YouVersion Logo
Search Icon

ኦሪት ዘፍጥረት 50

50
1ዮሴፍ በአባቱ ሬሳ ላይ ወደቀና ፊቱን እየሳመ አለቀሰ። 2ከዚህ በኋላ ዮሴፍ አገልጋዮቹ የሆኑትን መድኃኒት ቀማሚዎች የአባቱን ሬሳ መልካም መዓዛ ባለው ሽቶ እያሹ እንዲያደርቁት ትእዛዝ ሰጠ። 3መድኃኒት ቀማሚዎቹም በሀገሩ ልማድ መሠረት ሬሳውን ለማድረቅ አርባ ቀን ፈጀባቸው። ግብጻውያን ሰባ ቀን ሙሉ አለቀሱለት።
4የለቅሶው ወራት በተፈጸመ ጊዜ ዮሴፍ የፈርዖንን ባለ ሥልጣኖች እንዲህ አላቸው፦ “መልካም ፈቃዳችሁ ቢሆን እባካችሁ ለፈርዖን፥ 5‘አባቴ ለመሞት ሲቃረብ በከነዓን ምድር ባዘጋጀው መቃብር እንድቀብረው በመሐላ ቃል አስገብቶኛል፤ ስለዚህ እዚያ ሄጄ አባቴን ቀብሬ እንድመለስ ይፈቀድልኝ ሲል ጠይቆአል’ ብላችሁ ንገሩልኝ” አላቸው። #ዘፍ. 47፥29-31።
6ፈርዖንም ይህን ሰምቶ “ቃል በገባህለት መሠረት ሄደህ አባትህን ቅበር” አለው።
7ስለዚህ ዮሴፍ አባቱን ለመቅበር ሄደ፤ የፈርዖን ባለሥልጣኖችና በቤተ መንግሥቱ የሚገኙ ታላላቅ ሰዎች፥ ሌሎችም የግብጽ መኳንንት ዮሴፍን ተከትለው ሄዱ። 8እንዲሁም የዮሴፍ ቤተሰቦች፥ ወንድሞቹና ሌሎችም የአባቱ ቤተሰቦች ሁሉ ከዮሴፍ ጋር ሄዱ፤ በጌሴም የቀሩት ሕፃናት ልጆቻቸው፥ በጎቻቸው፥ ፍየሎቻቸውና ከብቶቻቸው ብቻ ነበሩ። 9ባለ ሠረገሎችና ፈረሰኞች ተከትለውት ወጡ፤ በጠቅላላው የተከተለው አጀብ እጅግ ብዙ ነበር።
10ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ “አጣድ” ተብላ ወደምትጠራው አውድማ ደረሱ፤ እዚያም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በመጮኽ አለቀሱ፤ ዮሴፍም እዚያ ሰባት ቀን ሙሉ የሐዘን ውሎ አደረገ። 11በዚያ የሚኖሩ ከነዓናውያን በአጣድ አውድማ ለቅሶውን ባዩ ጊዜ “ይህ የግብጻውያን ለቅሶ እንዴት መሪር ነው?” አሉ። በዚህ ምክንያት በዮርዳኖስ ሜዳ ያለው የዚያ ቦታ ስም “አቤል ምጽራይም” ተባለ፤ ትርጒሙም በዕብራይስጥ “የግብጻውያን ለቅሶ” ማለት ነው።
12በዚህ ሁኔታ የያዕቆብ ልጆች አባታቸው እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ 13አስከሬኑን ወደ ከነዓን ወስደው ከመምሬ በስተምሥራቅ በምትገኘው በማክፌላ ዋሻ ቀበሩት፤ ይህም ዋሻ አብርሃም ለመቃብር ቦታ እንዲሆን ከሒታዊው ከዔፍሮን በገዛው እርሻ ውስጥ የሚገኝ ነው። #ሐ.ሥ. 7፥16። 14ዮሴፍ አባቱን ከቀበረ በኋላ ከወንድሞቹና ለቀብር አጅበውት ከሄዱት ሰዎች ሁሉ ጋር ሆኖ ወደ ግብጽ ተመለሰ።
ዮሴፍ ወንድሞቹን ማረጋጋቱ
15የዮሴፍ ወንድሞች አባታቸው ከሞተ በኋላ “ዮሴፍ ባደረስንበት በደል ሁሉ እስከ አሁንም ቂም ይዞ ሊበቀለን ቢፈልግ ምን እናደርጋለን?” ተባባሉ። 16ስለዚህ እንዲህ የሚል መልእክት ወደ ዮሴፍ ላኩ፤ “አባትህ ከመሞቱ በፊት፥ 17‘ወንድሞችህ በበደሉህ ጊዜ ያደረሱብህን ጒዳት ሁሉ አትቊጠርባቸው ብሎሃል’ ብለን እንድንነግርህ አዞናል፤ ስለዚህ እኛ የአባትህ አምላክ አገልጋዮች ያደረስንብህን በደል ሁሉ ይቅር እንድትለን እንለምንሃለን።” ዮሴፍ ይህን በሰማ ጊዜ አለቀሰ።
18ከዚህ በኋላ ወንድሞቹ ራሳቸው በፊቱ ቀርበው ጐንበስ ብለው እጅ ነሡና “እነሆ እኛ ሁላችን አገልጋዮችህ ነን” አሉት።
19ነገር ግን ዮሴፍ እንዲህ አላቸው፤ “አይዞአችሁ አትፍሩ፤ እኔ በእግዚአብሔር ምትክ የምሆን አይደለሁም፤ 20በእርግጥ እናንተ ክፉ ነገር መክራችሁብኝ ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ወደ መልካም ነገር ለወጠው፤ ይህንንም ያደረገው አሁን በሕይወት ያሉትን የብዙ ሰዎችን ሕይወት ለማትረፍ ብሎ ነው። 21ምንም የሚያስፈራችሁ ነገር የለም፤ እኔ እናንተንና ልጆቻችሁን እመግባችኋለሁ።”
በዚህም ዐይነት በመልካም ንግግር በማጽናናት አረጋጋቸው።
የዮሴፍ መሞት
22ዮሴፍ ከአባቱ ቤተሰቦች ጋር በግብጽ ተቀመጠ፤ ከዚያም ዕድሜው መቶ ዐሥር ዓመት እስኪሆነው ኖረ፤ 23የኤፍሬምንም ልጆችና የልጅ ልጆች እስከሚያይ ድረስ ቈየ፤ ከምናሴ የተወለደውንም የማኪርንም ልጆች እንደ ልጆቹ አድርጎ ተቀበላቸው።
24ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ እኔ የምሞትበት ጊዜ ተቃርቦአል፤ እናንተን ግን እግዚአብሔር በረድኤት ይጐበኛችኋል፤ ከዚህም አገር አውጥቶ ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ለመስጠት በመሐላ ቃል ወደ ገባላቸው ምድር ይመልሳችኋል። 25እግዚአብሔር በሚጐበኛችሁና ወደዚያች ምድር በሚመልሳችሁ ጊዜ ዐፅሜን ከዚህ ይዛችሁ የምትወጡ መሆናችሁን በማረጋገጥ ቃል ግቡልኝ” ብሎ አስማላቸው። #ዘፀ. 13፥19፤ ኢያሱ 24፥32፤ ዕብ. 11፥22።
26ዮሴፍም ዕድሜው መቶ ዐሥር ዓመት ሲሞላው ሞተ፤ አስከሬኑንም በሽቶ አሽተው በማድረቅ በግብጽ ምድር በሣጥን ውስጥ አኖሩት።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in