YouVersion Logo
Search Icon

ኦሪት ዘዳግም 7

7
እስራኤልና የከነዓን ሕዝቦች
(ዘፀ. 34፥11-16)
1“እግዚአብሔር አምላክህ ልትወርሳት ወደምትገባባት ምድር በሚያመጣህ ጊዜ በፊትህ ያሉትን ብዙ ሕዝቦች ያስወግድልሃል፤ እነርሱም ከአንተ በብዛትና በኀይል የሚበልጡት ሰባት የአሕዛብ ነገዶች ሒታውያን፥ ጌርጌሳውያን፥ አሞራውያን፥ ከነዓናውያን፥ ፈሪዛውያን፥ ሒዋውያንና ኢያቡሳውያን ተብለው የሚጠሩት ናቸው። #ሐ.ሥ. 13፥19። 2እግዚአብሔር አምላክህ እነዚህን ሁሉ ሕዝቦች ለእናንተ አሳልፎ ሲሰጣቸውና እነርሱን ድል በምትነሣበት ጊዜ ሁሉንም መደምሰስ አለብህ፤ ከእነርሱ ጋር ምንም ዐይነት ውል አታድርግ፤ አትራራላቸውም። 3ከእነርሱ አትጋባ፤ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ልጆችህ ከእነርሱ ማንንም እንዲያገቡ አትፍቀድላቸው። 4ይህን ብታደርግ ልጆችህን ከእግዚአብሔር አስኰብልለው ባዕዳን አማልክትን እንዲከተሉ ያደርጉአቸዋል፤ ይህም ከሆነ እግዚአብሔር በአንተ ላይ ተቈጥቶ ወዲያው ያጠፋሃል፤ 5ነገር ግን በእነርሱ ላይ የምታደርጉት እንደዚህ ነው፦ መሠዊያዎቻቸውን አፍርሱ፤ ከድንጋይ የተሠሩ የጣዖት ማምለኪያ ዐምዶቻቸውንም እያንከታከታችሁ ጣሉ፤ አሼራ ተብላ የምትጠራውን ሴት አምላክ ምስል ሰባብሩ፤ ጣዖቶቻቸውንም በእሳት አቃጥሉ፤ #ዘዳ. 12፥3። 6አንተ እግዚአብሔር አምላክህ የራሱ ወገን አድርጎ የመረጠህ ቅዱስ ሕዝብ ነህ፤ በምድር ላይ ካሉት ሕዝቦች ሁሉ አንተ ለእርሱ የተለየህ ምርጥ ሕዝብ እንድትሆን አድርጎሃል። #ዘፀ. 19፥5፤ ዘዳ. 4፥20፤ 14፥2፤ 26፥18፤ ቲቶ 2፥14፤ 1ጴጥ. 2፥9።
7“እግዚአብሔር እናንተን የወደዳችሁና የመረጣችሁ ከሌሎች ሕዝቦች ይበልጥ ብዙዎች በመሆናችሁ አይደለም፤ ይልቁንም እናንተ በምድር ላይ ከሁሉ በቊጥር ያነሳችሁ ሕዝብ ነበራችሁ። 8ነገር ግን እግዚአብሔር እናንተን ስለ ወደደ ለቀድሞ አባቶቻችሁ የሰጠውን የተስፋ ቃል መጠበቅ ፈለገ፤ በታላቅ ኀይሉ ያዳናችሁና የግብጽ ንጉሥ ባርያዎች ከመሆን ነጻ ያወጣችሁም በዚህ ምክንያት ነበር። 9ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካችሁ በፍጹም የታመነ አምላክ መሆኑን አስታውሱ፤ እርሱ ቃል ኪዳኑን ይጠብቃል፤ ለሚወዱትና ትእዛዞቹንም ለሚፈጽሙ ሁሉ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ዘለዓለማዊ ፍቅሩን ያሳያል። 10ነገር ግን የሚጠሉትን በማጥፋት ይበቀላል፤ እነርሱንም ከመበቀል ፈጽሞ አይዘገይም። #ዘፀ. 20፥5-6፤ 34፥6-7፤ ዘኍ. 14፥18፤ ዘዳ. 5፥9-10። 11ስለዚህም ዛሬ እኔ ያዘዝኩህን ትእዛዝ፥ ሕግና ሥርዓት በጥንቃቄ ጠብቅ።
ለእግዚአብሔር መታዘዝ የሚያስገኘው በረከት
(ዘዳ. 28፥1-14)
