YouVersion Logo
Search Icon

ኦሪት ዘፍጥረት 24

24
የይስሐቅና የርብቃ ጋብቻ
1በዚህ ጊዜ አብርሃም በጣም አርጅቶ ነበር፤ እግዚአብሔርም አብርሃምን በሁሉም ነገር ባረከው። 2አብርሃም የንብረቱ ሁሉ ኀላፊ በመሆን ለረዥም ዘመን የኖረውን አገልጋዩን እንዲህ አለው፤ “እጅህን በጒልበቴ ላይ አድርገህ ማልልኝ፤ #24፥2 “በጒልበቴ ላይ” ወይም “ከጭኔ በታች” በዕብራይስጥ ባህል የሚያሳየው የማይለወጥ መሐላ መሆኑን ነው። 3ይኸውም እኔ በመካከላቸው ከምኖረው ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች መካከል ለልጄ ሚስት እንዳትመርጥ በሰማይና በምድር አምላክ በእግዚአብሔር ስም ማልልኝ፤ 4ነገር ግን ወደ ትውልድ አገሬ ሂድ፤ እዚያም ካሉት ወገኖቼ መካከል ለልጄ ለይስሐቅ ሚስት ምረጥለት።”
5አገልጋዩም “ምናልባት የምመርጥለት ሴት ከእኔ ጋር ወደዚህ አገር ለመምጣት እምቢ ብትልስ? ልጅህን ቀድሞ አንተ ወደነበርክበት አገር እንዲመለስ ላድርገውን?” ብሎ ጠየቀ።
6አብርሃም ግን እንዲህ አለው፤ “በምንም ምክንያት ቢሆን ልጄን ወደዚያ አገር መልሰህ እንዳትወስድ ተጠንቀቅ! 7ከአባቴ ቤትና ከትውልድ አገሬ አውጥቶ ይህን ምድር ለዘሬ እንደሚሰጥ በመሐላ ቃል የገባልኝ እግዚአብሔር፥ የሰማይ አምላክ ከዚያ ለልጄ ሚስት ማግኘት እንድትችል መልአኩን በፊትህ ይልካል። 8ልጅትዋ ከአንተ ጋር ለመምጣት ፈቃደኛ ባትሆን ከዚህ መሐላ ነጻ ትሆናለህ፤ ልጄን ግን በምንም ዐይነት ወደዚያ አትመልሰው።” 9ከዚህ በኋላ አገልጋዩ እጁን በጌታው በአብርሃም ጒልበት ላይ አድርጎ አብርሃም ያዘዘውን ሁሉ እንደሚፈጽም በመሐላ ቃል ገባ።
10የአብርሃም ንብረት ኀላፊ የነበረው መጋቢ ከጌታው ቤት ምርጥ የሆኑ የስጦታ ዕቃዎችን በዐሥር ግመሎች ጭኖ በሰሜን መስጴጦምያ ናኮር ወደሚኖርበት ከተማ ሄደ። 11እዚያ በደረሰ ጊዜ ከከተማው ውጪ ባለ የውሃ ጒድጓድ አጠገብ ግመሎቹ ተንበርክከው እንዲያርፉ አደረገ፤ ሰዓቱም ሊመሽ ተቃርቦ፥ ሴቶች ውሃ ለመቅዳት የሚወጡበት ጊዜ ነበር፤ 12አገልጋዩም እንዲህ ብሎ ጸለየ፤ “የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ ዛሬ የእኔን ሐሳብ በመፈጸም ለጌታዬ ለአብርሃም ዘለዓለማዊ ፍቅርህን ግለጥ። 13እነሆ፥ እኔ በዚህ የውሃ ጒድጓድ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ የከተማይቱም ልጃገረዶች ውሃ ሊቀዱ ወደዚህ ይመጣሉ፤ 14ከእነርሱም አንድዋን ልጃገረድ ‘እንስራሽን ዘንበል አድርገሽ ውሃ አጠጪኝ’ እላታለሁ፤ ‘አንተም ጠጣ፤ ግመሎችህም እንዲጠጡ ውሃ ቀድቼ አመጣለሁ’ ካለችኝ ለአገልጋይህ ለይስሐቅ ሚስት እንድትሆን የመረጥካት እርስዋ ትሁን፤ በዚህም ሁኔታ ለጌታዬ ለአብርሃም ዘለዓለማዊ ፍቅርህን እንዳሳየኸው ዐውቃለሁ።”
