ትንቢተ ሕዝቅኤል 40
40
ወደፊት ስለሚሠራው ቤተ መቅደስ የተገለጠ ራእይ
1በተሰደድን በሃያ አምስተኛው ዓመት፥ ኢየሩሳሌምም በጠላት እጅ በወደቀች በዐሥራ አራተኛው ዓመት፥ በመጀመሪያው ወር፥ ከወሩም በዐሥረኛው ቀን፥ በዚያው ዕለት የእግዚአብሔር ኀይል ወደ እኔ መጥቶ ነበር፤ እርሱም ብድግ አድርጎ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰደኝ፤ 2በእግዚአብሔርም ራእይ ወስዶ በእስራኤል ምድር በአንድ ከፍተኛ ተራራ ላይ አኖረኝ፤ እዚያም አንድ ብዙ ቤቶች የተሠሩበትን ከተማ የሚመስል ከተራራው በስተደቡብ በኩል አየሁ። #ራዕ. 21፥10። 3ወደዚያ ሲወስደኝም እንደ ነሐስ የሚያበራ መልክ ያለውን አንድ ሰው አየሁ፤ እርሱም ከበፍታ የተሠራ ገመድና መለኪያ ዘንግ ይዞ በቅጽሩ በር አጠገብ ቆሞ ነበር። #ራዕ. 11፥1፤ 21፥15።
4ሰውየውም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! እዚህ ድረስ እንድትመጣ የተደረገበት ምክንያት እኔ የማሳይህን ሁሉ እንድትረዳ ስለ ሆነ ልብ ብለህ ተመልከት፤ በጥንቃቄም ስማ፤ የምታየውንም ሁሉ ለእስራኤል ሕዝብ ንገራቸው።”
የምሥራቁ ቅጽር በር
5በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ቅጥር ነበረ፤ በሰውዬው እጅ ያለው መለኪያ ዘንግ በእርሱ ረጃጅም ክንዶች ስድስት ይሆናል፤ የቅጽሩ ስፋት ሲለካ አንድ ዘንግ፥ ከፍታው ሲለካ አንድ ዘንግ ሆነ። የእርሱ ክንድ ግን በሌሎች ሰዎች ክንድ ሲለካ አንድ ክንድ ከጋት ይሆናል። #1ነገ. 6፥1-38፤ 2ዜ.መ. 3፥1-9። 6ከዚያም በኋላ በስተምሥራቅ በኩል ወዳለው የቅጽር በር አልፎ ሄደ፤ ደረጃውንም ወጥቶ ከጫፉ የመድረኩን ወለል ሲለካ አንድ ዘንግ ሆነ፤ 7አንድ ዘንግ ቁመትና አንድ ዘንግ ወርድ ያላቸው የዘብ ማረፊያ ክፍሎች ነበሩት፤ በማረፊያ ክፍሎቹ መካከል ያለው ርቀት አምስት ክንድ ነው፤ የቅጽሩ በር መግቢያ መድረክ ወደ ውስጥ እስከሚያስገባው መተላለፊያ ጫፍ ድረስ አንድ ዘንግ ነው። 8-9ሰውየውም የመግቢያውን መተላለፊያ ሲመትር ስምንት ክንድ ሆኖ አገኘው፤ የግንቦቹ ስፋት ሁለት ክንድ ሆነ፤ የበሩ መተላለፊያ ወደ ቤተ መቅደሱ የሚያመራ ነበር። 10እነዚህም የዘብ ማረፊያ ክፍሎች ከመተላለፊያው በስተጐን እያንዳንዳቸው ተመሳሳይ ስፋት ነበራቸው፤ በእነርሱ መካከል ያሉትም ግንቦች ሁሉ ተመሳሳይ ውፍረት ነበራቸው።
11የበሩን መግቢያ ሲለካ ወርዱ ዐሥር ክንድ ርዝመቱ ደግሞ ዐሥራ ሦስት ክንድ ሆኖ አገኘው። 12በእያንዳንዱ ማረፊያ ክፍል ፊት ለፊት ከፍታው አንድ ክንድ ውፍረቱም አንድ ክንድ የሆነ ዝቅተኛ ግንብ ነበር፤ ክፍሎቹም የአራት ማእዘን ቅርጽ ያላቸው ሆነው እያንዳንዱ ማእዘን ስድስት ክንድ ርዝመት ነበረው። 13ከዚያ በኋላ መግቢያውን ከአንዱ ማረፊያ ክፍል በስተጀርባ እስከ ሁለተኛው ማረፊያ ክፍል በስተጀርባ፥ ከግድግዳ እስከ ግድግዳ ድረስ ለክቶ ኻያ አምስት ክንድ ሆኖ ተገኘ።
