YouVersion Logo
Search Icon

ኦሪት ዘዳግም 9

9
በእግዚአብሔር ላይ ማመፅ የሚያመጣው ችግር
1“የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! አድምጥ፤ ከአንተ የሚበልጡትንና በኀይልም ብርቱ የሆኑትን የአሕዛብ ምድርና ቅጽሮቻቸው እስከ ሰማይ የደረሱ ታላላቅ ከተሞቻቸውን ለመውረስ ትገባ ዘንድ ዛሬ ዮርዳኖስን ትሻገራለህ። 2በዚያ የሚኖሩ ሕዝቦች ግዙፋን የሆኑ ቁመተ ረጃጅሞችና ብርቱዎች ናቸው፤ እነርሱም ‘ማንም ሊቋቋማቸው የማይችል የዔናቅ ዘሮች ናቸው’ ሲባል ሰምተሃል፤ 3ነገር ግን እንደሚባላ እሳት የሆነ እግዚአብሔር አምላክህ በፊትህ የሚሄድ መሆኑን ዛሬ ታያለህ፤ አንተ ወደ ፊት በሄድህ መጠን እርሱ ድል ይነሣቸዋል፤ ስለዚህም እርሱ በሰጠው ተስፋ መሠረት እነርሱን ነቃቅለህ በማባረር በፍጥነት ታጠፋቸዋለህ።
4“እግዚአብሔር አምላካችሁ እነርሱን ከፊታችሁ ካባረረላችሁ በኋላ ‘እግዚአብሔር ወደዚህች ምድር ያመጣን ስለ መልካም ሥራችን ነው’ ብላችሁ አታስቡ፤ እግዚአብሔር እነዚህን ሕዝብ ነቃቅሎ የሚያባርርልህ እነርሱ ክፉዎች ስለ ሆኑ ብቻ ነው። 5እግዚአብሔር የእነርሱን ምድር እንድትወርስ የፈቀደልህ አንተ ደግ በመሆንህና ትክክለኛውን ነገር በማድረግህ አይደለም፤ እርሱ እነርሱን ነቃቅሎ የሚያባርርበት ምክንያት እነርሱ ክፉዎች ስለ ሆኑና እንዲሁም ለቀድሞ አባቶችህ፥ ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ለመጠበቅ ሲል ነው። 6እንግዲህ አንተ ልብህ የደነደነ እልኸኛ ስለ ሆንክ እግዚአብሔር ይህችን ለም ምድር የሚሰጥህ አንተ እርስዋን ለመውረስ የተገባህ አለመሆንህን ዕወቅ።
7“እግዚአብሔር አምላክህን በበረሓ እንዴት እንዳስቈጣኸው ከቶ አትርሳ፤ የግብጽን ምድር ለቀህ ከወጣህበት ቀን ጀምሮ እዚህ እስከ መጣህበት እስከ አሁን ድረስ በእርሱ ላይ ዐምፀሃል። 8በሲና በረሓ እንኳ እናንተን ለማጥፋት እስኪነሣሣ ድረስ እግዚአብሔርን በብርቱ አስቈጥታችሁታል። 9እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር የገባው ቃል ኪዳን የተጻፈባቸውን የድንጋይ ጽላቶች ለመቀበል እኔ ወደ ተራራው ወጥቼ ነበር፤ በዚያም ምንም ነገር ሳልበላና ሳልጠጣ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቈየሁ። #ዘፀ. 24፥18። 10ከዚያም በኋላ እናንተ በተራራው ግርጌ በተሰበሰባችሁ ጊዜ እግዚአብሔር በእሳት ውስጥ ሆኖ ሲናገር የሰማችሁትን ቃል በእጁ የጻፈባቸውን ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ሰጠኝ። 11ከአርባ ቀንና ከአርባ ሌሊት በኋላ እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን የጻፈባቸውን ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ሰጠኝ።
12“ከዚያም በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ ‘ፈጥነህ ከተራራው ራስ ላይ ውረድ፤ ከግብጽ ምድር መርተህ ያወጣኸው ሕዝብህ፥ ክፉ ነገር በማድረግ ረክሶአል፤ እኔ ከሰጠኋቸው ትእዛዝ ሁሉ ወዲያውኑ ርቀው፥ የሚያመልኩትን ጣዖት ለራሳቸው ሠርተዋል።’