12“እነዚህን ትእዛዞች ብታዳምጥና በታማኝነትም ብትፈጽማቸው፥ እግዚአብሔር አምላክህ ለቀድሞ አባቶችህ በመሐላ የሰጠውን ቃል ኪዳንና ዘለዓለማዊ ፍቅር ለአንተም ያጸናልሃል፤ 13እርሱ አንተን ይወድሃል፤ ይባርክህማል፤ ስለዚህም በቊጥር ትበዛለህ፤ የምትወልዳቸው ልጆች ይባረካሉ፤ የምድርህም ፍሬ ይባረካል፤ ስለዚህም ብዙ እህል፥ ወይንና የወይራ ዘይት ታገኛለህ፤ ከዚህም ጋር ብዙ የከብትና የበግ መንጋ ያበዛልሃል፤ ለአንተ ይሰጥህ ዘንድ ለቀድሞ አባቶችህ ተስፋ በሰጠው ምድር ላይ ይህን ሁሉ በረከት ይሰጥሃል። 14የአንተን ያኽል በብዙ የተባረከ ሕዝብ በዓለም ላይ ከቶ አይገኝም፤ ከአንተ መካከል ወንድም ሆነ ሴት እንዲሁም ከእንስሶችህ መካከል መኻን አይገኝም። 15እግዚአብሔር ከበሽታ ሁሉ ይጠብቅሃል፤ በግብጽ አገር በነበርክ ጊዜ ካየኸው አሠቃቂ በሽታ ሁሉ ማንኛውንም በአንተ ላይ አያመጣም፤ ነገር ግን እነዚህን በሽታዎች በሚጠሉህ ላይ ያመጣባቸዋል። 16እግዚአብሔር በእጅህ ላይ የጣለልህን ሕዝቦች ሁሉ ያለ ርኅራኄ ደምስስ፤ ጣዖቶቻቸውንም ለማምለክ ወጥመድ ውስጥ አትግባ። #ዘዳ. 11፥13-17።
17“ ‘እነዚህ ሕዝቦች ከእኔ ይበልጣሉ፤ እንዴትስ አድርጌ እነርሱን ነቅዬ አወጣቸዋለሁ’ ብለህ በማሰብ 18አትፍራቸው፤ አምላክህ እግዚአብሔር በግብጽ ንጉሥና በሕዝቡ ሁሉ ላይ ያደረገውን አስታውስ። 19በገዛ ዐይኖችህ ያየሃቸውን ታላላቅ መቅሠፍቶች፥ ተአምራትንና ድንቅ ሥራዎችን፥ እንዲሁም እግዚአብሔር አምላክህ አንተን ነጻ ያወጣበትን ታላቅ ኀይሉንና ሥልጣኑን አስታውስ፤ ግብጻውያንን ባጠፋበት ዐይነት ዛሬ አንተ የምትፈራቸውን እነዚህንም ሕዝቦች ሁሉ ያጠፋቸዋል። 20አምላክህ እግዚአብሔርም በመካከላቸው ሽብር እንዲፈጠር ያደርጋል፤ ከአንተ ሸሽተው የተደበቁት እንኳ ይጠፋሉ። #7፥20 ሽብር እንዲፈጠር ያደርጋል፤ ወይም ተርብ ወይም መቅሠፍት ይሰድባቸዋል። 21ስለዚህም እነዚህን ሕዝቦች አትፍራ፤ እግዚአብሔር አምላክህ ከአንተ ጋር ነው፤ እርሱ ታላቅና መፈራትም የሚገባው አምላክ ነው። 22አምላክህ እግዚአብሔር እነዚህን ሕዝቦች ጥቂት በጥቂት እየነቃቀለ ያስወጣቸዋል፤ እነርሱን ሁሉ በአንድ ጊዜ ማጥፋት አትችልም፤ ይህን ብታደርግ አራዊት በምድሪቱ ላይ በዝተው ያስቸግሩሃል፤ 23እግዚአብሔር ጠላቶችህን በእጆችህ ላይ ይጥልልሃል፤ እስኪደመሰሱም ድረስ በብርቱ ያሸብራቸዋል፤ 24ንጉሦቻቸውን በእጅህ ይጥልልሃል፤ እነርሱንም ታጠፋና ስማቸው የተረሳ እንዲሆን ታደርጋለህ፤ ማንም ተቋቊሞ ሊገታህ አይችልም፤ ሁሉንም ታወድማለህ። 25ጣዖቶቻቸውን በእሳት አቃጥል፤ በእነርሱ ላይ የተለበጠውን ብር ወይም ወርቅ የራስህ ንብረት አድርገህ ለመውሰድ ልብህ አይመኝ፤ ይህን ብታደርግ ወጥመድ ይሆንብሃል፤ እግዚአብሔርም አምልኮ ጣዖትን ስለሚጠላ ብርቱ ጥፋትን ያስከትልብሃል። 26እነዚህንም የረከሱ ጣዖቶች ወደ ቤትህ አታስገባ፤ ብታስገባ ግን አንተም እንደ እነርሱ ትጠፋለህ፤ እነርሱ ለጥፋት የተገቡ ስለ ሆነ በጣም ልትጠላቸውና ልትጸየፋቸው ይገባል።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in