YouVersion Logo
Search Icon

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 17

17
ጎልያድ እስራኤላውያንን እንደ ተፈታተነ
1ፍልስጥኤማውያን ሶኮ ተብላ በምትጠራው በይሁዳ ለጦርነት ተሰለፉ፤ እነርሱም በሶኮና በዐዜቃ መካከል ኤፌስዳሚም ተብሎ በሚጠራው ቦታ ሰፍረው ነበር። 2ሳኦልና እስራኤላውያንም ፍልስጥኤማውያንን ለመውጋት በተዘጋጁበት በኤላ ሸለቆ ተሰብስበው መሸጉ። 3በመካከላቸው አንድ ሸለቆ ሲኖር በአንድ በኩል ባለው ኮረብታ ፍልስጥኤማውያን፥ በሌላ በኩል ባለው ኮረብታ እስራኤላውያን ተሰልፈው ነበር።
4ከጋት ከተማ የመጣ፥ ጎልያድ ተብሎ የሚጠራ አንድ ግዙፍ ሰው፥ ከፍልስጥኤማውያን ሰፈር ወጥቶ እስራኤላውያንን መፈታተን ጀመረ፤ የዚያም ሰው ቁመት ሦስት ሜትር ያኽል ነበር፤ 5ከነሐስ የተሠራና ክብደቱ ኀምሳ ሰባት ኪሎ የሚሆን ጥሩርና ከነሐስ የተሠራ የራስ ቊር ነበረው። 6እግሮቹም ከነሐስ በተሠራ ገንባሌ የተሸፈኑ ነበሩ፤ ከነሐስ የተሠራ ጦርም በትከሻው ነበር፤ 7የጦሩ ዘንግ ውፍረቱ የሸማኔ መጠቅለያ ያኽል ነበር፤ የጦሩም ብረት ክብደቱ ሰባት ኪሎ ያኽል ነበር፤ ጋሻውንም ጋሻጃግሬው ተሸክሞለት በፊት በፊቱ ይሄድ ነበር። 8ጎልያድ ተነሥቶ በመቆም በእስራኤል ሠራዊት ላይ እንዲህ እያለ ይደነፋባቸው ጀመር፦ “አሁን በዚያ ቦታ ለጦርነት የተሰለፋችሁት ከቶ ምን ልታደርጉ ነው? እኔ ፍልስጥኤማዊ ነኝ፤ እናንተ ደግሞ የሳኦል ባሪያዎች ናችሁ፤ እንግዲህ ከእኔ ጋር የሚዋጋ አንድ ሰው ከወታደሮቻችሁ መካከል ምረጡና ወደ እኔ መጥቶ ይግጠመኝ። 9እርሱ እኔን አሸንፎ ከገደለኝ፥ እኛ የእናንተ ባሪያዎች ሆነን እንገዛላችኋለን፤ ነገር ግን እኔ አሸንፌ ከገደልኩት፥ እናንተ የእኛ ባርያዎች ሆናችሁ ትገዙልናላችሁ። 10እነሆ እኔ ዛሬ በዚህ የእስራኤልን ሠራዊት እፈታተናለሁ! ከእኔ ጋር የሚዋጋ አንድ ሰው ስጡኝ!” አለ። 11ሳኦልና ወታደሮቹም የፍልስጥኤማዊውን ቃል በሰሙ ጊዜ በፍርሃት ተንቀጠቀጡ።
ዳዊት በሳኦል ጦር ሰፈር
12ዳዊት በይሁዳ በምትገኘው በቤተልሔም የሚኖር የኤፍራታዊው የእሴይ ልጅ ነበር፤ እሴይ ስምንት ልጆች ያሉት ሲሆን ሳኦል በነገሠበት ዘመን በዕድሜ የገፋ ሽማግሌ ሰው ነበር። 13ሦስቱ ታላላቅ ልጆቹም ከሳኦል ጋር ወደ ጦርነት ዘምተው ነበር፤ እነርሱም በኲሩ ኤሊአብ፥ ሁለተኛው አሚናዳብ፥ ሦስተኛውም ሻማ ተብለው ይጠሩ ነበር። 14ዳዊት የሁሉ ታናሽ ሲሆን፥ ሦስት ታላላቅ ወንድሞቹ ሳኦልን ተከትለው ነበር። 15ዳዊት በየጊዜው ከሳኦል ዘንድ እየተመላለሰ በቤተልሔም የአባቱን በጎች ይጠብቅ ነበር።
16ፍልስጥኤማዊውም ለአርባ ቀኖች በፊታቸው እየመጣ ቆሞ ይፎክር ነበር።
