YouVersion Logo
Search Icon

የሐዋርያት ሥራ 13

13
በርናባስና ሳውል በመንፈስ ቅዱስ ተመርጠው ለማስተማር እንደ ተላኩ
1በአንጾኪያ ባለችው ቤተ ክርስቲያን ነቢያት ተብለው የሚጠሩ ሰባኪዎችና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም፦ በርናባስ፥ ጥቊር የተባለው ስምዖን፥ የቀሬናው ሉክዮስ፥ የአራተኛው ክፍል ገዢ የሄሮድስ አብሮ ዐደግ የነበረው ምናሔና ሳውል ነበሩ። 2እነርሱ ጌታን ሲያገለግሉና ሲጾሙ ሳሉ መንፈስ ቅዱስ “እኔ ለመረጥኳቸው ሥራ በርናባስንና ሳውልን ለዩልኝ!” አለ።
3እነርሱም ጾመውና ጸልየው እጆቻቸውን ከጫኑባቸው በኋላ ላኳቸው።
በርናባስና ሳውል በቆጵሮስ
4በርናባስና ሳውል በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ሄዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ተጓዙ። 5ወደ ሰላሚስ ከተማ በደረሱ ጊዜ በአይሁድ ምኲራቦች የእግዚአብሔርን ቃል አስተማሩ፤ ዮሐንስ ማርቆስም ከእነርሱ ጋር ሆኖ ይረዳቸው ነበር።
6የቆጵሮስን ደሴት አቋርጠው ወደ ጳፉ በደረሱ ጊዜ ባርየሱስ የሚባለውን አንድ አይሁዳዊ ጠንቋይ አገኙ፤ እርሱ ሐሰተኛ ነቢይ ነበር። 7የሚኖረውም ሰርግዮስ ጳውሎስ ከሚባለው አስተዋይ አገረ ገዢ ጋር ነበረ፤ ይህ አገረ ገዢ በርናባስንና ሳውልን አስጠርቶ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ፈለገ። 8ነገር ግን በግሪክ ቋንቋ “ኤሊማስ” ተብሎ የሚጠራው ጠንቋይ ባርየሱስ አገረ ገዢው እንዳያምን ፈልጎ በርናባስንና ሳውልን ተቃወማቸው። 9ጳውሎስ የተባለው ሳውል ግን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ሰውየውን ትኲር ብሎ ተመለከተውና እንዲህ አለው፦ 10“አንተ የዲያብሎስ ልጅ! የእውነት ሁሉ ጠላት! ማታለልና ክፋት ሁሉ የሞላብህ፥ ቀጥተኛውን የጌታን መንገድ ማጣመም አትተውምን! 11አሁንም እነሆ፥ የጌታ እጅ ይመታሃል፤ ዕውርም ትሆናለህ፤ ለጥቂት ጊዜም የፀሐይን ብርሃን አታይም።”
ወዲያውኑ ዐይኖቹን ጭጋግና ጨለማ ሸፈናቸው፤ እጁን ይዞ የሚመራውንም ሰው ዙሪያውን መፈለግ ጀመረ። 12አገረ ገዢውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ አመነ፤ ስለ ጌታ በሰማውም ትምህርት ተደነቀ።
በርናባስና ጳውሎስ በጲስድያ ወደምትገኘው አንጾኪያ መሄዳቸው
13ከዚህ በኋላ ጳውሎስና ጓደኞቹ በመርከብ ተሳፍረው ከጳፉ በጵንፍልያ ወደምትገኘው ወደ ጴርጌ ሄዱ፤ ማርቆስ የተባለው ዮሐንስ ግን ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ ሄደ። 14እነርሱ ግን ከጴርጌ ተነሥተው በጲስድያ ወደምትገኘው ወደ አንጾኪያ ሄዱ፤ በሰንበት ቀን ወደ አንድ ምኲራብ ገብተው ተቀመጡ። 15የሕግና የነቢያት መጻሕፍት ከተነበቡ በኋላ የምኲራቡ አለቆች “ወንድሞች ሆይ፥ ሕዝቡን የሚያጽናና የምክር ቃል ካላችሁ ተናገሩ” ብለው ወደነጳውሎስ ሰው ላኩ። 16ስለዚህ ጳውሎስ ተነሣና ሕዝቡን በእጁ ጠቀሰ፤ እንዲህም ሲል ተናገረ፤ “የእስራኤል ሰዎችና እግዚአብሔርን የምትፈሩ እናንተ አሕዛብ! ስሙ! 17የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ የቀድሞ አባቶቻችንን መረጠ፤ በግብጽ አገር በነበሩበት ጊዜም ትልቅ ሕዝብ አደረጋቸው፤ በታላቅ ኀይሉም ከዚያ አገር አወጣቸው። #ዘፀ. 1፥7፤ 12፥51። 