YouVersion Logo
Search Icon

የሐዋርያት ሥራ 25

25
ጳውሎስ ወደ ሮም ንጉሠ ነገሥት ይግባኝ ማለቱ
1ፊስጦስ ወደ ግዛቱ ወደ ቂሣርያ ገብቶ ሦስት ቀን ከቈየ በኋላ ከዚያ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ። 2-3እዚያም የካህናት አለቆችና አንዳንድ ታላላቅ የአይሁድ ወገኖች በጳውሎስ ላይ ክሳቸውን አቀረቡ፤ “ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም በማስመጣት ለእኛ መልካም ነገር አድርግልን” ሲሉም ለመኑት፤ ይህንንም ያሉበት ምክንያት ጳውሎስን በመንገድ ጠብቀው ሊገድሉት ስለ ፈለጉ ነው። 4ፊስጦስ ግን “ጳውሎስ በቂሳርያ በእስር ቤት እየተጠበቀ ነው፤ እኔም አሁን በቶሎ ተመልሼ ወደዚያ እሄዳለሁ፤ 5ባለሥልጣኖቻችሁ ከእኔ ጋር ወደ ቂሳርያ ይሂዱ፤ ጳውሎስ ያደረገው በደል ካለ እዚያ ይክሰሱት” አላቸው።
6ፊስጦስ ከስምንት ወይም ከዐሥር ቀኖች ያልበለጠ ጊዜ ከእነርሱ ጋር ካሳለፈ በኋላ ወደ ቂሳርያ ሄደ፤ እዚያ በደረሰ ጊዜ በማግስቱ በፍርድ ወንበር ላይ ተቀመጠና ጳውሎስን እንዲያቀርቡት አዘዘ። 7ጳውሎስ በቀረበ ጊዜ ከኢየሩሳሌም የመጡት አይሁድ ከበውት ቆሙና ማስረጃ ሊያገኙለት የማይችሉትን ብዙ ከባድ ክስ አቀረቡበት፤ 8ጳውሎስም “እኔ በአይሁድ ሕግ ላይም ሆነ በቤተ መቅደስ ወይም በሮም ንጉሠ ነገሥት ላይ ያደረግኹት በደል የለም” ሲል የመከላከያ መልሱን ሰጠ።
9ፊስጦስ ግን አይሁድን ደስ ለማሰኘት ፈልጎ ጳውሎስን “ወደ ኢየሩሳሌም ሄደህ ስለዚህ ጉዳይ እዚያ በእኔ ፊት ልትፋረድ ትፈልጋለህን?” አለው። 10ጳውሎስ ግን እንዲህ ሲል መልስ ሰጠ፤ “እነሆ! እኔ ልፋረድበት በሚገባኝ በሮም ንጉሠ ነገሥት የፍርድ ወንበር ፊት ቆሜአለሁ፤ አንተም በደንብ እንደምታውቀው በአይሁድ ላይ ያደረግኹት ምንም በደል የለም፤ 11በደለኛ ከሆንኩ ወይም በሞት የሚያስቀጣ በደል ካደረግሁ ከሞት ልዳን አልልም፤ ነገር ግን የእነርሱ ክስ ከንቱ ከሆነ ማንም ለእነርሱ አሳልፎ ሊሰጠኝ አይችልም፤ እኔ ወደ ሮማ ንጉሠ ነገሥት ይግባኝ ብዬአለሁ።”
12በዚያን ጊዜ ፊስጦስ ከአማካሪዎቹ ጋር ተነጋገረና “ወደ ሮማ ንጉሠ ነገሥት ይግባኝ ካልክ ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ትሄዳለህ” አለው።
ጳውሎስ በአግሪጳና በበርኒቄ ፊት መቅረቡ
