YouVersion Logo
Search Icon

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 7

7
1የቂርያትይዓሪም ሰዎችም የእግዚአብሔርን ታቦት ወስደው በኮረብታ ላይ ወደሚኖረው አቢናዳብ ተብሎ ወደሚጠራ ሰው ቤት አስገቡት፤ የእግዚአብሔርንም ታቦት እንዲጠብቅ ልጁን አልዓዛርን የተለየ እንዲሆን አደረጉ። #2ሳሙ. 6፥2-4።
ሳሙኤል የእስራኤል መሪ መሆኑ
2የእግዚአብሔር ታቦት ለረዥም ጊዜ በቂርያትይዓሪም ኖረ፤ ይኸውም ኻያ ዓመት ያኽል ነበር፤ በዚህን ጊዜ እስራኤላውያን ወደ እግዚአብሔር እጅግ አለቀሱ።
3ሳሙኤልም የእስራኤልን ሕዝብ፦ “በሙሉ ልባችሁ ወደ እግዚአብሔር ከተመለሳችሁ ባዕዳን አማልክትንና ዐስታሮትን ከእናንተ ዘንድ አስወግዱ፤ ራሳችሁንም ለእግዚአብሔር አስገዙ፤ እግዚአብሔርም ከፍልስጥኤማውያን እጅ ያድናችኋል” አላቸው። 4ስለዚህም እስራኤላውያን የባዓልንና የዐስታሮትን ጣዖቶች አስወግደው እግዚአብሔርን ብቻ አመለኩ።
5ከዚህም በኋላ ሳሙኤል “እኔ በዚያ ለእናንተ ወደ እግዚአብሔር ስለምጸልይላችሁ በምጽጳ ተሰብሰቡ” ብሎ ለእስራኤላውያን ሁሉ ጥሪ አደረገ። 6እነርሱም በአንድነት በምጽጳ ተሰበሰቡ፤ ውሃም ቀድተው ለእግዚአብሔር መባ አድርገው በማፍሰስ በዚያን ዕለት ቀኑን ሙሉ ጾሙ፤ “እኛ እግዚአብሔርን በድለናል” ብለውም ተናዘዙ፤ ሳሙኤል በእስራኤላውያን መካከል ይፈርድ የነበረው በምጽጳ ነበር።
7እስራኤላውያን በምጽጳ መሰብሰባቸውንም ፍልስጥኤማውያን በሰሙ ጊዜ አምስቱ የፍልስጥኤም ገዢዎች አደጋ ሊጥሉባቸው ወጡ፤ እስራኤላውያንም ይህን በሰሙ ጊዜ ፈሩ። 8ሳሙኤልንም፦ “ከፍልስጥኤማውያን እጅ ያድነን ዘንድ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር መጸለይን አታቋርጥ” አሉት። 9ሳሙኤልም ገና ጡት ያልተወ ትንሽ የበግ ጠቦት ዐርዶ በሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕት በማድረግ ለእግዚአብሔር አቀረበው፤ ከዚህም በኋላ ስለ እስራኤላውያን ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰማለት፤ 10ሳሙኤል የሚቃጠለውን መሥዋዕት በማቅረብ ላይ ሳለ ፍልስጥኤማውያን እስራኤላውያንን ለመውጋት ዘመቱ፤ ነገር ግን በዚያች ቀን እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን ላይ ከፍተኛ ነጐድጓድ አንጐድጒዶ አርበደበዳቸው፤ እነርሱም ከእስራኤላውያን ፊት ሸሹ። 11እስራኤላውያንም ከምጽጳ ተነሥተው ፍልስጥኤማውያንን እስከ ቤትካር በታች እያሳደዱ በየመንገዱ ገደሉአቸው።
12ሳሙኤልም አንድ ድንጋይ ወስዶ በምጽጳና በሼን መካከል ተከለው፦ እግዚአብሔር እስካሁን ረድቶናል ለማለት ስሙን አቤንዔዜር ብሎ ሰየመው። 13በዚህም ዐይነት ፍልስጥኤማውያን ድል ተመቱ። ሳሙኤል በኖረበት ዘመን ሁሉ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ስለ ነበረ ፍልስጥኤማውያን ዳግመኛ ወደ እስራኤል ድንበር አልቀረቡም። 14ፍልስጥኤማውያን የያዙአቸው በዔቅሮንና በጋት መካከል የነበሩትም ከተሞች ሁሉ ለእስራኤላውያን ተመለሱላቸው፤ እስራኤላውያንም ድንበሮቻቸውን ከፍልስጥኤማውያን እጅ አዳኑ፤ በእስራኤላውያንና በአሞራውያን መካከልም ዕርቀ ሰላም ወርዶ ነበር።
15ሳሙኤል በነበረበት ዘመን ሁሉ የእስራኤልን ሕዝብ መራ፤ 16በየዓመቱም ወደ ቤትኤል፥ ጌልጌላና ምጽጳ እየሄደ በእነዚህ ስፍራዎች ይፈርድ ነበር። 17ከዚያም በራማ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤቱ እየተመለሰ እዚያም የዳኝነት ሥራ ይሠራ ነበር፤ በዚህም በራማ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in