17አንድ ቀን እሴይ ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ዐሥር ኪሎ የተጠበሰ እሸትና ዐሥር የዳቦ ሙልሙል ያዝ፤ ፈጥነህም በመሄድ በጦር ሰፈር ለሚገኙት ወንድሞችህ አድርስላቸው። 18እነዚህንም ዐሥር የአይብ ጥፍጥፎች ለሻለቃው የጦር አዛዥ ስጠው፤ ወንድሞችህም እንዴት እንዳሉ በዐይንህ አይተህ የደኅንነታቸውን መረጃ አምጣልኝ። 19ንጉሥ ሳኦል፥ ወንድሞችህና መላው እስራኤላውያን በኤላ ሸለቆ ከፍልስጥኤማውያን ጋር በመዋጋት ላይ ናቸው።”
20ዳዊትም በማግስቱ ማልዶ ተነሣ፤ በጎቹን ለሌላ እረኛ በመተው እሴይ ባዘዘው መሠረት የተዘጋጀውን ምግብ ይዞ ሄደ፤ እስራኤላውያን ጦርነት ለመግጠም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በሚደነፉበት ጊዜ ዳዊት ወደ ጦሩ ሰፈር ደረሰ። 21የፍልስጥኤማውያን ሠራዊትና የእስራኤላውያን ሠራዊት ቦታ ቦታቸውን ይዘው በጦሩ ግንባር ፊት ለፊት በመተያየት ላይ ነበሩ። 22ዳዊትም የያዘውን ምግብ ለስንቅ ጠባቂው ትቶ ወደ ጦሩ ግንባር እየሮጠ ወደ ወንድሞቹ ሄደ፤ ስለ ደኅንነታቸውም ጠየቃቸው። 23ዳዊትም ከወንድሞቹ ጋር በመነጋገር ላይ ሳለ እነሆ፥ ጎልያድ የተባለው ግዙፍ ፍልስጥኤማዊ የጋት ሰው ከዚያ በፊት ያደርገው እንደ ነበር ወደፊት በማምራት በእስራኤላውያን ላይ መፎከሩን ቀጠለ፤ ዳዊትም የእርሱን ድንፋታ ሰማ። 24እስራኤላውያንም ጎልያድን ባዩ ጊዜ በታላቅ ፍርሀት ሸሹ። 25እስራኤላውያንም እርስ በርሳቸውም እንዲህ ይባባሉ ነበር፤ “ይህ በየቀኑ እስራኤልን ለመፈታተን የሚወጣውን ሰው ታያላችሁን? ንጉሥ ሳኦል እርሱን ለሚገድልለት ሰው ብዙ ሀብት ለመስጠት ቃል ገብቶአል፤ ሴት ልጁንም እንደሚድርለትና የአባቱም ቤተሰብ ከግብር ነጻ እንደሚያደርግለት ተናግሮአል።”
26ዳዊትም በአጠገቡ የቆሙትን ሰዎች “ይህን ፍልስጥኤማዊ ገድሎ እስራኤልን ከዚህ አሳፋሪ ውርደት ለሚያድን ሰው ምን ይደረግለታል? ኧረ ለመሆኑ የሕያው እግዚአብሔርን ሠራዊት የሚፈታተን ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ ማን ነው?” ሲል ጠየቀ። 27እነርሱም ጎልያድን ለሚገድል ሰው ምን እንደሚደረግለት ነገሩት።
28የዳዊት ታላቅ ወንድም ኤሊአብም ዳዊት ከሰዎቹ ጋር ሲነጋገር ሰማ፤ እርሱም በዳዊት ላይ በጣም ተቈጥቶ “እዚህ ምን ትሠራለህ? በበረሓ ያሉትንስ እነዚያን ጥቂቶች በጎችህን ለማን ተውካቸው? እኔ ትዕቢተኛነትህንና የልብህን ክፋት ዐውቃለሁ! አሁን የመጣኸው እኮ የጦርነቱን ሁኔታ ለመመልከት ነው!” አለው።
29ዳዊትም “አሁን እኔ ምን አደረግሁ? ለመጠየቅ እንኳ አልችልምን?” ሲል መለሰለት፤ 30ከዚያም ወደ ሌላው ሰው መለስ ብሎ ያንኑ ጥያቄ አቀረበለት፤ በጠየቀ ቊጥር የሚያገኘው መልስ ተመሳሳይ ነበር።