13ከጥቂት ቀን በኋላ ንጉሥ አግሪጳና በርኒቄ ፊስጦስን “እንኳን ደኅና መጣህ” ለማለት ወደ ቂሳርያ መጡ። 14እዚያም ብዙ ቀን በመቀመጣቸው ፊስጦስ የጳውሎስን ጉዳይ እንዲህ ሲል ለንጉሥ አግሪጳ ገለጠ፤ “ፊልክስ አስሮ የተወው እዚህ አንድ ሰው አለ፤ 15እኔ በኢየሩሳሌም በነበርኩበት ጊዜ የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሽማግሌዎች የዚህን ሰው ጉዳይ ካመለከቱኝ በኋላ እንድፈርድበት ጠየቁኝ። 16እኔ ግን ‘ተከሳሽ ከከሳሾች ፊት ቆሞ ለተከሰሰበት ነገር የመከላከያ መልስ ሳይሰጥ ተከሳሹን አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ሥርዓት አይደለም’ ብዬ መለስኩላቸው። 17ስለዚህ ከሳሾቹ ተሰብስበው ወደዚህ በመጡ ጊዜ ሳልዘገይ በማግስቱ በፍርድ ወንበር ተቀመጥሁና ጳውሎስን በፊቴ እንዲያቀርቡት አዘዝኩ፤ 18ከሳሾቹም ለመናገር አጠገቡ በቆሙ ጊዜ እኔ ክፉ ነገር ሠርቶአል ብዬ የገመትኩትን ያኽል ለክስ የሚያበቃ ምንም ነገር አላቀረቡበትም። 19ነገር ግን ከእርሱ ጋር ይከራከሩበት የነበረው ስለ ሃይማኖታቸውና ሞቶ ስለ ነበረው ጳውሎስ ግን ‘ሕያው ነው’ ስለሚለው ኢየሱስ ነው። 20እኔም እንዲህ ዐይነቱን ነገር መመርመር ስለ ቸገረኝ ጳውሎስን ‘ወደ ኢየሩሳሌም ሄደህ እዚያ በዚህ ነገር ልትፋረድ ትወዳለህን?’ አልኩት። 21እርሱ ግን ጉዳዩ በሮም ንጉሠ ነገሥት እንዲታይለት ፈልጎ ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ይግባኝ በማለቱ ወደ እዚያ እስክልከው ድረስ በእስር ቤት እንዲቈይ አዘዝኩ።”
22አግሪጳም ፊስጦስን “እኔም ይህ ሰው ሲናገር መስማት እፈልጋለሁ” አለው። ፊስጦስም “ነገ ትሰማዋለህ” አለው።
23ስለዚህ በማግስቱ አግሪጳና በርኒቄ ልብሰ መንግሥታቸውን ለብሰውና በታላቅ ግርማ ሆነው በጦር አለቆችና በከተማው ታላላቅ ሰዎችም ታጅበው መጡና ወደ ፍርድ አዳራሽ ገቡ፤ ከዚያም በኋላ ፊስጦስ ጳውሎስን አስጠራ። 24እንዲህም አለ፤ “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ! እናንተም ከእኛ ጋር ያላችሁ ሰዎች ሁሉ! አይሁድ ‘ይህ ሰው ከእንግዲህ ወዲህ በሕይወት መኖር አይገባውም’ በማለት እየጮኹ በኢየሩሳሌምም፥ በዚህም እንዲፈረድበት የጠየቁኝ ይህ የምታዩት ሰው ነው። 25እኔ ግን በሞት የሚያስቀጣው ምንም በደል አላገኘሁበትም፤ እርሱ ወደ ሮም ንጉሠ ነገሥት ይግባኝ በማለቱ ወደዚያ ልልከው ወሰንኩ። 26ይሁን እንጂ ስለ እርሱ ለጌታዬ የምጽፈው የተረጋገጠ ነገር የለኝም፤ ስለዚህ ከተመረመረ በኋላ የምጽፈው ነገር እንዳገኝ ብዬ በፊታችሁ ይልቁንም ንጉሥ አግሪጳ ሆይ! በፊትህ አቅርቤዋለሁ። 27እስረኛ ወደ በላይ ሲላክ፥ የተከሰሰበትን ምክንያት አለመግለጥ ሞኝነት መስሎ ታይቶኛል።”

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in