዚያው በተከላችሁት ቀን አድጎ ቢያብብ እንኳ ከቶ አታመርቱትም፤ በዚህ ፈንታ የምታመርቱት ችግርና የማይፈወስ በሽታ ይሆናል።
እግዚአብሔር ለሕዝቡ እንደሚከላከል
12እንደ ባሕር ሞገድ ድምፀ ለሚያሰሙ ለብዙ ወገን ስብስቦች ወዮላቸው! እንደ ኀይለኛ ጐርፍ ለሚጣደፉ ሕዝቦች ወዮላቸው! 13ሕዝቦች እንደ ኀይለኛ ውሃ ድምፅ ያሰማሉ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሲገሥጻቸው በተራራ ላይ ገለባዎች በነፋስ እንደሚበተኑና በዐውሎ ነፋስም ዐቧራ እንደሚበተን ርቀው ይሸሻሉ። 14በምሽት ጊዜ እነሆ፥ ሽብር ይሆናል፤ በማለዳ ግን ይጠፋሉ፤ የሚዘርፉንና የሚበዘብዙን ሰዎችም ዕድል ፈንታ ይኸው ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 17: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997