14በስተመጨረሻ ያለው ክፍል ወደ አደባባዩ ያመራ ነበር፤ እርሱም ሲለካ ኻያ ክንድ ሆኖ ተገኘ። 15ከመግቢያው ጀምሮ እስከ መውጫው ድረስ ያለው የመተላለፊያው ርዝመት ኀምሳ ክንድ ነበር። 16ማረፊያ ክፍሎቹና ዐምዶቻቸው በውስጥ በኩል ዙሪያውን መስኮቶችና ዐይነ ርግቦች ነበሩአቸው፤ በስተመጨረሻ ያሉትም ክፍሎች በውስጥ በኩል ዙሪያውን መስኮቶች ነበሩአቸው፤ በግድግዳ ዐምዶቻቸውም ላይ የዘንባባ ዛፎች ቅርጽ ነበሩባቸው።
የውጪው አደባባይ
17ከዚያ በኋላ ሰውዬው ወደ ውጪው አደባባይ አመጣኝ፤ በአደባባዩ ዙሪያ የድንጋይ ንጣፍና ክፍሎች ነበሩ ከንጣፉም ፊት ለፊት ሠላሳ ክፍሎች ነበሩ። 18የድንጋዩም ንጣፍ እስከ አደባባዩ ዙሪያ ይዘልቃል፤ የውጪውም አደባባይ ከውስጠኛው አደባባይ ዝቅ ያለ ነበር።
19ወደ ውስጠኛው አደባባይ የሚያደርስ ከፍ ብሎ የተሠራ የቅጽር በር ነበር፤ ያም ሰው በሁለቱ የቅጽር በሮች ከመካከል ያለውን ርቀት ለካ፤ እርሱም መቶ ክንድ ሆነ።
የሰሜኑ ቅጽር በር
20ያ ሰው በሰሜን በኩል ወደ ውጪው አደባባይ ትይዩ ያለውን የቅጽር በር ለካ፤ 21ግራና ቀኝ ያሉት ሦስቱ የዘብ ማረፊያ ክፍሎችና የግድግዳ ዐምዶች እንዲሁም በስተመጨረሻ ያለው ክፍል በምሥራቁ የቅጽር በር በኩል ከታዩት ጋር ተመሳሳይ የሆነ ልክ ነበራቸው፤ የቅጽር በሩ ጠቅላላ ርዝመት ኀምሳ ክንድ፥ ወርዱ ኻያ አምስት ክንድ ነበር። 22በስተ መጨረሻ ያለው ክፍል መስኮቶቹና የተሳሉት የዘንባባ ዛፍ ቅርጾችም ከዚህ በፊት በምሥራቁ የቅጽር በር ከታዩት ጋር ተመሳሳይ መጠን ነበራቸው፤ ወደ እርሱም የሚያመሩ ሰባት ደረጃዎች ነበሩ፤ በውስጥ መተላለፊያ በስተመጨረሻ ያለው ክፍልም በአደባባዩ ትይዩ ይገኝ ነበር። 23በምሥራቁ በር እንዳለው ዐይነት በሰሜኑ በር ትይዩ ወደ ውስጠኛው አደባባይ የሚያስገባ በር ነበር፤ ሰውዬው ከአንዱ በር እስከ ሌላው በር ሲለካ አንድ መቶ ክንድ ሆነ።
የደቡቡ ቅጽር በር
24ከዚያም በኋላ ወደ ደቡብ ወሰደኝ፤ እዚያም በደቡብ በኩል የሚያስወጣ አንድ በር ነበር፤ ሰውየውም የበሩን የግድግዳ ዐምዶችና በስተመጨረሻ ያለውን ክፍል ለካ፤ ስፋታቸውም ከሌሎቹ ጋር እኩል ነበር። 25ርዝመቱ ኀምሳ ክንድ ወርዱ ኻያ አምስት ክንድ የሆነው በር ከነመተላለፊያው እንደ ሌሎቹ ቦታዎች መስኮቶች አሉት። 26ወደዚያም የሚያደርሱ ሰባት ደረጃዎች አሉ፤ በውስጥ መተላለፊያ በስተመጨረሻ ያለው ክፍል ቀጥሎ ይገኛል፤ በሁለቱ በኩል ባሉት የግድግዳ ዐምዶች ላይ ደግሞ የዘንባባ ቅርጾች ተስለውባቸው ነበር። 27ወደ ውስጠኛው አደባባይ የሚያደርስ ሌላም የቅጽር በር ደግሞ ነበር፤ ያም ሰው ውጪኛውን አደባባይ አቋርጦ አደባባይ እስከዚህ እስከ ሁለተኛው ቅጽር በር ያለውን ስፋት ለካ፤ እርሱም መቶ ክንድ ነበር።
