አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 20
20
ዮናታን ዳዊትን እንደ ረዳ
1ከዚህ በኋላ ዳዊት በራማ ከምትገኘው ከናዮት በመሸሽ ወደ ዮናታን ሄዶ “ከቶ ምን አደረግሁ? ምንስ ወንጀል ፈጸምኩ? አባትህ ለመግደል የሚፈልገኝስ ምን በድየው ነው?” ሲል ጠየቀው።
2ዮናታንም “ይህንንስ ከአንተ ያርቀው! አትሞትም፤ ትልቅም ሆነ ትንሽ አባቴ ከእኔ የሚሰውረው ነገር የለም፤ ይህንንም ነገር ቢሆን አባቴ ከእኔ አይሰውርም በፍጹም አይደረግም!” አለው።
3ዳዊት ግን “አባትህ አንተ እኔን ምን ያኽል እንደምትወደኝ በደንብ ያውቃል፤ ስለዚህም ዕቅዱን አንተ እንድታውቅበት ላለማድረግ ወስኖአል፤ ይህንንም የሚያደርገው አንተ ይህን ብታውቅ በብርቱ እንደምታዝን ስለሚያውቅ ነው፤ በሕያው እግዚአብሔር ስምና በነፍስህ እምላለሁ፤ ከአሁን ወዲያ ወደ ሞት ለመድረስ የቀረችን አንዲት ዕርምጃ ብቻ ናት!” አለው።
4ዮናታንም “አንተ የምትፈልገውን ሁሉ አደርግልሃለሁ” አለው።
5ዳዊትም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ነገ አዲስ ጨረቃ የምትታይበት በዓል ነው፤ እኔም ከንጉሡ ጋር መብላት ይኖርብኛል፤ እስከ ነገ ወዲያ ምሽት ድረስ እንድደበቅ ፍቀድልኝ” አለው። #ዘኍ. 28፥11። 6“ምናልባት አባትህ ቢፈልገኝ በቤተሰቡ ዓመታዊ በዓል የሚከበር ስለ ሆነ ወደ ቤተልሔም እንዲሄድ እፈቅድለት ዘንድ ዳዊት እኔን አጥብቆ ለምኖኛል ብለህ ንገረው። 7ንጉሡም ‘እሺ’ ቢል፥ እኔ አገልጋይህ በሰላም እንደምኖር ዐውቃለሁ፤ ንጉሡ ከተቈጣ ግን ጒዳት ሊያደርስብኝ የወሰነ መሆኑን ታውቃለህ፤ 8በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ስለ ተማመንን የሰጠኸኝን የተቀደሰ ተስፋ በመጠበቅ እባክህ ለእኔ ለአገልጋይህ መልካም ነገር አድርግልኝ፤ ወንጀለኛ ሆኜ ከተገኘሁ ግን አንተው ራስህ ግደለኝ እንጂ እንዲገድለኝ ወደ አባትህ ለምን ትወስደኛለህ?”
9ዮናታን ግን “እንዲህ ያለውን ነገር ፈጽሞ አታስብ! በአንተ ክፉ ነገር አስቦ ቢሆን ኖሮ፥ እነግርህ አልነበረም?” አለው።
10ዳዊትም “ታዲያ አባትህ ስለ እኔ ክፉ ቃል ቢናገር ማን ያስረዳኛል?” ሲል ጠየቀ።
11ዮናታንም “ና! ወደ ሜዳ እንሂድ!” ሲል መለሰለት፤ ሁለቱም ወደ ሜዳ ወጡ። 12ዮናታን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ነገ በዚህ ሰዓት ወይም በሦስተኛው ቀን ስለ አንተ መልካም አስተሳሰብ ያለው መሆኑን አባቴን ጠይቄ ከተረዳሁ በኋላ ስለዚሁ ጉዳይ የሚገልጥልህ መልእክተኛ እልክብሃለሁ፤ ለዚህም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ምስክር ይሁን! 13አንተን ለመጒዳት የሚፈልግ ከሆነ ግን፥ ስለ እርሱ ባልገልጥልህና አንተም በሰላም እንድታመልጥ ባላደርግ አባቴ በአንተ ላይ ሊያደርግ ያሰበውን ክፉ ነገር እግዚአብሔር በእኔ ላይ ያድርሰው። እግዚአብሔር ከአባቴ ጋር እንደ ነበር ከአንተም ጋር ይሁን፤ 14-15በሕይወት ብኖር እግዚአብሔር የሚወድደውን ታማኝ ፍቅር አሳየኝ፤ ብሞት ግን እግዚአብሔር የአንተን የዳዊትን ጠላቶች ሁሉ ከገጸ ምድር በሚያጠፋበት ጊዜ ታማኝ የሆነውን ፍቅርህን ከቤተሰቤም አታቋርጥ፥ #2ሳሙ. 9፥1። 16ይህ የገባነው ቃል ኪዳን ለዘለቄታው እንደ ተጠበቀ ይኑር፤ ይህን ቃል ኪዳን ብታፈርስ ግን እግዚአብሔር ይፈርድብሃል።”