15ገና ጸሎቱን ሳይጨርስ ርብቃ እንስራ ተሸክማ መጣች፤ የዚህችም ልጅ አባት በቱኤል ይባል ነበር፤ እርሱም የአብርሃም ወንድም ናኮር ከሚስቱ ከሚልካ የወለደው ነው። 16ርብቃ ገና ወንድ ያልደረሰባት በጣም ቈንጆ ልጃገረድ ነበረች፤ እርስዋ ወደ ውሃው ጒድጓድ ወርዳ በእንስራዋ ውሃ ከቀዳች በኋላ ተመለሰች። 17አገልጋዩም ወደ እርስዋ ሮጦ ሄደና “እባክሽ ከእንስራሽ ጥቂት ውሃ አጠጪኝ” አላት።
18እርስዋም “እሺ ጌታዬ ጠጣ” አለችና እንስራዋን ከትከሻዋ አውርዳ ዘንበል አድርጋ ያዘችለት። 19ጠጥቶም ከረካ በኋላ “ለግመሎችህም ውሃ እቀዳላቸዋለሁ፤ እስኪበቃቸውም ድረስ ይጠጡ” አለችው። 20ወዲያውኑ በእንስራዋ የያዘችውን ውሃ ግመሎቹ በሚጠጡበት ገንዳ ላይ ገልብጣ ግመሎቹ ሁሉ ጠጥተው እስከሚረኩ ድረስ እየተጣደፈች ከጒድጓድ ውሃ መቅዳት ቀጠለች። 21ሰውየውም እግዚአብሔር የሄደበትን ተልእኮ አቃንቶለት እንደሆን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ሁሉ ዝም ብሎ ይመለከት ነበር።
22ግመሎቹ ጠጥተው ካበቁ በኋላ ሰውየው አምስት ግራም ያኽል የሚመዝን የወርቅ ጒትቻ አውጥቶ በጆሮዋ ላይ አደረገላት፤ መቶ ዐሥር ግራም ያኽል የሚመዝን ሁለት የወርቅ አምባሮችንም አውጥቶ በእጆችዋ ላይ አደረገላትና፥ 23“የማን ልጅ ነሽ? እስቲ እባክሽ ንገሪኝ፤ ለእኔና አብረውኝ ላሉት ሰዎች ማደሪያ የሚሆን ስፍራ በአባትሽ ቤት ይገኛልን?” ብሎ ጠየቃት።
24እርስዋም “የባቱኤል ልጅ ነኝ፤ ባቱኤልም ሚልካ ለናኮር የወለደችለት ነው፤ 25በቤታችን ብዙ ገለባና ድርቆሽ አለ፤ ለእናንተም ማደሪያ ቦታ ይገኛል” አለችው።
26ሰውየውም በመንበርከክ ለእግዚአብሔር ሰግዶ፥ 27“ለጌታዬ ያለውን ታማኝነትና ዘለዓለማዊ ፍቅር የጠበቀ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፤ በቀጥታ መርቶ ወደ ጌታዬ ዘመዶች ቤት ያመጣኝ እርሱ ነው” አለ።
28ልጅትዋ ወደ ቤት ሮጣ ሄደችና የሆነውን ሁሉ ለእናትዋና ከእርስዋ ጋር ላሉት ሁሉ ነገረቻቸው። 29ርብቃ ላባ የተባለ ወንድም ነበራት፤ እርሱ የአብርሃም አገልጋይ ወዳለበት ውሃ ጒድጓድ እየሮጠ ሄደ። 30ላባ ወደ ሰውየው የሄደው እኅቱ በጆሮዋ ላይ ያደረገችውን ጒትቻና በእጆችዋ ላይ ያደረገቻቸውን አንባሮች ስላየና ርብቃ ሰውየው ያላትን ስትናገር ስለ ሰማም ነው። እርሱንም በውሃው ጒድጓድ አጠገብ ከግመሎቹ ጋር ቆሞ አገኘው። 31ስለዚህ ላባ “አንተ እግዚአብሔር የባረከህ ሰው፥ ና ወደ ቤት እንሂድ፤ በውጪ የቆምከው ለምንድን ነው? በቤታችን ለአንተ ማረፊያ ስፍራ አለ፤ ለግመሎችህም ማደሪያ የተዘጋጀ ቦታ አለ” አለው።
32ከዚህ በኋላ ሰውየው ወደ ቤት ሄደ፤ ላባም በግመሎቹ ላይ የነበረውን ጭነት አራግፎ ገለባና ድርቆሽ አቀረበላቸው፤ ቀጥሎም የአብርሃም አገልጋይና አብረውት የነበሩት ሰዎች እግራቸውን የሚታጠቡበት ውሃ አመጣላቸው። 33ገበታ በቀረበ ጊዜ ሰውየው “የተላክሁበትን ጉዳይ ከመናገሬ በፊት እህል አልቀምስም” አለ። ላባም “ይሁን ተናገር” አለው።