የውስጠኛው አደባባይ፥ የደቡብ ቅጽር በር
28ያ ሰው በደቡቡ ቅጽር በር በኩል ወደ ውስጠኛው አደባባይ ወሰደኝ፤ እርሱም የቅጽር በሩን ሲለካ ስፋቱ በውጪ ካሉት የቅጥር በሮች ጋር እኩል ሆኖ ተገኘ። 29የዘብ የማረፊያ ክፍሎቹ የግድግዳ ዐምዶቹና በስተመጨረሻ ያለው ክፍል ስፋት እንደ ሌሎቹ ነበር፤ የበሩና የመተላለፊያው ርዝመት ኀምሳ ክንድ ወርዱም ኻያ አምስት ክንድ ነበር፤ በመተላለፊያውም ዙሪያ ሁሉ መስኮቶች ነበሩ። 30ዙሪያውም ኻያ አምስት ክንድ ርዝመትና አምስት ክንድ ወርድ ያላቸው መተላለፊያዎች ነበሩ። 31መግቢያው ክፍል ከውጪው አደባባይ ጋር ትይዩ ነበር፤ በግድግዳ ዐምዶቹም ላይ የዘንባባ ዛፍ ቅርጾች ነበሩ። መወጣጫውም ስምንት ደረጃዎች ነበሩት።
የውስጠኛው አደባባይ፥ የምሥራቁ ቅጽር በር
32ያም ሰው በምሥራቁ ቅጽር በር በኩል ወደ ውስጠኛው አደባባይ ወሰደኝ፤ እርሱም የቅጽሩን በር ሲለካው መጠኑ ልክ እንደ ሌሎቹ ሆኖ አገኘው። 33የዘብ ማረፊያ ክፍሎቹ፥ የግድግዳ ዐምዶቹና የመግቢያው ክፍል ስፋት እንደ ሌሎቹ ነበር፤ የበሩና የመተላለፊያው ርዝመት ኀምሳ ክንድ ወርዱም ኻያ አምስት ክንድ ነበር፤ በመተላለፊያውም ዙሪያ ሁሉ መስኮቶች ነበሩ። 34መግቢያው ክፍል ከውጪው አደባባይ ጋር ትይዩ ነበር፤ በግድግዳ ዐምዶቹም ላይ በሁለቱም በኩል የዘንባባ ዛፍ ቅርጾች ነበሩ፥ መወጣጫውም ስምንት ደረጃዎች ነበሩት።
የውስጠኛው አደባባይ፥ የሰሜኑ ቅጽር በር
35ያ ሰው ወደ ሰሜኑ ቅጽር በር ወሰደኝ፤ በለካውም ጊዜ ስፋቱ በሌሎቹ ልክ ሆኖ ተገኘ። 36የዘብ ማረፊያ ክፍሎቹ፥ የግድግዳ የዐምዶቹና የመግቢያው ክፍል ስፋት እንደ ሌሎቹ ነበር፤ የበሩ የማረፊያ ክፍል ርዝመት ኀምሳ ክንድ፥ ወርዱም ኻያ አምስት ክንድ ነበር፥ በመተላለፊያውም ዙሪያ ሁሉ መስኮቶች ነበሩ። 37የመግቢያው ክፍል ከውጪው አደባባይ ጋር ትይዩ ነበር፤ በግድግዳ ዐምዶቹም ላይ በሁለቱም በኩል የዘንባባ ዛፍ ቅርጾች ነበሩ፤ መወጣጫውም ስምንት ደረጃዎች ነበሩት።
በሰሜን ቅጽር በር አጠገብ ያሉት ሕንጻዎች
38በውጪው አደባባይ በስተ ሰሜን በኩል ከውስጠኛው የቅጽር በር ጋር የተያያዘ ሌላም ተጨማሪ ክፍል ነበር፤ እርሱም ከአደባባዩ ፊት ለፊት ወደሚገኘው ወደ መግቢያው ክፍል የሚያስገባ ሌላ በር ነበረው፤ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርቡ የእንስሶች ሥጋ የሚታጠበውም በዚያ ነበር። 