18ለአርባ ዓመትም ያኽል በበረሓ ታገሣቸው #13፥18 ታገሣቸው፦ አንዳንድ የብራና ጽሑፎች “ተንከባከባቸው” ይላሉ። #ዘኍ. 14፥34፤ ዘዳ. 1፥31። 19ከዚያም በኋላ በከነዓን አገር ሰባት መንግሥታትን አጥፍቶ የእነርሱን ምድር አወረሳቸው፤ #ዘዳ. 7፥1፤ ኢያሱ 14፥1። 20ከዚህም በኋላ ለአራት መቶ ኀምሳ ዓመት ያኽል እስከ ነቢዩ ሳሙኤል ድረስ መሳፍንትን ሰጣቸው። #መሳ. 2፥16፤ 1ሳሙ. 3፥20።
21“ከዚያም ቀጥሎ ንጉሥ እንዲያነግሥላቸው እግዚአብሔርን ለመኑ፤ እግዚአብሔርም ከብንያም ወገን የሆነውን የቂስን ልጅ ሳኦልን ለአርባ ዓመት አነገሠላቸው። #1ሳሙ. 8፥5፤ 10፥21። 22ሳኦልንም ከሻረው በኋላ ዳዊትን አነገሠላቸው፤ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት ሲመሰክር፦ ‘እንደ ፍላጎቴ የሚሆንልኝን፤ ፈቃዴንም የሚፈጽመውን፥ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ’ ብሎአል። #1ሳሙ. 13፥14፤ 16፥12፤ መዝ. 89፥20። 23ከዚህ ሰው ዘር እግዚአብሔር በገባው የተስፋ ቃል መሠረት የእስራኤልን አዳኝ ኢየሱስን አስነሣላቸው። 24ኢየሱስ ከመምጣቱ በፊት ዮሐንስ ለእስራኤል ሰዎች ሁሉ የንስሓን ጥምቀት ሰብኮ ነበር። #ማር. 1፥4፤ ሉቃ. 3፥3። 25ዮሐንስ ሥራውን በጨረሰ ጊዜ ‘እኔ ማን መሰልኳችሁ? እኔ መሲሕ አይደለሁም፤ ነገር ግን የጫማውን ማሰሪያ ለመፍታት እንኳ የማልበቃ ከእኔ በኋላ ሌላ ይመጣል’ ይል ነበር። #ማቴ. 3፥11፤ ማር. 1፥7፤ ሉቃ. 3፥16፤ ዮሐ. 1፥20፤27።
26“እናንተ ከአብርሃም ዘር የተወለዳችሁ ወንድሞችና እናንተም እግዚአብሔርን የምትፈሩ አሕዛብ! ይህ የመዳን ቃል የተላከው ለእኛ ነው። 27በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሰዎችና አለቆቻቸው ኢየሱስ አዳኝ መሆኑን አላወቁም፤ በየሰንበቱም የሚነበቡትን የነቢያት መጻሕፍት ባለማስተዋላቸው በእርሱ ላይ በፈረዱበት ጊዜ ትንቢቱ ተፈጻሚ እንዲሆን አድርገዋል። 28ምንም እንኳ ለሞት የሚያበቃ ምክንያት ባያገኙበት እርሱን እንዲገድልላቸው ጲላጦስን ለመኑት። #ማቴ. 27፥22-23፤ ማር. 15፥13-14፤ ሉቃ. 23፥21-23፤ ዮሐ. 19፥15። 29ስለ እርሱ የተጻፈውን ሁሉ ከፈጸሙበት በኋላ ከመስቀል አውርደው ቀበሩት፤ #ማቴ. 27፥57-61፤ ማር. 15፥42-47፤ ሉቃ. 23፥50-56፤ ዮሐ. 19፥38-42። 30ነገር ግን እግዚአብሔር ከሞት አስነሣው። 31ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም ከእርሱ ጋር ለመጡትም ብዙ ቀን ታያቸው፤ እነርሱም አሁን በሕዝብ ፊት ምስክሮቹ ናቸው። #ሐ.ሥ. 1፥3። 32እኛም ይዘንላችሁ የመጣነው እግዚአብሔር ለአባቶቻችን በተስፋ የሰጠውን መልካም ዜና ነው። 33እግዚአብሔር ኢየሱስን ከሞት በማስነሣቱ ይህንኑ ተስፋ ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞታል፤ ይህም በሁለተኛው መዝሙር፥
‘አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፤’
ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። #መዝ. 2፥7። 34መበስበስ እንዳይደርስበት እግዚአብሔር ከሞት እንዳስነሣው ለማስረዳት፥