34እርሱም “እኔ የአብርሃም አገልጋይ ነኝ፤ 35እግዚአብሔር ጌታዬን እጅግ ባርኮታል፤ ባለጸጋም አድርጎታል፤ ብዙ የበግ፥ የፍየልና የከብት መንጋ፥ ብርና ወርቅ፥ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮች ግመሎችና አህዮች ሰጥቶታል። 36የጌታዬ ሚስት ሣራ በእርጅናዋ ዘመን ወንድ ልጅ ወልዳለታለች፤ ጌታዬም ያለውን ሀብት ሁሉ ለዚሁ ልጅ አውርሶታል። 37ጌታዬም እንዲህ ሲል አስማለኝ፤ እኔ ካለሁበት አገር ከከነዓናውያን ሴቶች ለልጄ ሚስት አትምረጥ፤ 38ነገር ግን ወደ አባቴ ቤት ወደ ወገኖቼ ሄደህ ለልጄ ሚስት ምረጥ፤ 39እኔም ጌታዬን ‘ልጅቷ ከእኔ ጋር ለመምጣት ፈቃደኛ ባትሆንስ ምን ላድርግ?’ ብዬ ጠየቅሁት። 40እርሱም እንዲህ አለኝ ‘ዘወትር የማገለግለው እግዚአብሔር መልአኩን ከአንተ ጋር ይልካል፤ ጒዞህም የተቃና እንዲሆን ያደርጋል፤ በዚህ ሁኔታ አንተም ከአባቴ ቤተሰብና ከዘመዶቼ መካከል ለልጄ ሚስት ልታጭለት ትችላለህ፤ 41ከመሐላህ ነጻ የምትሆነው ወደ ዘመዶቼ ሄደህ እነርሱ ልጅትዋን አንሰጥም ብለው የከለከሉህ እንደ ሆነ ብቻ ነው።’
42“ከዚህም በኋላ ዛሬ ወደ ውሃው ጒድጓድ ስመጣ እንዲህ ብዬ ጸለይኩ፤ ‘የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ እባክህ የመጣሁበት ጉዳይ እንዲቃና አድርግልኝ፥ 43እነሆ፥ በዚህ የውሃ ጒድጓድ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ አንዲት ልጃገረድ ውሃ ልትቀዳ ስትመጣ፥ እባክሽ ከእንስራሽ ጥቂት ውሃ አጠጪኝ’ ብዬ እጠይቃታለሁ፤ 44እርስዋም ‘እሺ ጠጣ፤ ለግመሎችህም እቀዳላቸዋለሁ’ የምትለኝ ብትሆን፥ ለጌታዬ ልጅ ሚስት እንድትሆን አንተ የመረጥካት እርስዋ ትሁን። 45የኅሊና ጸሎቴን ገና ሳልጨርስ ርብቃ እንስራ ተሸክማ ብቅ አለች፤ ወደ ጒድጓዱም ሄዳ ውሃ ቀዳች፤ እኔም ‘እባክሽ ጥቂት ውሃ አጠጪኝ’ አልኳት። 46እርስዋም እንስራዋን በፍጥነት ከትከሻዋ አወረደችና ዘንበል አድርጋ ‘እሺ ጠጣ፤ ግመሎችህንም አጠጣልሃለሁ’ አለችኝ፤ ስለዚህ እኔም ጠጣሁ፤ ግመሎቼንም አጠጣችልኝ። 47እኔም ‘የማን ልጅ ነሽ?’ ብዬ ጠየቅኋት። እርስዋም ‘የባቱኤል ልጅ ነኝ፤ የባቱኤል አባት ናኮር እናቱም ሚልካ ይባላሉ’ አለችኝ። ከዚህ በኋላ ጒትቻ በጆሮዋ ላይ፥ አንባሮቹንም በእጆችዋ ላይ አደረግሁላት፤ 48ከዚህ በኋላ ለጌታዬ ልጅ ሚስት የምትሆነዋን ሴት ወዳገኘሁበት ወደ ጌታዬ ወንድም ቤት በቀና መንገድ ለመራኝ ለእግዚአብሔር በጒልበቴ ተንበርክኬ ሰገድሁ፤ የጌታዬን የአብርሃምን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገንኩ፤ 49እንግዲህ የጌታዬን ዐደራ በእውነት ተቀብላችሁ እርሱን ደስ ለማሰኘት የምትፈቅዱ እንደ ሆነ ንገሩኝ፤ የማትፈቅዱም እንደ ሆነ ቊርጡን ንገሩኝ፤ እኔም እግዚአብሔር ወደሚመራኝ እሄዳለሁ።”