39በመግቢያው ክፍል በኩል በግራና በቀኝ ትይዩ ሁለት ሁለት ጠረጴዛዎች ነበሩ፤ በእነዚያም ጠረጴዛዎች ላይ ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ ለኃጢአት መሥዋዕትና ለበደል መሥዋዕት የሚቀርቡ እንስሶች ይታረድባቸው ነበር። 40ከመግቢያው ክፍል በስተውጪ በሰሜን ቅጽር መግቢያ በር አጠገብ ሁለቱ በአንድ በኩል፥ ሁለቱ በሌላ በኩል በትይዩ የተቀመጡ አራት ተመሳሳይ ጠረጴዛዎች ነበሩ። 41ስለዚህም ለመሥዋዕት የሚቀርቡ እንስሶች የሚታረዱባቸው በአጠቃላይ ስምንት ጠረጴዛዎች ነበሩ፤ የእነርሱም አቀማመጥ አራቱ በውስጥ በኩል፥ አራቱ ደግሞ በውጭ በኩል ነበሩ። 42እንደዚሁም ለሚቃጠለው መሥዋዕት ከተጠረበ ድንጋይ የተሠሩ አራት ጠረጴዛዎች ነበሩ፤ ርዝመታቸው አንድ ክንድ ተኩል ወርዳቸው አንድ ክንድ ተኩል፥ ከፍታቸው አንድ ክንድ ነበር፤ እነርሱም ለሚቃጠለውና ለሌሎች መሥዋዕት የማረጃ ዕቃዎች ማስቀመጫነት የሚያገለግሉ ነበሩ። 43ለጥቃቅን ዕቃዎች ማስቀመጫነት የሚያገለግል ስፋቱ አንድ ጋት የሆነ ክፈፍ በውስጥ በኩል በግድግዳዎቹ ላይ ዙሪያውን ተሠርቶ ነበር፤ በጠረጴዛዎቹም ላይ የመሥዋዕቱ ሥጋ ይቀመጥ ነበር።
44ከዚህም በኋላ ያ ሰው እኔን ወደ ውስጠኛው አደባባይ አስገባኝ፤ እዚያም ሁለት ክፍሎች ነበሩ፤ ከእነርሱም አንዱ በሰሜን የቅጽር በር አጠገብ ወደ ደቡብ የሚያመለክት ሲሆን፥ ሁለተኛው በደቡብ የቅጽር በር አጠገብ ወደ ሰሜን የሚያመለክት ነበር። 45ያም ሰው እንዲህ አለኝ፦ “ወደ ደቡብ የሚያመለክተው ክፍል በቤተ መቅደሱ ለማገልገል ኀላፊነት ለተሰጣቸው ካህናት ማረፊያ ነው። 46ወደ ሰሜን የሚያመለክተውም ክፍል በመሠዊያው ለማገልገል ኃላፊነት ለተሰጣቸው ካህናት ማረፊያ ነው፤ እነዚህ ሁሉ ካህናት ከሳዶቅ ዘር የተወለዱ ሌዋውያን ሲሆኑ፥ በፊቱ ቆመው እግዚአብሔርን ለማገልገል የተፈቀደላቸው እነርሱ ብቻ ናቸው።”
የውስጠኛው አደባባይና የቤተ መቅደሱ ሕንጻ
47ያ ሰው የውስጠኛውን አደባባይ ሲለካ ርዝመቱ መቶ ክንድ ወርዱም መቶ ክንድ ሆነ፤ በቤተ መቅደሱ በፊት ለፊቱም አንድ መሠዊያ ነበር። 48ከዚያ በኋላ ወደ ቤተ መቅደሱ መግቢያ ክፍል አመጣኝ፤ የመግቢያው ክፍል የግድግዳውም ዐምዶች ሲለካ የሁለቱም ትይዩ አምስት ክንድ ሆኖ አገኘው፤ የመግቢያውም ወርድ ዐሥራ አራት ክንድ ነበር፤ የመግቢያውም ግድግዳ ውፍረት በሁለቱም በኩል ሦስት ሦስት ክንድ ነበር። 49የመግቢያው ክፍል ርዝመት ኻያ ክንድ፥ ወርዱ ዐሥራ ሁለት ክንድ ነበር፤ ዐሥር የመወጣጫ ደረጃዎቹም ወደዚያ ያደርሱ ነበር፤ በሁለቱ መወጣጫ ደረጃዎች ጐን ዐምዶች ነበሩ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 40: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997