YouVersion Logo
Search Icon

ኦሪት ዘፍጥረት 19

19
የሰዶም ኃጢአት
1በዚያኑ ምሽት ሁለቱ መላእክት ወደ ሰዶም መጡ፤ በዚያን ጊዜ ሎጥ በከተማይቱ በር ተቀምጦ ነበር፤ መላእክቱን ባያቸው ጊዜ ሊያነጋግራቸው ከተቀመጠበት ተነሥቶ ሄደ፤ ጐንበስ ብሎም እጅ ነሣቸውና፥ 2“ጌቶቼ ሆይ፥ ተቀብዬ ላስተናግዳችሁ ዝግጁ ነኝ፤ እባካችሁ ወደ ቤቴ ግቡ፤ እግራችሁንም ታጥባችሁ እዚሁ ዕደሩ፤ ጠዋት በማለዳ ተነሥታችሁ ጒዞአችሁን ትቀጥላላችሁ” አላቸው።
እነርሱ ግን “አይሆንም፤ እኛ እዚሁ በከተማይቱ አደባባይ እናድራለን” አሉት።
3ነገር ግን ወደ ቤቱ እንዲገቡ አጥብቆ ስለ ለመናቸው፥ ከእርሱ ጋር ወደ ቤቱ ገቡ፤ ከዚህም በኋላ ሎጥ እንጀራ ጋግረው መልካም ራት እንዲያዘጋጁ ለአገልጋዮቹ ነገራቸው፤ ራትም በተዘጋጀ ጊዜ እንግዶቹ በሉ።
4እንግዶቹ ከመተኛታቸው በፊት የሰዶም ሰዎች ቤቱን ከበቡት፤ ወጣቶችና ሽማግሌዎች ሳይቀሩ የከተማይቱ ወንዶች ሁሉ እዚያ ተሰበሰቡ። 5ሎጥንም ጠርተው “ከአንተ ጋር ለማደር ወደዚህ የገቡት ሰዎች የት አሉ? ከእነርሱ ጋር ግንኙነት ለማድረግ ስለምንፈልግ ወደ እኛ አውጣቸው!” አሉት።
6ሎጥ ግን ወደ ውጪ ወጥቶ በሩን ከበስተኋላው ዘጋው፤ 7እንዲህም አላቸው “ወዳጆቼ ሆይ፥ እባካችሁ ይህን ክፉ ነገር አታድርጉ! #መሳ. 19፥22-24። 8እነሆ፥ ሁለት ያላገቡ ሴቶች ልጆች አሉኝ፤ እነርሱን ወደ እናንተ ላምጣላችሁና በእነርሱ ላይ የፈለጋችሁትን ነገር አድርጉ፤ በእነዚህ ሰዎች ግን ምንም ነገር አታድርጉ፤ እነርሱ የእኔ እንግዶች ስለ ሆኑ ልጠነቀቅላቸው ይገባኛል።”
9ሰዎቹ ግን “አንተ ስደተኛ፥ ሂድ ወዲያ! ለመሆኑ ልናደርገው የሚገባንን ነገር የምትነግረን አንተ ማን ነህ? ሂድ ወዲያ፤ አለበለዚያ በእነርሱ ላይ ልናደርግ ካሰብነው የከፋ ነገር በአንተ ላይ እናደርጋለን” አሉት። በዚህ ዐይነት ሎጥን ወዲያ ገፍትረው በሩን ለመስበር ተነሣሡ፤ 10ከቤቱ ውስጥ ያሉት ሁለቱ እንግዶች ግን እጆቻቸውን ወደ ውጪ አውጥተው ሎጥን ስበው ወደ ቤቱ ውስጥ አስገቡትና በሩን ዘጉ። 11ከዚያ በኋላ ውጪ የነበሩት ወጣቶችና ሽማግሌዎች ሁሉ በሩን ማየት እንዳይችሉ ዐይናቸውን አሳወሩአቸው። #2ነገ. 6፥18።
ሎጥ ሰዶምን ለቆ መውጣቱ
