YouVersion Logo
Search Icon

ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 20

20
በኤዶም ላይ የተደረገ ጦርነት
1ከዚህ በኋላ የዐሞንና የሞአብ ሠራዊት ከእነርሱም ጋር የጦር ቃል ኪዳን ጓደኞቻቸው የሆኑት መዑናውያን ኢዮሣፍጥን ለመዋጋት መጡ፤ 2ሰዎች መጥተው ለንጉሥ ኢዮሣፍጥ “በአንተ ላይ አደጋ ለመጣል እጅግ ብዙ የሆነ ሠራዊት ከሙት ባሕር ባሻገር ካለው ከኤዶም ምድር መጥቶብሃል፤ እነሆ ሐጸጾንታማርን ቀደም ሲል በድል አድራጊነት ይዘዋል” ሲሉ ነገሩት፤ (ሐጸጾንታማር የዔንገዲ ሌላ መጠሪያ ስሙ ነው፤) 3ኢዮሣፍጥ እጅግ ስለ ፈራ ፈቃዱን እንዲገልጥለት ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ ከዚህ በኋላ በመላው አገሪቱ ሕዝቡ ሁሉ እንዲጾም ትእዛዝ አስተላለፈ፤ 4ከመላው የይሁዳ ከተሞች ሰዎች ሁሉ እግዚአብሔር እንዲረዳቸው ለመጸለይ ፈጥነው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። 5ከኢየሩሳሌምም ነዋሪዎች ጋር በአንድነት ሆነው በቤተ መቅደሱ አዲስ አደባባይ ተሰበሰቡ፤ ንጉሥ ኢዮሣፍጥም መጥቶ በሕዝቡ ፊት ቆመ፤ 6ድምፁንም ከፍ በማድረግ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “የቀድሞ አባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ በሰማይ ሆነህ የዓለም መንግሥታትን ሁሉ የምታስተዳድር አንተ ነህ፤ ኀይልና ሥልጣን ሁሉ በአንተ እጅ ነው፤ አንተን ሊቋቋምህ የሚችል ማንም የለም፤ 7አንተ አምላካችን ነህ፤ ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህች ምድር በገባ ጊዜ ቀደም ሲል በዚህ ይኖሩ የነበሩትን አሕዛብ አስወጥተህ ወዳጅህ ለነበረው ለአብርሃም ዘሮች ምድሪቱን የሰጠህ አንተ ነህ፤ #ኢሳ. 41፥8፤ ያዕ. 2፥23። 8ሕዝብህም በዚህች ምድር እስከ አሁን ይኖራል፤ ለአንተም ክብር ቤተ መቅደስን ሠርቶአል፤ ይህንንም ያደረገበት ምክንያት፥ 9‘እኛን ለመቅጣት ጦርነትን፥ ቸነፈርን ወይም ራብን የመሳሰለውን መቅሠፍት ብታደርስብን የአንተ ስም ወደሚጠራበት ወደዚህ ቤተ መቅደስ ፊት ለፊት መጥተን በመቆም ከመከራችን እንድታድነን ወደ አንተ እንጸልያለን፤ አንተም ጸሎታችንን ሰምተህ በመታደግ ታድነናለህ’ ብሎ ነው።
10“እነሆ አሁን የዐሞን፥ የሞአብና የኤዶም ሕዝቦችን ተመልከት፤ አደጋ ጥለውብናል፤ የቀድሞ አባቶቻችን ከግብጽ ምድር በወጡ ጊዜ ወደነዚህ ሕዝቦች ግዛቶች እንዲገቡ አልፈቀድክላቸውም፤ የቀድሞ አባቶቻችን እነርሱን ዞረው አለፉ እንጂ አላጠፉአቸውም፤ #ዘዳ. 2፥4-19። 11እነርሱ የሚከፍሉን ወሮታ ግን ይህ ነው፦ አንተ ርስት አድርገህ ከሰጠኸን ምድር አባረው ሊያስወጡን መጥተዋል፤ 12አምላካችን ሆይ! በእኛ ላይ አደጋ ሊጥሉ በብዛት የመጡትን እነዚህን ሠራዊት ሁሉ መቋቋም ስለማንችል አንተ ራስህ ፍረድባቸው፤ የአንተን ርዳታ ለማግኘት ዐይናችንን ወደ አንተ ከማንሣት በቀር ሌላ ምንም ማድረግ እንደሚገባን አናውቅም።”