17ዮናታን ዳዊትን እንደ ራሱ አድርጎ ይወደው ስለ ነበር “በእርግጥ እንደምትወደኝ ለመግለጥ እንደገና ማልልኝ” አለው። 18ከዚህ በኋላ ዮናታን እንዲህ አለው “ነገ አዲስ ጨረቃ የምትታይበት በዐል ነው፤ መቀመጫህ ባዶ ስለሚሆን በማእድ ላይ አለመኖርህ ይታወቃል፤ 19ከነገ ወዲያ ወደ ማታ ጊዜ ከዚህ በፊት ይህ ችግር ሲጀመር ወደ ተደበቅህበት ቦታ ሄደህ ከኤጼል ድንጋይ በስተጀርባ ተሸሸግ፤ 20እኔም ወደ ጎኑ ዒላማ በማስመሰል ሦስት ፍላጻዎችን እወረውራለሁ፤ 21ከዚያም በኋላ ፍላጻዎቹን እንዲያመጣ ልጁን እልካለሁ፤ ‘ፍላጻዎቹ ከአንተ ወደዚህ ናቸውና አምጣቸው!’ ካልሁት አንተ ከተደበቅኽበት ቦታ ልትወጣ ትችላለህ፤ ስለዚህ ምንም ችግር እንደማይደርስብህና ምንም አደጋ እንደሌለ በእግዚአብሔር ስም እምልልሃለሁ። 22ነገር ግን ልጁን እነሆ! ‘ፍላጻዎቹ ከአንተ ወዲያ ናቸው!’ ያልኩት እንደ ሆነ እግዚአብሔር አሰናብቶሃልና መንገድህን ሂድ። 23እርስ በርሳችን የገባነውን ቃል ኪዳን ለዘለዓለም እንደምንጠብቀው እግዚአብሔር ምስክራችን ነው። ”
24ስለዚህም ዳዊት በዱር ተደብቆ ቈየ፤ አዲስ ጨረቃ በምትታይበት በዓል ሳኦል ግብሩን ለማብላት ተቀመጠ፤ 25ከግድግዳው ጥግ በተለመደው የክብር ስፍራ ሲቀመጥ፥ አበኔር ከእርሱ ቀጥሎ ተቀመጠ፤ ዮናታንም በንጉሡ ፊት ለፊት ተቀምጦ ነበር፤ በዚህ ጊዜ የዳዊት ወንበር ባዶ ነበር፤ 26ይሁን እንጂ ሳኦል በዚያን ቀን ምንም ቃል አልተናገረም፤ ሳኦል ስለ ዳዊት ሲያስብ “ምናልባት አንድ ነገር ገጥሞት ይሆናል፤ ወይም በሕጉ መሠረት በሥርዓት አልነጻም ይሆናል” በማለት ያሰላስል ነበር፤ 27አዲስ ጨረቃ የታየችበት በዓል ካለፈ በኋላም በተከታዩ ቀን የዳዊት ወንበር ባዶ ነበር፤ ስለዚህ ሳኦል ልጁን ዮናታንን “የእሴይ ልጅ ትናንትም፥ ዛሬም ወደዚህ ግብዣ ያልመጣው ስለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው።
28ዮናታንም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ዳዊት ወደ ቤተልሔም ይሄድ ዘንድ እንድፈቅድለት አጥብቆ ለመነኝ፤ 29‘የእኛ ቤተሰብ በከተማው ውስጥ መሥዋዕት ስለሚያቀርብና ወንድሜም በዚያ እንድገኝ ስላዘዘኝ በአንተ ዘንድ ሞገስን አግኝቼ ከሆነ እባክህ ፍቀድልኝና ወንድሞቼን ለማየት ልሂድ’ ብሎ ጠይቆኝ ነበር፤ በዚህ ምክንያት በንጉሡ ግብር ላይ አልተገኘም።”
30የሳኦልም ቊጣ በዮናታን ላይ ነድዶ እንዲህ አለ፤ “አንተ የጠማማና የዐመፀኛ ሴት ልጅ! በራስህ ላይ ኀፍረትንና በእናትህም ላይ ውርደትን ለማምጣት ከእሴይ ልጅ ጋር መወዳጀትህን ደኅና አድርጌ ዐውቃለሁ! 31የእሴይ ልጅ በሕይወት እስካለ ድረስ አንተና መንግሥትህ ጸንታችሁ ለመኖር እንደማትችሉ አታውቅምን? አሁን ሄደህ አምጣው! እርሱ በሞት መቀጣት አለበት!”
