ኦሪት ዘጸአት 1
1
እስራኤላውያን በግብጽ ሲኖሩ የደረሰባቸው ግፍና በደል
1እያንዳንዱ ከቤተሰቡ ጋር ሆኖ ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብጽ የገቡት፥ እስራኤል ተብሎ የተጠራው የያዕቆብ ልጆች ስሞች እነዚህ ናቸው፦ 2ሮቤል፥ ስምዖን፥ ሌዊ፥ ይሁዳ፥ 3ይሳኮር፥ ዛብሎን፥ ብንያም፥ 4ዳን፥ ንፍታሌም፥ ጋድና አሴር። #ዘፍ. 46፥8-27። 5በቀጥታ ከያዕቆብ የተገኙት የተወላጆቹ ጠቅላላ ብዛት ሰባ ሲሆን፥ ዮሴፍ ግን ቀደም ብሎ በግብጽ ይኖር ነበር። #1፥5 በዕብራይስጥ ቅጂ “ሰባ” ይላል (ዘፍ. 46፥26-27 ተመልከት) በሙት ባሕር በተገኘው ቅጂና በሰባ ሊቃናት ትርጒም “ሰባ አምስት” ይላል (የሐዋ.ሥ 7፥14 ተመልከት) 6በዘመናት ውስጥ ዮሴፍ፥ ወንድሞቹና የዚያ ትውልድ አባቶች ሁሉ ሞቱ። 7ሆኖም የእነርሱ ዘሮች የሆኑ እስራኤላውያን ተዋልደው ቊጥራቸው ከመብዛቱ የተነሣ የግብጽን ምድር ሞሉአት፤ እጅግም ብርቱዎች ሆኑ። #ሐ.ሥ. 7፥17።
8ከዚህ ሁሉ በኋላ ዮሴፍ ያደረገውን ነገር የማያውቅ አዲስ ንጉሥ በግብጽ ተነሣ። #ሐ.ሥ. 7፥18። 9እርሱም ለሕዝቡ እንዲህ አለ፦ “እነሆ፥ እነዚህ እስራኤላውያን ቊጥራቸው በዝቶአል፤ የኀይላቸውም ብርታት አስጊ ሆኖብናል፤ 10ከዚህም የተነሣ ከጠላቶቻችን ጋር ተባብረው ከወጉን በኋላ ከአገሪቱ አምልጠው መሄድ ይችላሉ፤ ስለዚህ ቊጥራቸው እየበዛ እንዳይሄድ ኑ፤ አንድ ዘዴ እንፈልግ።” #ሐ.ሥ. 7፥19። 11ከዚህ በኋላ በብርቱ ሥራ ይጨቊኑአቸው ዘንድ ጨካኞች የሆኑ አሠሪዎችን ሾሙባቸው፤ በዚህም ሁኔታ ዕቃ ማከማቻ የሆኑትን ፊቶምና ራምሴ የተባሉትን ከተሞች ለፈርዖን ሠሩ። 12ነገር ግን እስራኤላውያን በተጨቈኑ መጠን ቊጥራቸው ይበልጥ እየበዛና በምድሪቱም ላይ እየተስፋፉ ሄዱ፤ ከዚህም የተነሣ ግብጻውያን እስራኤላውያንን ፈሩአቸው። 13ርኅራኄ በጐደለውም ጭካኔ በባርነት አሠሩአቸው። 14ጭቃ በማቡካት፥ ጡብ በማዘጋጀትና በእርሻ ውስጥ በጭካኔ ከባድ ሥራ በማሠራት ሕይወታቸው መራራ እንዲሆን አደረጉ።
15ከዚህ በኋላ የግብጽ ንጉሥ የዕብራውያን ሴቶችን የሚረዱ ጺጳራና ፉሐ ተብለው የሚጠሩትን ሁለት አዋላጆች እንዲህ አላቸው፤ 16“የዕብራውያንን ሴቶች በምታዋልዱበት ጊዜ የሚወለደው ሕፃን ወንድ ከሆነ ወዲያውኑ ግደሉት፤ ሴት ከሆነች ግን በሕይወት እንድትኖር ተዉአት”። 17አዋላጆቹ ግን እግዚአብሔርን በመፍራት የግብጽ ንጉሥ እንዳዘዛቸው አላደረጉም፤ ወንዶችንም ልጆች በሕይወት እንዲኖሩ ተዉአቸው። 18ከዚህ በኋላ የግብጽ ንጉሥ አዋላጆቹን አስጠርቶ “ወንዶች ልጆች በሕይወት እንዲኖሩ ያደረጋችኹበት ምክንያት ምንድን ነው?” ሲል ጠየቃቸው።
19እነርሱም “የዕብራውያን ሴቶች እንደ ግብጻውያን ሴቶች አይደሉም፤ እነርሱ ብርቱዎች ስለ ሆኑ አዋላጆች ወደ እነርሱ ገና ከመምጣታቸው በፊት ያለምንም ችግር ይወልዳሉ” ሲሉ መለሱለት። 20-21አዋላጆቹ እግዚአብሔርን ስለ ፈሩ እግዚአብሔርም ለእነርሱ መልካም ነገር አደረገላቸው፤ ለያንዳንዳቸውም ቤተሰብ ሰጣቸው፤ በዚህም ዐይነት የእስራኤል ሕዝብ በቊጥር እየበዙና ብርቱዎችም እየሆኑ ሄዱ። 22ከዚህም በኋላ ንጉሡ “ከዕብራውያን የሚወለደውን ወንድ ልጅ ሁሉ እያነሣችሁ ዓባይ ወንዝ ውስጥ ጣሉ፤ ሴቶች ልጆች ግን በሕይወት ይኑሩ” ሲል ለሕዝቡ ጥብቅ ትእዛዝ አስተላለፈ። #ሐ.ሥ. 7፥19።
Currently Selected:
ኦሪት ዘጸአት 1: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997