ኦሪት ዘፍጥረት 42
42
የዮሴፍ ወንድሞች ወደ ግብጽ መሄዳቸው
1ያዕቆብ በግብጽ እህል መኖሩን በሰማ ጊዜ ልጆቹን “እርስ በርሳችሁ እየተያያችሁ የምትቀመጡት ለምንድን ነው? 2በግብጽ አገር እህል መኖሩን ሰምቼአለሁ፤ በራብ እንዳንሞት ወደዚያ ሂዱና እህል ሸምቱልን” አላቸው። #ሐ.ሥ. 7፥12። 3ስለዚህ ዐሥሩ የዮሴፍ ወንድሞች እህል ለመሸመት ወደ ግብጽ ሄዱ፤ 4ነገር ግን “ጒዳት ይደርስበታል” ብሎ ስለ ፈራ ያዕቆብ ከዮሴፍ ጋር ከአንድ እናት የወለደውን ልጁን ብንያምን ከወንድሞቹ ጋር ወደ ግብጽ አላከውም፤ 5በከነዓን ምድርም ራብ ገብቶ ስለ ነበር የያዕቆብ ልጆች ከሌሎች ሰዎች ጋር እህል ለመሸመት ወደ ግብጽ ሄዱ።
6ዮሴፍ የግብጽ ምድር አስተዳዳሪ በመሆኑ ከዓለም ዙሪያ ለሚመጡ ሰዎች ሁሉ እህል እንዲሸጥላቸው ያደርግ ነበር፤ ስለዚህ የዮሴፍ ወንድሞች ወደ እርሱ መጡና ግንባራቸው መሬት እስኪነካ ዝቅ ብለው እጅ ነሡት። 7ዮሴፍ ወንድሞቹን ባያቸው ጊዜ ዐወቃቸው፤ ነገር ግን የማያውቃቸው በመምሰል በቊጣ ቃል “ከየት ነው የመጣችሁት?” ብሎ ጠየቃቸው።
እነርሱም “እህል ለመሸመት ከከነዓን አገር መጣን” አሉት።
8ዮሴፍ ወንድሞቹን ያወቃቸው ቢሆንም እንኳ እነርሱ አላወቁትም ነበር፤ 9ስለ እነርሱ ያየው ሕልም ሁሉ ትዝ አለውና “እናንተ ሰላዮች ናችሁ፤ የመጣችሁትም የአገራችንን ደካማነት እምን ላይ እንደ ሆነ ለመሰለል ነው” አላቸው። #ዘፍ. 37፥5-10።
10እነርሱም “ጌታችን ሆይ፥ እኛ ሰላዮች አይደለንም፤ እኛ አገልጋዮችህ እዚህ የመጣነው እህል ለመግዛት ነው” አሉት። 11“እኛ ሁላችን የአንድ ሰው ልጆች ነን፤ እኛ የምንታመን ነን፤ ሰላዮችም አይደለንም” አሉት።
12ዮሴፍም “አይደለም! እናንተ የመጣችሁት የአገራችንን ደካማነት በምን በኩል እንደ ሆነ ለመሰለል ነው” አላቸው።
13እነርሱም “እኛ አገልጋዮችህ በከነዓን ምድር የሚኖር የአንድ ሰው ልጆች የሆንን ዐሥራ ሁለት ወንድማማቾች ነን፤ አንዱ ወንድማችን ሞቶአል፤ የመጨረሻ ታናሽ ወንድማችን አሁን ከአባታችን ጋር ይገኛል” አሉት።
14ዮሴፍም እንዲህ አላቸው “ይኸው እኔ እንዳልኩት ያለ ጥርጥር ሰላዮች ናችሁ፤ 15እንግዲህ ታማኝነታችሁ ተፈትኖ የሚረጋገጠው በዚህ ነው፤ ታናሽ ወንድማችሁ እስከሚመጣ ድረስ እንደማልለቃችሁ በንጉሡ በፈርዖን ስም እምላለሁ። 16ከእናንተ አንዱ ሄዶ ወንድማችሁን ያምጣ፤ የተናገራችሁት እውነት መሆኑ ተረጋግጦ ነጻ እስክትለቀቁ ድረስ የቀራችሁት እዚሁ በእስር ቤት ትቈያላችሁ አለበለዚያ ግን በፈርዖን ስም እምላለሁ፤ እናንተ ሰላዮች ናችሁ።” 17ከዚህ በኋላ ሦስት ቀን አስሮ አቈያቸው።
18በሦስተኛው ቀን ዮሴፍ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ እግዚአብሔርን የምፈራ ሰው ስለ ሆንኩ እንዲህ ብታደርጉ ሕይወታችሁን ታድናላችሁ፤ 19እናንተ ታማኞች ሰዎች ከሆናችሁ ከእናንተ አንዱ እዚሁ በእስር ቤት ይቈይ፤ የቀራችሁት እህሉን ይዛችሁ ወደ ተራቡት ዘመዶቻችሁ ሂዱ። 20ከዚህ በኋላ ታናሽ ወንድማችሁን ይዛችሁልኝ ኑ፤ በዚህ ዐይነት የተናገራችሁት ሁሉ እውነት መሆኑ ይረጋገጣል፤ ከመሞትም ትድናላችሁ።”
እነርሱም በዚህ ነገር ተስማሙ፤ 21እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ “በእርግጥ በወንድማችን ላይ ስላደረስነው በደል ተገቢውን ቅጣት በመቀበል ላይ ነን፤ ምሕረት እንድናደርግለት ተጨንቆ ሲለምነን ልመናውን አልተቀበልንም ነበር፤ በእኛም ላይ ይህ ጭንቀት ሊደርስብን የቻለው በዚህ ምክንያት ነው።”