13የይሁዳ ሰዎች ሁሉ ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር በዚያው በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ቆመው ነበር፤ 14በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ ከሕዝቡ ጋር በነበረ በአንድ ሌዋዊ ላይ ወረደ፤ ይህም ሌዋዊ ያሐዚኤል ተብሎ የሚጠራ የዘካርያስ ልጅ ነበር፤ እርሱም በማታንያ፥ በይዒኤልና በበናያ በኩል ደግሞ የአሳፍ ወገን ነበር፤ 15ያሐዚኤልም እንዲህ አለ፦ “ንጉሥ ሆይ! እናንተም የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ በሙሉ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ተስፋ አትቊረጡ፤ ይህንንም ታላቅ ሠራዊት ለመቋቋም አትፍሩ፤ ጦርነቱ የእግዚአብሔር ነው እንጂ የእናንተ አይደለም፤ #ዘዳ. 20፥1-4። 16ስለዚህ ነገ እነርሱ በጺጽ አጠገብ ወዳለው መተላለፊያ ሲመጡ አደጋ ጣሉባቸው፤ በይሩኤል አጠገብ ወዳለው በረሓማ አገር በሚያመራው ሸለቆ መጨረሻ ጫፍ ላይ ታገኙአቸዋላችሁ። 17በዚህ ጦርነት ላይ የምትዋጉ እናንተ አይደላችሁም፤ ስፍራ ስፍራችሁን ይዛችሁ ብቻ ጠብቁ፤ እግዚአብሔር ድልን እንደሚያጐናጽፋችሁ ታያላችሁ፤ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች ሆይ! ሳታመነቱና በፍርሃት ሳትሸበሩ ነገ በቀጥታ ሄዳችሁ ተዋጉ! እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ይሆናል!’ ” #ዘፀ. 14፥13-14።
18ከዚህ በኋላ ንጉሥ ኢዮሣፍጥና ከእርሱ ጋር የነበሩት የይሁዳና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሁሉ በግንባራቸው ወደ መሬት ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤ 19የቀዓትና የቆሬ ጐሣዎች አባላት የሆኑ ሌዋውያን ቆሙ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገኑ።
20ሰዎቹ በማግስቱ ጠዋት በማለዳ ተነሥተው ተቆዓ ተብሎ ከሚጠራ ስፍራ አጠገብ ወደሚገኘው በረሓማ አገር ሄዱ፤ ወደዚያ ለመሄድ ጒዞ በመጀመር ላይ ሳሉም ኢዮሣፍጥ እነርሱን “የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች ሆይ! በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ተማመኑ፤ እርሱም ብርታትን ይሰጣችኋል፤ የእግዚአብሔር ነቢያት የሚነግሩአችሁንም እመኑ፤ ይሳካላችኋልም” አላቸው። 21ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ከሕዝቡ ጋር ከተመካከረ በኋላ መዘምራኑ በተቀደሱ በዓላት የሚለብሱአቸውን ካባዎች ለብሰው “ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ!” እያሉ በመዘመር በሠራዊቱ ፊት ለፊት እንዲያልፉ አዘዘ።
22መዘምራኑ መዘመርና ማመስገን በጀመሩ ጊዜ እግዚአብሔር በወራሪዎቹ ሠራዊት ላይ ድብቅ ጦር አምጥቶባቸው፥ ግራ ተጋቡ፤ 23ስለዚህ ዐሞናውያንና ሞአባውያን በኤዶማውያን ሠራዊት ላይ አደጋ ጥለው በሙሉ ደመሰሱአቸው፤ ከዚያም በመቀጠል በጭካኔ እርስ በርሳቸው ተፋጁ፤ 24የይሁዳ ሠራዊት በረሓውን የሚያሳይ ከፍተኛ ቦታ በደረሱ ጊዜ ጠላቶቹ ወዳሉበት አቅጣጫ ሲመለከቱ ጠላቶቹ በሙሉ አልቀው ሬሳዎቻቸው በምድር ላይ ተጋድመው አዩ፤ አንድም እንኳ በሕይወት ተርፎ ያመለጠ አልነበረም።