12ሁለቱም እንግዶች ሎጥን እንዲህ አሉት፤ “በዚህች ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ፥ የልጆችህ እጮኛዎችና ሌሎች ዘመዶች ቢኖሩህ ከዚህች ከተማ በፍጥነት እንዲወጡ አድርግ፤ 13ይህችን ከተማ ልናጠፋት ነው፤ የእነዚህ ሰዎች ኃጢአት እጅግ መብዛቱን እግዚአብሔር ሰምቶአል፤ ሰዶምንም እንድናጠፋ ልኮናል።”
14ከዚህ በኋላ ሎጥ ሴቶች ልጆቹን ወዳጩአቸው ሰዎች ቤት ሄደና “ቶሎ ብላችሁ ከዚህ ውጡ፤ እግዚአብሔር ይህን ስፍራ ሊደመስሰው ነው” አላቸው፤ እነርሱ ግን የሚቀልድ መስሎአቸው ቸል አሉ።
15በማግስቱ ጠዋት በማለዳ መላእክቱ ሎጥን “ፍጠን! ከተማይቱ ስትጠፋ አብራችሁ እንዳትጠፉ ሚስትህንና ሁለቱን ሴቶች ልጆችህን ይዘህ ከዚህ ውጣ” እያሉ አጣደፉት። 16ሎጥ ግን አመነታ፤ ሆኖም እግዚአብሔር ለእርሱና ለቤተሰቡ ስለ ራራ መላእክቱ ሎጥንና ሚስቱን፥ ሁለቱን ሴቶች ልጆቹን፥ እጆቻቸውን ይዘው ከከተማዋ እንዲያወጡአቸው አደረገ። #2ጴጥ. 2፥7። 17ካወጡአቸውም በኋላ ከመላእክቱ አንዱ “ሕይወታችሁን አድኑ! ወደ ኋላ አትመልከቱ! በሸለቆው ውስጥ አትዘግዩ፤ እንዳትሞቱ ወደ ተራራው ሽሹ!” አላቸው።
18ሎጥ ግን እንዲህ አላቸው፤ “ጌቶቼ፥ እባካችሁ ወደዚያ እንድንወጣ አታደርጉ፤ 19እኔ አገልጋያችሁ በፊታችሁ ሞገስ ስላገኘሁ ሕይወቴን ለማዳን ታላቅ ርዳታ አድርጋችሁልኛል፤ ነገር ግን ይህ ጥፋት ደርሶብኝ እሞታለሁ ብዬ ስለምሰጋ ወደዚያ ተራራ መሸሽ አልችልም። 20እኔ በፍጥነት ሸሽቼ ላመልጥበት የምችል እነሆ አንዲት ትንሽ ከተማ በቅርብ አለች፤ ስለዚህ ሸሽቼ ወደ እርሷ እንድሄድ ፍቀዱልኝ፤ እንደምታዩአት ትንሽ ከተማ ናት፤ ወደ እርስዋ ብሄድ ሕይወቴ ከጥፋት ይድናል።”
21መልአኩም “እሺ አንተ ባልከው እስማማለሁ፤ ይህችን አንተ የምትላትን ከተማ አላጠፋትም፤ 22ወደዚያች ከተማ እስከምትደርስ ምንም ማድረግ ስለማልችል ፈጥነህ ወደ እርስዋ ሽሽ!” አለው። ሎጥ ያቺን ከተማ ትንሽ ብሎአት ስለ ነበር ጾዓር ተባለች። #19፥22 ጾዓር፦ በዕብራይስጥ “ትንሽ” ማለት ነው።
የሰዶምና የገሞራ መደምሰስ
23ሎጥ ወደ ጾዓር ሲደርስ ገና ፀሐይ መውጣትዋ ነበር፤ 24እግዚአብሔር በሰዶምና በገሞራ ከተሞች ላይ እሳትና ዲን ከራሱ (ከእግዚአብሔር ዘንድ) ከሰማይ አዘነበ። 25በዚህ ዐይነት እነዚያን ከተሞችና ሸለቆዎች፥ እዚያ የሚኖሩትን ሰዎች ሁሉ፥ በምድሩም ላይ የበቀለውን ነገር ሁሉ ደመሰሰ። #ማቴ. 10፥15፤ 11፥23-24፤ ሉቃ. 10፥12፤ 17፥29፤ 2ጴጥ. 2፥6፤ ይሁዳ 7። 26የሎጥ ሚስትም ወደ ኋላዋ ስለ ተመለከተች የጨው ዐምድ ሆና ቀረች። #ሉቃ. 17፥32።