22ሮቤልም “እኔ በልጁ ላይ ጒዳት እንዳታደርሱ ነግሬአችሁ ነበር፤ ነገር ግን አልሰማችሁኝም፤ እነሆ፥ እርሱን በመግደላችን በቀሉን እየተቀበልን ነው” አላቸው። #ዘፍ. 37፥21-22። 23ዮሴፍ እነርሱ የሚሉትን ሁሉ ያዳምጥ ነበር፤ እነርሱ ግን ከዮሴፍ ጋር የሚነጋገሩት በአስተርጓሚ ስለ ነበር የእነርሱን ንግግር ዮሴፍ እንደሚሰማቸው አላወቁም። 24ዮሴፍ ከእነርሱ ነጠል ብሎ አለቀሰ፤ እንደገናም ወደ እነርሱ ተመልሶ አነጋገራቸውና ስምዖንን ከመካከላቸው ወስዶ በፊታቸው አሰረው።
የዮሴፍ ወንድሞች ወደ ከነዓን መመለሳቸው
25ዮሴፍ አገልጋዮቹን “ለእነዚህ ሰዎች በየስልቻዎቻቸው እህል ሙሉላቸው፤ ገንዘባቸውንም መልሳችሁ በየስልቻዎቻቸው ውስጥ ቋጥሩላቸው፤ ለጒዞአቸውም ስንቅ አስይዙአቸው” ብሎ አዘዘ። ይህም ከተደረገላቸው በኋላ፥ 26የዮሴፍ ወንድሞች የገዙትን እህል በአህዮቻቸው ጭነው ጒዞ ጀመሩ።
27በመንገድ ላይ ሳሉ ለዐዳር በሰፈሩበት ቦታ ከእነርሱ አንዱ ለአህያው ጥሬ ለመስጠት ስልቻውን በፈታ ጊዜ በስልቻው አፍ ላይ ገንዘቡ ተቋጥሮ አገኘው። 28እርሱም ለወንድሞቹ “ገንዘቤ ተመልሶልኛል፤ ይኸው በስልቻዬ ውስጥ አገኘሁት!” ብሎ ነገራቸው። ሁሉም በፍርሃት ተንቀጥቅጠው “እግዚአብሔር ያደረገብን ይህ ነገር ምንድን ነው?” ተባባሉ።
29በከነዓን ወዳለው ወደ አባታቸው ወደ ያዕቆብ ተመለሱ፤ የደረሰባቸውን ሁሉ እንዲህ ብለው ነገሩት፥ 30“የግብጽ አገር አስተዳዳሪ ‘አገሬን ልትሰልሉ የመጣችሁ ናችሁ’ በማለት በቊጣ ቃል ተናገረን፤ 31እኛም ‘ታማኞች ሰዎች ነን እንጂ ሰላዮች አይደለንም፤ 32እኛ የአንድ ሰው ልጆች የሆንን ዐሥራ ሁለት ወንድማማቾች ነን፤ አንዱ ጠፍቶአል፤ የመጨረሻ ታናሽ ወንድማችን በከነዓን ከአባታችን ጋር አለ’ አልነው። 33ሰውየውም እንዲህ አለን፤ ‘ታማኞች ሰዎች መሆናችሁን የማውቀው ይህን አንድ ነገር ብታደርጉ ነው፤ ይኸውም ከእናንተ አንዱ ከእኔ ጋር ይቈይ፤ ሌሎቻችሁ ለተራቡት ቤተሰቦቻችሁ እህል ይዛችሁ ወደ አገራችሁ ተመለሱ፤ 34ታናሽ ወንድማችሁንም ይዛችሁልኝ ኑ፤ በዚህ ዐይነት ታማኞች ሰዎች መሆናችሁንና ሰላዮችም አለመሆናችሁን አረጋግጣለሁ፤ ወንድማችሁንም መልሼ እሰጣችኋለሁ፤ በዚህም አገር ቈይታችሁ እንደ ፈለጋችሁ መነገድ ትችላላችሁ።’ ”
35ከዚህ በኋላ እህላቸውን ከስልቾቻቸው ባራገፉ ጊዜ በየስልቻዎቻቸው ውስጥ ገንዘባቸውን እንደ ተቋጠረ አገኙ፤ እነርሱና አባታቸው የተመለሰውን ገንዘብ ባዩ ጊዜ እጅግ ፈሩ። 36በዚህ ጊዜ አባታቸው “ልጆቼን ሁሉ እንዳጣ ትፈልጋላችሁን? ዮሴፍ የለም፤ ስምዖንም የለም፤ አሁን ደግሞ ብንያምን ለመውሰድ ትፈልጋላችሁ፤ በዚህ ሁሉ መከራ የምሠቃየው እኔ ነኝ!” አለ።
37ሮቤል አባቱን እንዲህ አለው፤ “ብንያምን ወደ አንተ መልሼ ባላመጣው ሁለቱን ወንዶች ልጆቼን ወስደህ ግደላቸው፤ ስለዚህ በእኔ ኀላፊነት ላከው፤ እኔም መልሼ አመጣዋለሁ።”
38ያዕቆብም “ምንም ቢሆን ከእናንተ ጋር አይሄድም፤ ወንድሙ ሞቶአል፤ የቀረው እርሱ ብቻ ነው፤ በመንገድ አንድ ጒዳት ቢደርስበት በእርጅናዬ ዘመን በመሪር ሐዘን ወደ መቃብር እንድወርድ ታደርጉኛላችሁ” አላቸው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 42: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997