YouVersion Logo
Search Icon

1 ወደ ጢሞቴዎስ 2

2
የቤተ ክርስቲያን ጸሎት
1እግዚአብሔርን በማምለክና ክብር በተመላ ሕይወት ልመና፥ ጸሎት፥ ምልጃና ምስጋና ለሰዎች ሁሉ እንዲደረግ እመክራለሁ። 2እግዚአብሔርን በመፍራትና በመልካም ጠባይ እየተመራን በሰላምና በጸጥታ እንድንኖር በተለይ ለነገሥታትና በከፍተኛ ሥልጣን ላይ ላሉ ሁሉ ጸልዩ። 3ይህም በአዳኛችን በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው። 4የእግዚአብሔር ፈቃድ ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነትን እንዲያውቁ ነው። 5እግዚአብሔር አንድ ነው፤ በመካከል ሆኖ እግዚአብሔርንና ሰውን የሚያስታርቀውም አንድ ነው፤ እርሱም ሰው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። 6ሰዎችን ሁሉ ከኃጢአት ለመዋጀት ራሱን ቤዛ አድርጎ የሰጠ እርሱ ነው፤ ይህም ትክክለኛው ጊዜ ሲደርስ የእግዚአብሔርን የማዳን ሥራ የሚያስረዳ ምስክርነት ነው። 7እኔም እምነትንና እውነትን ለማብሠር ሐዋርያና አስተማሪ ሆኜ ወደ አሕዛብ የተላክሁት በዚህ ምክንያት ነው፤ ይህንንም ስል እውነት እናገራለሁ እንጂ አልዋሽም። #2ጢሞ. 1፥11።
8እንግዲህ በየስፍራው ያሉ ወንዶች ቊጣንና ጥልን አስወግደው የተቀደሱ እጆቻቸውን ወደ ላይ በማንሣት እንዲጸልዩ እፈልጋለሁ። 9እንዲሁም ሴቶች ጠጒርን በማሳመር ወይም በወርቅ ወይም በዕንቊ ወይም ውድ በሆነ ልብስ በማጌጥ ሳይሆን በማፈርና በትሕትና ተገቢ የሆነ የጨዋ ልብስ ይልበሱ። #1ጴጥ. 3፥3። 10እግዚአብሔርን እናመልካለን የሚሉ ሴቶች ማድረግ በሚገባቸው ዐይነት በመልካም ሥራ ያጊጡ። 11ሴት በጸጥታና በመታዘዝ ትማር፤ 12ሴት ወንድን እንድታስተምር ወይም በወንድ ላይ ሥልጣን እንዲኖራት አልፈቅድም፤ እርስዋ ዝም ማለት ይገባታል። 13በመጀመሪያ የተፈጠረ አዳም ነው፤ በኋላም ሔዋን ተፈጠረች። #ዘፍ. 2፥7፤21-22። 14ደግሞም የተታለለችውና የእግዚአብሔርን ሕግ ያፈረሰችው ሴት ናት እንጂ የተታለለው አዳም አይደለም። #ዘፍ. 3፥1-6። 15ነገር ግን ሴት በእምነትና በፍቅር በቅድስናም ብትጽናና ራስን በመቈጣጠር ብትኖር ልጅ በመውለድ ትድናለች።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in