ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 8
8
ዳዊት በጦርነት የተቀዳጃቸው ድሎች
(1ዜ.መ. 18፥1-17)
1ጥቂት ዘግየት ብሎም ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን ድል አድርጎ በቊጥጥሩ ሥር አደረጋቸው፤ “ሜቴግ አማ” የተባለችውንም ከተማ ከእነርሱ እጅ ወሰደ።
2ቀጥሎም ንጉሥ ዳዊት ሞአባውያንን ድል አደረገ፤ እስረኞቹ በመሬት ላይ እንዲጋደሙ አድርጎ ከየሦስቱ ሰዎች ሁለት ሁለቱ በሞት እንዲቀጡ አደረገ። ስለዚህም ሞአባውያን የእርሱ ተገዢዎች በመሆን ይገብሩለት ነበር።
3ከዚያም በኋላ ዳዊት የሶርያ ግዛት የሆነችው የጾባ ንጉሥ የሆነውን የረሖብን ልጅ ሀዳድዔዜርን ድል አደረገ፤ ሀዳድዔዜር ድል በተመታበትም ጊዜ በላይኛው ኤፍራጥስ ወንዝ የሚገኘውን ግዛቱን ለማስመለስ በጒዞ ላይ ነበር። 4ዳዊትም ከሀዳድዔዜር አንድ ሺህ ሰባት መቶ ፈረሰኞችንና ኻያ ሺህ እግረኛ ወታደሮችን ማረከበት፤ ሠረገላ ለመሳብ የሚያገለግሉ አንድ መቶ ፈረሶችን አስቀርቶ፥ የቀሩትን ፈረሶች በሙሉ ቋንጃቸውን ቈርጦ ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆኑ አደረገ።
5በደማስቆ የሚኖሩ ሶርያውያንም ንጉሥ ሀዳድዔዜርን ለመርዳት ሠራዊት በላኩ ጊዜ ዳዊት አደጋ ጥሎ ኻያ ሁለት ሺህ ጭፍሮችን ገደለ። 6ከዚያም በኋላ በግዛታቸው ውስጥ የጦር ሰፈሮችን አቋቋመ፤ ሶርያውያንም ለእርሱ ተገዢዎች ሆነው ገበሩለት፤ እግዚአብሔርም ዳዊትን በሄደበት ስፍራ ሁሉ ድልን እንዲቀዳጅ አደረገው። 7ዳዊት የሀዳድዔዜር መኳንንት ያነገቡአቸውን ከወርቅ የተሠሩ ጋሻዎችን ማርኮ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዳቸው፤ 8እንዲሁም ንጉሥ ዳዊት ሀዳድዔዜር ከሚያስተዳድራቸው ቤጣሕና ቤሮታይ ተብለው ከሚጠሩት ከተሞች እጅግ ብዙ የሆነ ነሐስ ወሰደ።
9የሐማት ንጉሥ ቶዒ ዳዊት የሀዳድዔዜርን ሠራዊት በሙሉ ድል ማድረጉን ሰማ። 10ስለዚህም ንጉሥ ሀዳድዔዜርን ድል በመንሣቱ ሰላምታና የደስታ መግለጫ ያቀርብለት ዘንድ ልጁን ዮራምን ወደ ንጉሥ ዳዊት ላከው፤ ቀደም ሲልም ቶዒ በሀዳድዔዜር ላይ ጦርነት ሲያካሄድ የነበረ ነው፤ ዮራምም ከወርቅ፥ ከብርና ከነሐስ የተሠሩ ልዩ ልዩ ስጦታዎችን ለዳዊት ይዞለት ሄደ። 11-12ንጉሥ ዳዊትም ድል ካደረጋቸው ከኤዶም፥ ከሞአብ፥ ከዐሞን፥ ከፍልስጥኤምና ከዐማሌቅ ከወሰደው ብርና ወርቅ፥ እንዲሁም ከሀዳድዔዜር ከወሰደው ምርኮ ጋር እነዚህንም ደግሞ ለእግዚአብሔር የተለዩ አደረገ።
13ዳዊት የጨው ሸለቆ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ዐሥራ ስምንት ሺህ ኤዶማውያንን ገድሎ በተመለሰ ጊዜ ዝነኛ ሆነ፤ #መዝ. 60። 14በመላው ኤዶም ብዙ የጦር ሰፈሮችን አቋቋመ፤ በዚያም የሚኖሩ ሰዎች የእርሱ ተገዢዎች ሆኑ፤ እግዚአብሔር ዳዊትን በሄደበት ስፍራ ሁሉ ድልን ሰጠው።
የዳዊት መንግሥት ሹማምንት
15በዚህ ዐይነት ዳዊት የመላው እስራኤል ንጉሥ ሆኖ ሕዝቡ ዘወትር ትክክለኛ ፍርድ ማግኘት እንዲችል ጥረት ያደርግ ነበር፤ 16የጸሩያ ልጅ ኢዮአብ የሠራዊቱ አለቃ ሲሆን የአሒሉድ ልጅ ኢዮሣፍጥ ታሪክ ጸሐፊ ነበር፤ 17የአሒጡብ ልጅ ሳዶቅና የአብያታር ልጅ አቤሜሌክ ካህናት ነበሩ፤ ሠራያ ደግሞ ጸሐፊ ነበረ፤ 18የዮዳሄ ልጅ በናያ የዳዊት ክብር ዘብ አዛዥ ነበር፤ የዳዊትም ልጆች አማካሪዎቹ ነበሩ። #8፥18 አማካሪዎቹ፦ አንዳንድ የጥንት ቅጂዎች “ካህናት ነበሩ” ይላሉ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 8: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997