32ዮናታንም ለአባቱ ለሳኦል “ስለምን ይሞታል? ምንስ አደረገ?” ሲል መለሰ።
33ከዚህም የተነሣ ዮናታንን ለመግደል የያዘውን ጦር ወረወረበት፤ ስለዚህም ዮናታን አባቱ ሳኦል ዳዊትን ለመግደል ቊርጥ ውሳኔ ማድረጉን አረጋገጠ፤ 34ዮናታንም በቊጣ ከማእዱ ላይ ተነሣ፤ በዚያ ቀን ማለትም አዲስ ጨረቃ በታየችበት በዓል በሁለተኛ ቀን ምንም ምግብ አልበላም፤ ሳኦል ዳዊትን በማዋረዱ ምክንያት ስለ ዳዊት ሁኔታ ዮናታን በብርቱ አዝኖ ነበር። 35በማግስቱ ጠዋት በቀጠሮአቸው መሠረት ዮናታን ዳዊትን ለማግኘት ወደ ሜዳ ሄደ፤ ሲሄድም አንድ ትንሽ ልጅ አስከትሎ ነበር፤ 36ልጁንም “ፈጥነህ ሂድና የምወረውራቸውን ፍላጻዎች ፈልገህ አምጣልኝ” አለው፤ ልጁም ሲሮጥ ዮናታን ከዚያ ልጅ ፊት አሳልፎ አንድ ፍላጻ ወረወረ፤ 37ያም ልጅ ፍላጻው ባረፈበት ቦታ በደረሰ ጊዜ ዮናታን “ፍላጻው አልፎህ ሄዶአል! 38እዚያ ዝም ብለህ አትቁም! ፈጠን በል!” ሲል ጮኸበት፤ ልጁም ፍላጻውን አንሥቶ ወደ ጌታው ተመለሰ፤ 39ይህን ምሥጢር የሚያውቁት ዮናታንና ዳዊት ብቻ ነበሩ እንጂ ልጁ ምንም አያውቅም ነበር። 40ዮናታንም ያንን ልጅ “መሣሪያዎቼን ይዘህ ወደ ከተማ ተመለስ” አለው።
41ልጁም ከሄደ በኋላ ዳዊት ከድንጋዩ ቊልል በስተኋላ ከተደበቀበት ስፍራ ወጥቶ በጒልበቱ በመንበርከክ ሦስት ጊዜ ወደ መሬት ሰገደ፤ እርሱና ዮናታን በሚሳሳሙበት ጊዜ ሁለቱም ያለቅሱ ነበር፤ ከዮናታንም ይልቅ የዳዊት ሐዘን የበረታ ነበር። 42ከዚህ በኋላ ዮናታን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “በሰላም ሂድ፤ እኔና አንተ በዘሬና በዘርህ መካከል እግዚአብሔር ለዘለዓለም ይሁን ብለን በእግዚአብሔር ስም ተማምለናል።” ዳዊት ተነሥቶ ሄደ፤ ዮናታንም ወደ ከተማ ተመለሰ።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 20: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997