31አንዳንድ ሰዎች ዳዊት የተናገረውን ቃል ሰምተው ስለ ነበር፥ ሄደው ለሳኦል ነገሩት፤ ሳኦልም ልኮ ዳዊትን አስጠራው። 32ዳዊትም ሳኦልን “ንጉሥ ሆይ! ከዚህ ፍልስጥኤማዊ የተነሣ ማንም ሰው መፍራት የለበትም! እኔ ያንተ አሽከር ሄጄ እርሱን እዋጋዋለሁ” አለው።
33ሳኦልም ዳዊትን፦ “አንተ ገና ልጅ ነህ፤ እርሱም ከልጅነቱ ጀምሮ ጦረኛ ስለ ሆነ ይህን ፍልስጥኤማዊ ለመውጋት ትሄድ ዘንድ አትችልም” አለው።
34ዳዊትም እንዲህ አለ፤ “ንጉሥ ሆይ! እኔ ያንተ አሽከር የአባቴን በጎች የምጠብቅ እረኛ ነኝ፤ አንበሳም ሆነ ድብ መጥቶ ጠቦት በሚነጥቅበት ጊዜ፥ 35ተከትዬው ሄጄ አደጋ በመጣል የወሰደውን ጠቦት አስጥለው ነበር፤ አንበሳው ወይም ድቡ ወደ እኔ ተመልሶ በሚመጣበትም ጊዜ ጉሮሮውን አንቄ በመምታት እገድለው ነበር። 36እኔ ያንተ አሽከር አንበሳና ድብ ገድያለሁ፤ ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ የሕያው እግዚአብሔርን ሠራዊት ስለ ተፈታተነ ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል። 37ከአንበሳና ድብ ያዳነኝ እግዚአብሔር ከዚህም ፍልስጥኤማዊ እጅ ያድነኛል።”
ሳኦልም “መልካም ነው! እንግዲህ ሂድ፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሁን!” ሲል መለሰለት። 38ሳኦልም የገዛ ራሱን የጦር ልብስ ለዳዊት አለበሰው፤ ከነሐስ የተሠራውን የራስ ቊር በዳዊት ራስ ላይ ደፍቶ ጥሩርም አለበሰው፤ 39ዳዊትም ይህን ዐይነት ልብስ ለብሶ ስለማያውቅ ሰይፉን በጦር ልብሱ ላይ ታጥቆ ለመሄድ ሲነሣ መራመድ አልቻለም፤ ስለዚህ ዳዊት ሳኦልን፦ “ያልተለማመድኩት ነገር ስለ ሆነ ይህን ሁሉ ልብስ ለብሼ መዋጋት አልችልም፤” አለ፤ ስለዚህም ያንን ሁሉ አወለቀ፤ 40በትሩን አንሥቶ፥ ከወንዝ ዳር አምስት ድቡልቡል ድንጋዮች መርጦ በመልቀም በእረኝነት ኮረጆው ከተተ፤ ወንጭፉንም ይዞ ወደ ፍልስጥኤማዊው ቀረበ።
ዳዊት ጎልያድን ድል ማድረጉ
41ፍልስጥኤማዊው ጎልያድ ወደ ዳዊት ለመቅረብ መራመድ ጀመረ፤ ጋሻጃግሬውም በፊት በፊቱ ይሄድ ነበር፤ 42ዳዊት ቀይ፥ መልከ መልካም፥ ትንሽ ልጅ ስለ ነበረ ዳዊትን ጎልያድ ትኲር ብሎ ባየው ጊዜ በንቀት ዐይን ተመለከተው፤ 43ስለዚህም ጎልያድ ዳዊትን “በትር ይዘህ የምትመጣው እኔ ውሻ ነኝን” ካለው በኋላ በአማልክቱ ስም ረገመው። 44ቀጥሎም “ወዲህ ና! ሥጋህን ለሰማይ አሞራዎችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ” አለው።