13“ቀጥሎም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ ‘እነሆ፥ ይህ ሕዝብ ልቡ የደነደነ፥ እልኸኛ መሆኑን ዐውቃለሁ፤ 14እንግዲህ ተወኝ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ማንም ሊያስታውሳቸው በማይችል ሁኔታ ልደምስሳቸው፤ ከዚያም በኋላ አንተን ከእነርሱ ይበልጥ ኀይልና ብዛት ላለው ሕዝብ አባት አደርግሃለሁ።’
15“ስለዚህም ቃል ኪዳኑ የተጻፈባቸውን ሁለቱን የድንጋይ ጽላቶች በሁለት እጆቼ እንደ ያዝኩ ከተራራው ተመልሼ ወረድኩ፤ በዚያን ጊዜ የእሳት ነበልባል ከተራራው ይታይ ነበር፤ 16እናንተም እግዚአብሔር አምላካችሁ ከሰጣችሁ ትእዛዝ ወዲያው ፈቀቅ ብላችሁ፥ ወርቅ አቅልጣችሁ በጥጃ ምስል ጣዖት በመሥራት በእግዚአብሔር ላይ ማመፃችሁን ተመለከትኩ። #9፥16 ወርቅ፦ ዘጸ 32፥2-4 ተመልከት። 17ስለዚህም የድንጋይ ጽላቶቹን በፊታችሁ ወርውሬ ሰበርኳቸው፤ 18ከዚህም በኋላ እንደገና አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ምንም ነገር ሳልበላና ሳልጠጣ በእግዚአብሔር ፊት በግንባሬ ተደፍቼ ቈየሁ። ይህንንም ያደረግኹት እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ኃጢአት ሠርታችሁ እርሱን በማስቈጣታችሁ ምክንያት ነበር። 19በመዓቱም ሊደመስሳችሁ ስለ ተነሣሣ የእግዚአብሔር ብርቱ ቊጣ አስፈርቶኝ ነበር፤ ነገር ግን እንደገና እግዚአብሔር ልመናዬን ሰማ። #ዕብ. 12፥21። 20እግዚአብሔር በአሮንም ላይ እጅግ ስለ ተቈጣ ሊገድለው ተቃርቦ ነበር፤ ስለዚህ በዚያው ጊዜ ለአሮንም ጭምር ጸለይኩ፤ 21ያንንም በጥጃ አምሳል አቅልጣችሁ የሠራችሁትን በኃጢአት የተሞላ አጸያፊ ምስል አንሥቼ እሳት ውስጥ ጣልኩት፤ እርሱንም ሰባብሬ እንደ ትቢያ አደቀቅሁት፤ ትቢያውንም ከተራራው በሚወርደው ውሃ ውስጥ ጨመርኩት።
22“እንደገናም በታብዔራ፥ በማሳህና በቂብሮት ሐታዋ እግዚአብሔርን አስቈጣችሁት። #ዘኍ. 11፥3፤34፤ ዘፀ. 17፥7። 23እግዚአብሔር፥ ‘ሂዱ፤ የሰጠኋችሁንም የተስፋ ምድር ውረሱ’ ብሎ ከቃዴስ በርኔ በላካችሁም ጊዜ በእርሱ ላይ ዐመፃችሁ እንጂ አልተማመናችሁበትም፤ ለቃሉም አልታዘዛችሁም። #ዘኍ. 13፥25—14፥38፤ ዘዳ. 1፥21፤ ዕብ. 3፥16። 24እኔ ካወቅኋችሁ ጊዜ ጀምሮ በእግዚአብሔር ላይ እንዳመፃችሁ ናችሁ።
25“ከዚያም ሁሉ የተነሣ በእግዚአብሔር ፊት በግንባሬ ተደፍቼ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቈየሁ፤ ይህንንም ያደረግኹት እርሱ ‘እደመስሳችኋለሁ’ ብሎ ስለ ነበር ነው፤ 26እንዲህም ብዬ ጸለይኩ፥ ‘ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፥ በታላቅ ኀይልህና ብርታትህ ዋጅተህ ከግብጽ ምድር ያወጣኸውን የራስህን ሕዝብ አታጥፋ፤ 27አገልጋዮችህን አብርሃምን፥ ይስሐቅንና ያዕቆብን አስብ፤ የዚህን ሕዝብ እልኸኛነት፥ ክፋትና ኃጢአት ሁሉ አትቊጠርበት፤’ 28ይህ ባይሆን ግን፦ ‘እግዚአብሔር በሰጣቸው የተስፋ ቃል መሠረት ሕዝቡን ወደዚያች ምድር ሊያስገባቸው አልቻለም’ ብለው ግብጻውያን መዘባበት ይጀምራሉ፤ እንዲያውም፦ ‘ሕዝቡን ስለ ጠላቸው ሊገድላቸው ፈልጎ ወደ በረሓ አወጣቸው’ ይሉሃል። 29ከዚህም ሁሉ በላይ ይህ ሕዝብ ለራስህ ወገን እንዲሆን የመረጥከውና በታላቁ ኀይልህና ብርታትህ ከግብጽ ምድር ያወጣኸው ነው።”

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in