ወደ ዕብራውያን የተላከ መልእክት 7
7
ካህኑ መልከጼዴቅ
1መልከጼዴቅ የሳሌም ንጉሥና የልዑል እግዚአብሔር ካህን ነበር፤ ይህ መልከጼዴቅ አብርሃም ነገሥታትን አሸንፎ ሲመለስ በመንገድ ተገናኝቶ ባረከው። 2አብርሃምም ከያዘው ነገር ሁሉ ዐሥራት አውጥቶ ሰጠው፤ የመልከ ጼዴቅ የስሙ ትርጓሜ አንደኛው “የጽድቅ ንጉሥ” ሌላው “የሳሌም ንጉሥ” ወይም “የሰላም ንጉሥ” ማለት ነው። 3መልከጼዴቅ በጽሑፍ የታወቀ አባትና እናት ወይም የትውልድ ሐረግ የለውም፤ ለዘመኑ መጀመሪያ፥ ለሕይወቱም መጨረሻ የለውም፤ ይህ መልከጼዴቅ እንደ እግዚአብሔር ልጅ ምሳሌ በመሆን ለዘለዓለም ካህን ሆኖ ይኖራል።
4ይህ ሰው እንዴት ታላቅ እንደ ሆነ ተመልከቱ፤ የነገድ አባት የሆነው አብርሃም እንኳ በምርኮ ካገኘው ነገር ዐሥራት አውጥቶ ሰጠው። 5እነዚያ በክህነት ሥራ ላይ የሚመደቡት የሌዊ ዘሮች ከሕዝቡ ከአብርሃም ዘር ማለትም ከወንድሞቻቸው ዐሥራት እንዲቀበሉ በሕግ ታዞላቸዋል፤ #ዘኍ. 18፥21። 6ያ መልከጼዴቅ የሌዋውያን ዘር ባይሆንም እንኳ ከአብርሃም ዐሥራትን ተቀበለ፤ የተስፋ ቃል የተሰጠውን አብርሃምንም ባረከው። 7ታናሹ ከታላቁ ቡራኬን እንደሚቀበል ጥርጥር የለውም። 8በአንድ በኩል ዐሥራት የሚቀበሉት ሟች የሆኑት ናቸው፤ በሌላ በኩል ግን ዐሥራት የሚቀበለው ሕያው ሆኖ እንደሚኖር የተመሰከረለት መልከጼዴቅ ነው። 9-10እንግዲህ መልከጼዴቅ አብርሃምን በተገናኘው ጊዜ ሌዊ ከአባቱ ከአብርሃም ገና ስላልተወለደ ዐሥራትን መቀበል የሚገባው ሌዊ ራሱ በአብርሃም አማካይነት ዐሥራትን ከፍሎአል ማለት ነው።
11እንግዲህ ለሕዝቡ ሕግ የተሰጠው በሌዊ ክህነት መሠረት ነው፤ በዚህ በሌዋውያን ክህነት ፍጹምነት ቢገኝ ኖሮ የአሮን የክህነት ሹመት ሳይሆን የመልከ ጼዴቅ የክህነት ሹመት ያለው ሌላ ካህን መምጣት ባላስፈለገም ነበር፤ 12የክህነት ሐረጉ ሲለወጥ ሕጉም አብሮ መለወጥ አለበት። 13ይህ ሁሉ የተነገረለት ካህን ከሌላ ነገድ ነው፤ ከዚህ ነገድ ማንም ወደ መሠዊያው ቀርቦ ያገለገለ የለም። 14ጌታችን ከይሁዳ ነገድ መሆኑ የታወቀ ነው፤ ሆኖም ሙሴ ስለ ካህናት ሲናገር የይሁዳን ነገድ አስመልክቶ የተናገረው ምንም ነገር የለም።
ክርስቶስ እንደ መልከጼዴቅ ያለ ካህን መሆኑ
15ይህ ነገር በጣም ግልጥ ሆኖ የሚገኘው እንደ መልከጼዴቅ ያለ ሌላ ካህን በሚነሣበት ጊዜ ነው፤ 16እሱ የክህነት ሹመትን የተቀበለው ለሕይወቱ ፍጻሜ የሌለው በመሆኑ ነው እንጂ ከዘር በመጣ ሥርዓትና ሕግ አይደለም። 17“እንደ መልከጼዴቅ የክህነት ሹመት አንተ ለዘለዓለም ካህን ነህ” ተብሎ ተመስክሮለታል። #መዝ. 110፥4። 18የቀድሞው ትእዛዝ ደካማና የማይጠቅም ስለ ሆነ ተሽሮአል 19በሙሴ ሕግ ምንም ነገር ፍጹም ሊሆን አልቻለም፤ አሁን ግን ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት የተሻለ ተስፋ ተሰጥቶናል።
20ከዚህም በቀር ይህ ክህነት ያለ እግዚአብሔር መሐላ አልሆነም፤ እነዚያ ከዚህ በፊት ካህናት የሆኑት ያለ መሐላ ነው፤ 21ኢየሱስ ግን ካህን የሆነው በእግዚአብሔር መሐላ ነው፤ ይህም፦
“እግዚአብሔር ‘አንተ ለዘለዓለም ካህን ነህ’ ብሎ ምሎአል፤
አይለውጥም” ተብሎ በተነገረለት መሠረት ነው። #መዝ. 110፥4።
22በዚህ መሐላ ምክንያት ኢየሱስ ለተሻለው ቃል ኪዳን ዋስ ሆኖአል።
23በሞት ምክንያት አንድ ካህን ሳይለወጥ በሥራው ላይ ለዘለዓለም መኖር ስለማይችል የቀድሞዎቹ ካህናት ቊጥራቸው ብዙ ነበር፤ 24ኢየሱስ ግን ለዘለዓለም የሚኖር በመሆኑ ክህነቱ የማይለወጥ ነው። 25ስለዚህ እነርሱን ለማማለድ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ ስለሚኖር በእርሱ አማካይነት ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ሁሉ በፍጹም ሊያድናቸው ይችላል። 26እንዲህ ያለው ቅዱስ፥ ነቀፋ የሌለበት፥ ንጹሕ፥ ከኃጢአተኞች የተለየ፥ ከሰማይ በላይ ከፍ ያለ የካህናት አለቃ ያስፈልገናል። 27እርሱ እንደ ሌሎቹ የካህናት አለቆች በመጀመሪያ ስለ ራሱ ኃጢአት፥ በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት በየቀኑ መሥዋዕት ማቅረብ አያስፈልገውም፤ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ባቀረበ ጊዜ ይህን ነገር በማያዳግም ሁኔታ ፈጽሞታል። #ዘሌ. 9፥7። 28ሕግ የካህናት አለቆች አድርጎ የሚሾማቸው ደካሞች ሰዎችን ነው፤ ከሕግ በኋላ የመጣው የመሐላ ቃል ግን ለዘለዓለም ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔርን ልጅ ሾሞአል።
Currently Selected:
ወደ ዕብራውያን የተላከ መልእክት 7: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997