‘ቅዱሱን የታመነ በረከትን
ለዳዊት የተሰጠውን ተስፋ እሰጣችኋለሁ’ ብሎ ተናግሮአል።
# ኢሳ. 55፥3። 35ደግሞም በሌላ መዝሙር፥
‘ቅዱሱ ልጅህ መበስበስ እንዲደርስበት አታደርገውም’ ይላል።
# መዝ. 16፥10። 36ነገር ግን ዳዊት በሕይወቱ ዘመን አገልግሎቱን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ከፈጸመ በኋላ ሞቶአል፤ ከአባቶቹም ጋር ተቀብሮአል፤ መበስበስም ደርሶበታል። 37እግዚአብሔር ከሞት ያስነሣው ግን መበስበስ አልደረሰበትም። #ኢሳ. 42፥6፤ 49፥6። 38እንግዲህ ወንድሞች ሆይ! የኃጢአት ይቅርታ የሚገኘው በኢየሱስ መሆኑ እንደ ተሰበከላችሁ ዕወቁ፤ 39በእርሱ የሚያምን ሁሉ በሙሴ አማካይነት የተሰጠው ሕግ ነጻ ሊያወጣው ከማይችለው ኃጢአት ሁሉ ነጻ ይወጣል። 40ስለዚህ በነቢያት እንዲህ ተብሎ የተነገረው እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ፤
41‘እናንተ ፌዘኞች እዩ! ተደነቁ! ጥፉም!
ማንም ሰው ቢያወራላችሁ
የማታምኑትን ሥራ በዘመናችሁ እሠራለሁ።’ ”
42ጳውሎስና በርናባስ ከምኲራብ ሲወጡ ይህንኑ ነገር በሚመጣው ሰንበት እንደገና እንዲነግሩአቸው ሰዎቹ ለመኑአቸው። 43የምኲራቡ ጉባኤ በተበተነ ጊዜ ብዙ የአይሁድ ወገኖችና ወደ አይሁድ እምነት ገብተው እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ሰዎች ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሉአቸው፤ ጳውሎስና በርናባስም ሰዎቹን በማስተማር በእግዚአብሔር ጸጋ ጸንተው እንዲኖሩ አሳሰቡአቸው።
44በሚቀጥለው ሰንበት ከከተማው ነዋሪዎች አብዛኞቻቸው የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ተሰበሰቡ፤ 45አይሁድ የሕዝቡን ብዛት ባዩ ጊዜ በቅናት ተሞሉ፤ ንግግሩንም እየተቃወሙ ጳውሎስን ሰደቡት፤ 46ጳውሎስና በርናባስ ግን እንዲህ ሲሉ በድፍረት ተናገሩ፤ “የእግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ ለእናንተ እንዲነገር አስፈላጊ ነው፤ እናንተ አንቀበልም ካላችሁና የዘለዓለም ሕይወት እንደማይገባችሁ በራሳችሁ ከፈረዳችሁ ግን እነሆ፥ እኛ ዞር ብለን ወደ አሕዛብ እንሄዳለን። 47ይህንንም የምናደርገው ጌታ፦ ‘መዳንን እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ እንድታመጣ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ’ በማለት ስላዘዘን ነው።”
48አሕዛብ ይህን በሰሙ ጊዜ ደስ አላቸው፤ የጌታንም ቃል አከበሩ፤ ለዘለዓለም ሕይወት የተመረጡትም ሁሉ አመኑ።
49የጌታም ቃል በዚያ አገር ሁሉ ተስፋፋ። 50የአይሁድ መሪዎች ግን የአይሁድ እምነት ተከታዮች የሆኑትን ሀብታሞች ሴቶችና የከተማውን ታላላቅ ሰዎች አሳድመው በጳውሎስና በበርናባስ ላይ ስደት እንዲነሣ አደረጉ፤ ከአገራቸውም አስወጡአቸው። 51ጳውሎስና በርናባስም በእነርሱ ላይ የእግራቸውን አቧራ አራግፈው ወደ ኢቆንዮን ሄዱ። #ማቴ. 10፥14፤ ማር. 6፥11፤ ሉቃ. 9፥5፤ 10፥11። 52ደቀ መዛሙርቱም በደስታና በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in