45ዳዊትም እንዲህ ሲል መለሰ “አንተ ሰይፍ፥ ጦርና ሾተል ይዘህ መጥተህብኛል፤ እኔ ደግሞ አንተ በምትፈታተነውና በእስራኤል ሠራዊት አምላክ ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ፤ 46በዚህች ቀን እግዚአብሔር በአንተ ላይ ድልን ያጐናጽፈኛል፤ እኔም ራስህን እቈርጣለሁ፤ የፍልስጥኤማውያንንም ወታደሮች ሥጋ ለአሞራዎችና ለአራዊት ምግብ አድርጌ እሰጣለሁ፤ ከዚያም በኋላ መላው ዓለም በእስራኤል ዘንድ አምላክ እንዳለ ያውቃል። 47እዚህ የተሰበሰቡት ሁሉ እግዚአብሔር የሚያድነው በሰይፍና በጦር አለመሆኑን ያውቃሉ፤ ጦርነቱ የእግዚአብሔር ነውና፤ በእናንተም ላይ ድልን እንድንጐናጸፍ ያደርገናል።”
48ፍልስጥኤማዊው አደጋ ሊጥልበት ወደ ዳዊት በቀረበ ጊዜ ዳዊት ጎልያድን ለመግጠም ወደ ጦሩ ግንባር እየሮጠ ሄደ። 49እጁንም ወደ ኮረጆው ከቶ አንዲት ድንጋይ በማውጣት በጎልያድ ላይ ወነጨፈ፤ ድንጋዩም ግንባሩን በጥርቆ ወደ ራስ ቅሉ ገባ፤ ጎልያድም በምድር ላይ በግንባሩ ተደፋ። 50በዚህም ዐይነት ዳዊት በወንጭፍና በድንጋይ ጎልያድን መትቶ በመግደል ድል አደረገ! በእጁም ሰይፍ አልነበረም። #2ሳሙ. 21፥19። 51ወደ እርሱም ሮጦ በመሄድ በላዩ ላይ ቆመ፤ የጎልያድንም ሰይፍ ከሰገባው በመምዘዝ ራሱን ቈረጠው። #1ሳሙ. 21፥9።
ፍልስጥኤማውያንም የእነርሱ ዝነኛ ተዋጊ ጎልያድ መገደሉን ባዩ ጊዜ ሸሹ። 52ከዚህ በኋላ የእስራኤልና የይሁዳ ሰዎች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እየፎከሩ እነርሱን በመከተል እስከ ጋትና እስከ ዔቅሮን የቅጽር በሮች ድረስ አሳደዱአቸው፤ የፍልስጥኤማውያን ሬሳ እስከ ጋትና እስከ ዔቅሮን ድረስ ወደ ሻዕራይም በሚያደርሰው መንገድ ሁሉ ወደቀ። 53እስራኤላውያንም እነርሱን አሳደው ከተመለሱ በኋላ ፍልስጥኤማውያን የነበሩበትን ሰፈር ዘረፉ። 54ዳዊት የጎልያድን ራስ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፤ የጎልያድን የጦር መሣሪያዎች ግን በራሱ ድንኳን አስቀመጠ።
ዳዊት ወደ ሳኦል መቅረቡ
55ዳዊት ጎልያድን ለመውጋት በሚሄድበት ጊዜ ሳኦል ተመልክቶ የጦሩን አዛዥ አበኔርን “ይህ የማን ልጅ ነው?” ሲል ጠየቀው።
አበኔርም “ንጉሥ ሆይ! በሕይወትህ እምላለሁ፤ የማን ልጅ እንደ ሆነ ገና አላወቅሁም” አለው።
56ሳኦልም “ሄደህ ይህ ወጣት የማን ልጅ እንደ ሆነ አጥንተህ ዕወቅ” ሲል አዘዘው።
57ስለዚህ ዳዊት ጎልያድን ገድሎ ወደ ጦር ሰፈር በተመለሰ ጊዜ አበኔር ተቀብሎ ወደ ሳኦል አቀረበው፤ በዚህን ጊዜ ዳዊት የጎልያድን ራስ እንደ ያዘ ነበር፤ 58ሳኦልም “አንተ ወጣት የማን ልጅ ነህ?” ብሎ ጠየቀው።
ዳዊትም “የቤተልሔም ነዋሪ የሆነው የአገልጋይህ የእሴይ ልጅ ነኝ” ሲል መለሰለት።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in