ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 36
36
የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአሐዝ
(2ነገ. 23፥30-35)
1የይሁዳ ሕዝብ የኢዮስያስን ልጅ ኢዮአካዝን መርጠው በአባቱ እግር ተተክቶ በኢየሩሳሌም እንዲነግሥ አደረጉት፤ 2ኢዮአሐዝ በይሁዳ ላይ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ኻያ ሦስት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሦስት ወር ገዛ። 3የግብጽ ንጉሥ ኒካዑ ኢዮአሐዝን እስረኛ አድርጎ ወሰደው፤ የይሁዳንም ሕዝብ ሦስት ሺህ አራት መቶ ኪሎ የሚመዝን ብርና ሠላሳ አራት ኪሎ የሚመዝን ወርቅ እንዲገብርለት አደረገ። 4ኒካዑ የኢዮአሐዝን ወንድም ኤልያቄምን በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠው፤ ስሙንም በመለወጥ ኢዮአቄም ብሎ ጠራው፤ ኢዮአሐዝን ግን እስረኛ አድርጎ ወደ ግብጽ ወሰደው። #ኤር. 22፥11-12።
የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም
(2ነገ. 23፥36—24፥7)
5ኢዮአቄም በይሁዳ ላይ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ኻያ አምስት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ዐሥራ አንድ ዓመት ገዛ፤ እርሱም ኃጢአት በመሥራቱ አምላኩን እግዚአብሔርን አሳዘነ። #ኤር. 22፥18-19፤ 26፥1-6፤ 35፥1-19። 6የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር ይሁዳን ወረረ፤ ኢዮአቄምንም ማርኮ ከነሐስ በተሠራ ሰንሰለት በማሰር፥ ወደ ባቢሎን ወሰደው። #ኤር. 25፥1-38፤ 36፥1-32፤ 45፥1-5፤ ዳን. 1፥1-2። 7ናቡከደነፆር የቤተ መቅደሱን ሀብት ዘርፎ በመውሰድ፥ በባቢሎን በሚገኘው ቤተ መንግሥቱ ውስጥ አኖረው። 8ንጉሥ ኢዮአቄም ያደረገው ሁሉ፥ አጸያፊ የሆነው ልማዱና የፈጸመው ክፉ ነገር ጭምር፥ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጻሕፍት ተመዝግቦ ይገኛል፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኢኮንያን ነገሠ።
የይሁዳ ንጉሥ ኢኮንያን
(2ነገ. 24፥8-17)
9ኢኮንያን በይሁዳ ላይ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ስምንት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሦስት ወር ከዐሥር ቀን ገዛ፤ እርሱም ኃጢአት በመሥራቱ እግዚአብሔርን አሳዘነ። 10የጸደይ ወራት በደረሰ ጊዜ ንጉሥ ናቡከደነፆር ኢኮንያንን እስረኛ አድርጎ ወደ ባቢሎን ወሰደው፤ የቤተ መቅደሱንም ሀብት ዘርፎ ወሰደ፤ ከዚህ በኋላ የኢኮንያን አጎት የሆነውን ሴዴቅያስን በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠ። #36፥10 አጎት ወይም ወንድም። #ኤር. 22፥24-30፤ 24፥1-10፤ 29፥1-2፤ 37፥1፤ ሕዝ. 17፥12-13።
የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ
(2ነገ. 24፥18-20፤ ኤር. 52፥1-3)
11ሴዴቅያስ በይሁዳ ላይ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ኻያ አንድ ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ዐሥራ አንድ ዓመት ገዛ፤ #ኤር. 27፥1-22፤ 28፥1-17። 12እርሱም ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ የእግዚአብሔርን ቃል የተናገረውን ነቢዩን ኤርምያስን በትሕትና አላዳመጠውም።