27አብርሃም በማግስቱ ማለዳ ተነሥቶ ከዚህ ቀደም ከእግዚአብሔር ጋር ወደተገናኘበት ቦታ ሄደ። 28ወደ ሰዶምና ወደ ገሞራ ወደ ሸለቆውም ቊልቊል በተመለከተ ጊዜ ከታላቅ ምድጃ እንደሚወጣ ጢስ ከባድ የእሳት ጢስ ከዚያ ሲወጣ አየ። 29ሎጥ ይኖርባቸው የነበሩትን፥ በሸለቆ የሚገኙትን ከተሞች፥ እግዚአብሔር ባጠፋ ጊዜ አብርሃምን አስታወሰ፤ ስለዚህም ሎጥን ከጥፋት ወደሚድንበት ቦታ መራው።
የሞአባውያንና የዐሞናውያን አመጣጥ
30ሎጥ በጾዓር መቀመጥ ስለ ፈራ እርሱና ሁለቱ ሴቶች ልጆቹ ወደ ተራራዎቹ ወጥተው መኖሪያቸውን በዋሻ ውስጥ አደረጉ። 31አንድ ቀን ታላቂቱ ልጁ እኅትዋን እንዲህ አለቻት፦ “አባታችን ማርጀቱ ነው፤ ልጆች እንድንወልድ እኛን የሚያገቡ ወንዶች በዙሪያችን የሉም፤ 32ከእርሱ ጋር ተኝተን ከእርሱ ልጆች እንድናገኝ አባታችንን የወይን ጠጅ አጠጥተን እናስክረው።” 33በዚያን ምሽት አባታቸውን የወይን ጠጅ አጠጥተው አሰከሩት፤ ታላቂቱ ልጁም ከእርሱ ጋር ግንኙነት አደረገች። ሎጥ ግን በጣም ሰክሮ ስለ ነበር ስትተኛም ሆነ ስትነሣ አላወቀም።
34በማግስቱ ታላቂቱ ልጅ እኅቷን “ትናንት ማታ እኔ ከእርሱ ጋር ተኝቼአለሁ፤ ዛሬም እንደገና የወይን ጠጅ አጠጥተን እናስክረውና አንቺም አብረሽው ተኚ፤ በዚህ ዐይነት ሁለታችንም ከአባታችን ልጆች ወልደን ዘራችን እንዳይጠፋ እናድርግ” አለቻት። 35ስለዚህ በዚያን ምሽት አባታቸውን እንደገና የወይን ጠጅ አጠጥተው አሰከሩት፤ ታናሽቱ ልጁም ከእርሱ ጋር ግንኙነት አደረገች፤ አሁንም እጅግ ሰክሮ ስለ ነበር ስትተኛም ሆነ ስትነሣ አላወቀም። 36በዚህ ሁኔታ ሁለቱም የሎጥ ሴቶች ልጆች ከአባታቸው ፀነሱ። 37ታላቂቱ ወንድ ልጅ ወለደችና ስሙን ሞአብ አለችው፤ እርሱ ዛሬ ሞአባውያን ተብለው ለሚጠሩት ሕዝቦች ቅድመ አያት ነው። #19፥37 ሞአብ፦ በዕብራይስጥ “ከአባቴ የተወለደ” ማለት ነው። 38ታናሽቱም ወንድ ልጅ ወለደችና ስሙን ቤንዐሚ አለችው፤ እርሱ ዛሬ ዐሞናውያን ተብለው ለሚጠሩት ሕዝቦች ቅድመ አያት ነው። #19፥38 ቤንዐሚ፦ በዕብራይስጥ “የወገኔ ልጅ” ማለት ነው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in