25ከዚህ በኋላ ኢዮሣፍጥና ወታደሮቹ ምርኮ ለመውሰድ ወደዚያ ሄዱ፤ ብዙ የቀንድ ከብት፥ ስንቅና ትጥቅ፥ ልብስና ሌላም ውድ የሆኑ ዕቃዎች አገኙ፤ ምርኮውንም ለመሰብሰብ ሦስት ቀን ፈጀባቸው፤ ነገር ግን ምርኮው እጅግ ብዙ ስለ ነበር ሁሉንም መውሰድ አልቻሉም፤ 26በአራተኛው ቀን እስከ ዛሬ ድረስ “የበረከት ሸለቆ” ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ተሰበሰቡ፤ እግዚአብሔር ስላደረገላቸውም ነገር ሁሉ አመሰገኑት፤ ሸለቆው “በረከት” ተብሎ የተጠራውም ስለዚህ ነው። 27ከዚያ በኋላ በኢዮሣፍጥ መሪነት የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች ሁሉ እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው ላይ ድልን ስላጐናጸፋቸው እየተደሰቱ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። 28ወደ ኢየሩሳሌም በደረሱ ጊዜም በእምቢልታ፥ በዋሽንትና በበገና ድምፅ እየታጀቡ በሰልፍ ወደ ቤተ መቅደስ ገቡ፤ 29እግዚአብሔር የእስራኤልን ጠላቶች እንዴት እንደ ተዋጋ የሰሙ መንግሥታት ሁሉ የእግዚአብሔር ፍርሀትና ድንጋጤ ዐደረባቸው። 30ስለዚህም ኢዮሣፍጥ አገሪቱን በሰላም አስተዳደረ፤ እግዚአብሔርም በሁሉ አቅጣጫ የሰላም ዋስትና ሰጠው።
የኢዮሣፍጥ ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ
(1ነገ. 22፥41-50)
31ኢዮሣፍጥ የይሁዳ ንጉሥ የሆነው በሠላሳ አምስት ዓመቱ ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ኻያ አምስት ዓመት ገዛ፤ እናቱ ዐዙባ ተብላ የምትጠራ የሺልሒ ልጅ ነበረች፤ 32ኢዮሣፍጥ ከእርሱ በፊት እንደ ነበረው እንደ አባቱ እንደ አሳ በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ አደረገ፤ 33ነገር ግን በከፍተኛ ቦታዎች ላይ የሚገኙትን የማምለኪያ ቦታዎች አላስወገደም፤ ሕዝቡም ወደ ቀድሞ አባቶቹ አምላክ ወደ እግዚአብሔር በሙሉ ልቡ ገና አልተመለሰም ነበር።
34ኢዮሣፍጥ ከነገሠበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዘመነ መንግሥቱ ፍጻሜ ድረስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ ከእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ክፍል አንዱ በሆነው በሐናኒ ልጅ በኢዩ ታሪክ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል።
35በአንድ ወቅት ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ብዙ ክፉ ነገር ከፈጸመው ከእስራኤል ንጉሥ አካዝያስ ጋር የስምምነት ውል አድርጎ ነበር፤ 36ሁለቱም በመተባበር ዔጽዮንጋብር ተብሎ በሚጠራ ወደብ ላይ ውቅያኖስን አቋርጠው ሊጓዙ የሚችሉ መርከቦችን ሠርተው ነበር፤ 37ነገር ግን የማሬሻ ተወላጅ የሆነው የዶዳዋ ልጅ ኤሊዔዘር ኢዮሣፍጥን “ከአካዝያስ ጋር የስምምነት ውል ስላደረግህ እግዚአብሔር የሠራኸውን ሁሉ ያጠፋል” ሲል አስጠንቅቆት ስለ ነበር መርከቦቹ በሙሉ ተሰባበሩ፤ ከቶም በባሕር ላይ አልተጓዙም።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Videos for ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 20