የኢየሩሳሌም መውደቅ
(2ነገ. 25፥1-21፤ ኤር. 52፥3-11)
13ሴዴቅያስ፥ ታማኝ እንዲሆንለት በእግዚአብሔር ስም ባስማለው በንጉሥ ናቡከደነፆር ላይ ዐመፀ፤ ተጸጽቶ ንስሓ በመግባት ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ በእልኸኛነት እምቢ አለ። #ሕዝ. 17፥15። 14በተጨማሪም የካህናት መሪዎችና ሕዝቡ ጣዖቶችን በማምለክ በዙሪያቸው የሚገኙትን ሕዝቦች መጥፎ ምሳሌነት ተከተሉ፤ እግዚአብሔር ራሱ የቀደሰውን ቤተ መቅደስም አረከሱ፤ 15የቀድሞ አባቶቻቸው አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡና ለቤተ መቅደሱ ስላዘነ ያስጠነቅቁአቸው ዘንድ ነቢያትን መላልሶ መላክን ቀጠለ። 16እስራኤላውያን ግን በእግዚአብሔር መልእክተኞች ላይ ተሳለቁ፤ በነቢያቱም በማፌዝ፥ የእግዚአብሔርን ቃል አቃለሉ፤ ከዚህም የተነሣ፥ የእግዚአብሔር ቊጣ በሕዝቡ ላይ ወረደ፤ ከታላቅ ቊጣውም ለማምለጥ አልቻሉም።
17ስለዚህ የባቢሎን ንጉሥ በእነርሱ ላይ አደጋ እንዲጥል እግዚአብሔር ፈቀደ፤ ንጉሡም በቤተ መቅደሱ ውስጥ የነበሩትን እንኳ ሳይቀር፥ በይሁዳ የሚገኙትን ወጣቶች ወንዶችን ሁሉ በሰይፍ ፈጀ፤ እግዚአብሔር ለናቡከደነፆር አሳልፎ ስለ ሰጣቸውም ወጣት ወይም ሽማግሌ፥ ወንድ ወይም ሴት ማንንም ሳይለይ፥ ሁሉንም ያለ ምሕረት አጠፋቸው። #ኤር. 21፥1-10፤ 34፥1-5። 18የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የቤተ መቅደሱን፥ የንጉሡንና የእርሱ ባለሟሎች የሆኑትን ባለሥልጣኖች ግምጃ ቤት በሙሉ ዘርፎ ወደ ባቢሎን ወሰደ፤ 19ቤተ መቅደሱንና የኢየሩሳሌምን ከተማ ከነቤተ መንግሥት ሕንጻዎችና ከነሀብትዋ አቃጠለ፤ የከተማይቱንም የቅጽር ግንብ አፈራረሰ፤ 20በሰይፍ ከመገደል የተረፉትንም ሁሉ ማርኮ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው፤ እነርሱም የፋርስ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት እስከ ተነሣበት ጊዜ ድረስ፥ በዚያው በባቢሎን ባሪያዎች ሆነው፥ ንጉሥ ናቡከደነፆርንና የእርሱን ዘሮች ያገለግሉ ነበር። 21በዚህ ዐይነት አስቀድሞ እግዚአብሔር በነቢዩ ኤርምያስ አማካይነት፥ “ሕዝቡ ሰንበቶችን ባላከበሩበት ልክ ምድሪቱ ለሰባ ዓመት ባድማ ሆና ስለምትቀር፥ የሰንበት ዕረፍት ታገኛለች” ሲል የተናገረው የትንቢት ቃል ተፈጸመ። #ኤር. 25፥11፤ 29፥10።
የፋርስ ንጉሠ ነገሥት ቂሮስ አይሁድን ከግዞት እንዲመለሱ ማዘዙ
(ዕዝ. 1፥1-4)
22እግዚአብሔር በነቢዩ ኤርምያስ አማካይነት አስቀድሞ የተናገረው የትንቢት ቃል፥ ቂሮስ የፋርስ ንጉሠ ነገሥት በሆነ በመጀመሪያው ዓመት ተፈጸመ፤ ከዚህ የሚከተለውን ዐዋጅ እንዲያወጣና በንጉሠ ነገሥቱ ግዛት ሁሉ በጽሑፍ በማስተላለፍ ከፍ ባለ ድምፅ ለሕዝቡ በንባብ እንዲገለጥ ያደርግ ዘንድ እግዚአብሔር ቂሮስን አነሣሣው።
23የዐዋጁም ቃል እንዲህ የሚል ነው፤ “ይህ የፋርስ ንጉሠ ነገሥት የቂሮስ ትእዛዝ ነው፤ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር በዓለም ሁሉ ላይ ገዢ አድርጎኛል፤ በይሁዳ ውስጥ በምትገኘው በኢየሩሳሌም ከተማ ለእርሱ ክብር ቤተ መቅደስን እሠራ ዘንድ ኀላፊነት ሰጥቶኛል፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር ሰዎች የሆናችሁ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ሂዱ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ይሁን።” #ኢሳ. 44፥28።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 36: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997