50ላባና ባቱኤልም “ይህ ነገር ከእግዚአብሔር የመጣ ስለ ሆነ፥ መከልከል አንችልም፤ 51ርብቃ ይህችውልህ፤ እነሆ፥ ይዘሃት ሂድ፤ እግዚአብሔር ራሱ እንደ ተናገረው ለጌታህ ልጅ ሚስት ትሁን” አሉት። 52የአብርሃም አገልጋይ ይህን በሰማ ጊዜ በጒልበቱ ተንበርክኮ ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ 53ከወርቅና ከብር የተሠሩ ጌጣጌጦችን፥ እንዲሁም ልብስ አውጥቶ ለርብቃ ሰጣት፤ ለወንድምዋና ለእናትዋም በጣም ውድ የሆኑ ስጦታዎችን አውጥቶ ሰጣቸው።
54ከዚህ በኋላ የአብርሃም አገልጋይና አብረውት የነበሩ ሰዎች በልተው ጠጥተው እዚያው ዐደሩ፤ ጠዋት በተነሡ ጊዜ የአብርሃም አገልጋይ “እንግዲህ ወደ ጌታዬ እንድመለስ ፍቀዱልኝ” አለ።
55ነገር ግን የርብቃ ወንድምና እናትዋ “ልጅትዋ ዐሥር ቀን ያኽል ከእኛ ጋር ትቈይ፤ ከዚያ በኋላ ከአንተ ጋር ልትሄድ ትችላለች” አሉት።
56እርሱ ግን “እባካችሁ አታቈዩኝ፤ እግዚአብሔር የመጣሁበትን ጉዳይ ስላቃናልኝ ቶሎ ብዬ ወደ ጌታዬ ልመለስ” አላቸው።
57እነርሱም “እስቲ ልጅቷን እንጥራና እርስዋ የምትለውን እንስማ” አሉ። 58ስለዚህ ርብቃን ጠሩና “ከዚህ ሰው ጋር መሄድ ትፈልጊያለሽን?” ብለው ጠየቅዋት።
እርስዋም “አዎ እሄዳለሁ” አለች።
59ስለዚህ ርብቃ ሞግዚትዋን አስከትላ፥ ከአብርሃም አገልጋይና ከእርሱ ሰዎች ጋር እንድትሄድ ፈቀዱላት። 60“አንቺ እኅታችን የብዙ ሺህ ሕዝብ እናት ሁኚ፤ ዘሮችሽም የጠላቶቻቸውን ከተሞች ይውረሱ!” ብለው ርብቃን መረቁአት። 61ከዚህ በኋላ ርብቃ ከደንገጡሮችዋ ጋር ለመሄድ ተነሣች፤ በግመሎቹ ላይ ተቀምጠው ከአብርሃም አገልጋይ ጋር ለመሄድ ተዘጋጁ። በዚህ ዐይነት የአብርሃም አገልጋይ ርብቃን ይዞ ሄደ።
62በዚህ ጊዜ ይስሐቅ “ብኤር ላሐይ ሮኢ ወይም የሚያየኝ ሕያው አምላክ” የተባለው ኲሬ ወዳለበት በረሓ መጥቶ በኔጌብ ተቀምጦ ነበር። 63ከዕለታት አንድ ቀን ወደ ማታ ጊዜ እያሰላሰለ በመስክ ውስጥ ሲዘዋወር ሳለ ግመሎች ሲመጡ በሩቅ አየ። 64ርብቃ ይስሐቅን ባየች ጊዜ ከግመሏ ወረደችና፥ 65“ያ በመስክ ውስጥ ወደ እኛ የሚመጣው ሰው ማን ነው?” ስትል የአብርሃምን አገልጋይ ጠየቀችው። አገልጋዩም “እርሱ ጌታዬ ነው” አላት። ስለዚህ በፍጥነት በሻሽ ፊትዋን ሸፈነች።
66አገልጋዩም ያደረገውን ነገር ሁሉ ለይስሐቅ ነገረው። 67ከዚህ በኋላ ይስሐቅ እናቱ ሣራ ትኖርበት ወደነበረው ድንኳን ርብቃን ይዞአት ገባ፤ ሚስትም ሆነችው፤ ይስሐቅ ርብቃን ወደዳት፤ በእናቱ ሞት ምክንያት ከደረሰበትም ሐዘን በዚህ ሁኔታ ተጽናና።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in