YouVersion Logo
Search Icon

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 12

12
የሳሙኤል የመሰናበቻ ንግግር
1ከዚህ በኋላ ሳሙኤል ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ አለ፤ “ጥያቄአችሁን ሁሉ ተቀብዬ ንጉሥ አንግሼላችኋለሁ፤ 2ከእንግዲህ ወዲህ የሚመራችሁ ንጉሥ አግኝቼአለሁ፤ እኔ ግን ዕድሜዬ ስለ ገፋ ሸምግዬአለሁ፤ ልጆቼም ከእናንተው ጋር አሉ፤ ከወጣትነት ጊዜዬ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የእናንተ መሪ ሆኜ ቈይቼአለሁ። 3እነሆ አሁን በፊታችሁ ቆሜአለሁ፤ በእግዚአብሔርና እርሱ በቀባው ንጉሥ ፊት መስክሩብኝ፤ የማንን በሬ ወስጄአለሁ? የማንንስ አህያ ወስጄአለሁ? ማንንስ አታልዬአለሁ? ማንንስ ጨቊኜአለሁ? ፍርድን ለማዛባት ከማን ላይ ጉቦ ተቀብዬአለሁ? ከእነዚህ ሁሉ አንዱን አድርጌ ከሆነ የወሰድኩትን ለመመለስ ዝግጁ ነኝ።”
4ሕዝቡም “ከቶ አላታለልከንም፤ አልጨቈንከንም፤ ከማንም ሰው ምንም ነገር አልወሰድክም” ሲሉ መለሱለት።
5ሳሙኤልም “እንግዲህ ዛሬ በፊታችሁ ንጹሕ ሆኜ ስለ መገኘቴ እግዚአብሔርና እርሱ የመረጠው ንጉሥ ምስክሮች ናቸው” አለ።
ሕዝቡም “አዎ! እግዚአብሔር ምስክር ነው!” ሲሉ መለሱለት።
6ሳሙኤልም የሚናገረውን ቃል በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “ሙሴንና አሮንን የመረጠ፥ የቀድሞ አባቶቻችሁንም ከግብጽ ምድር ያወጣ እግዚአብሔር ነው፤ #ዘፀ. 6፥26። 7እንግዲህ ተነሥታችሁ ባላችሁበት ቁሙ፤ የቀድሞ አባቶቻችሁንና እናንተን ለማዳን እግዚአብሔር ያደረገላችሁን ድንቅ ሥራዎች ሁሉ በማስታወስ እነሆ እኔ በእግዚአብሔር ፊት እፋረዳችኋለሁ፤ 8ያዕቆብና ቤተሰቡ ወደ ግብጽ ወርደው በዚያ ሲኖሩ ግብጻውያን የጭቈና ቀንበር ጫኑባቸው፤ የቀድሞ አባቶቻቸውም ርዳታ ለማግኘት ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን ላከላቸው፤ እነርሱም ከግብጽ መርተው በማውጣት በዚህች ምድር እንዲሰፍሩ አደረጉአቸው፤ #ዘፀ. 2፥23። 9ነገር ግን ሕዝቡ አምላካቸውን እግዚአብሔርን ረሱ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር የሓጾር ሠራዊት አዛዥ ለነበረው ለሲሣራ፥ ለፍልስጥኤማውያን፥ ለሞአብም ንጉሥ አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም እስራኤላውያንን ድል ነሡ። #መሳ. 3፥12፤ 4፥2፤ 13፥1። 10ከዚያም በኋላ እነርሱ ‘አንተን ትተን በዓልንና ዐስታሮትን በማምለካችን በድለናል፤ አሁንም ከጠላቶቻችን አድነን፤ እናመልክህማለን!’ ብለው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። #መሳ. 10፥10-15። 11እግዚአብሔርም መጀመሪያ ጌዴዎንን፥ ከዚያም በኋላ ባራቅንና ዮፍታሔን፥ ከዚያም ሶምሶንን፥ በመጨረሻም እኔን ላከ፤ እኛም እያንዳንዳችን እናንተን ከጠላቶቻችሁ አዳናችሁ፤ በሰላምም ኖራችሁ፤ #1ሳሙ. 3፥20፤ መሳ. 4፥6፤ 7፥1፤ 11፥29። 12እናንተ ግን እግዚአብሔር አምላካችሁ ንጉሣችሁ ሆኖ ሳለ የአሞን ንጉሥ ናዖስ በእናንተ ላይ መነሣቱን ባያችሁ ጊዜ ‘አይሆንም ንጉሥ አንግሥልን’ አላችሁ። #1ሳሙ. 8፥19።
13“የጠየቃችሁትንና የመረጣችሁትን ንጉሥ እነሆ እግዚአብሔር አነገሠላችሁ፤ 14እግዚአብሔርን ብትፈሩና ብታመልኩት፥ ቃሉንም ብታዳምጡ፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዞች ብትጠብቁ፥ እናንተና በእናንተ ላይ የነገሠው ንጉሥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ብትከተሉ ሁሉ ነገር ይሠምርላችኋል፤ 15ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቃል ባታዳምጡ፥ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ላይ ብታምፁ በእናንተና በንጉሣችሁ ላይ የእግዚአብሔር ቅጣት ይበረታባችኋል፤ #12፥15 በንጉሣችሁ፦ በዕብራይስጡ በአባቶቻችሁ ይላል። 16ስለዚህ ባላችሁበት ጸንታችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር በፊታችሁ የሚያደርገውንም ድንቅ ነገር ታያላችሁ፤ 17እነሆ አሁን እንደምታውቁት የፀሐይ ሙቀት የበዛበት የስንዴ መከር ወራት አይደለምን? ነገር ግን እኔ አሁን እጸልያለሁ፤ እግዚአብሔርም ነጐድጓድና ዝናብ ይልካል፤ ይህም በሚሆንበት ጊዜ ንጉሥ እንዲያነግሥላችሁ በመጠየቃችሁ ምክንያት በደል በመሥራት እግዚአብሔርን ያሳዘናችሁ መሆናችሁን ታረጋግጣላችሁ።”
18ከዚህም በኋላ ሳሙኤል ጸለየ፤ እግዚአብሔርም በዚያኑ ዕለት ነጐድጓድና ዝናብ ላከ፤ ከዚህም የተነሣ ሕዝቡ እግዚአብሔርንና ሳሙኤልን እጅግ ፈሩ፤ 19ሳሙኤልንም እንዲህ አሉት፤ “እንዳንሞት እባክህ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይልን፤ ሌላውን ኃጢአት ሁሉ ከመሥራት አልፈን ንጉሥ እንዲያነግሥልን በመጠየቃችን በደለኞች መሆናችንን አሁን ተገንዝበናል።”
20ሳሙኤልም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “አይዞአችሁ አትፍሩ፤ ይህን የመሰለ ክፉ ነገር ያደረጋችኹ ብትሆኑ እንኳ በሙሉ ልባችሁ እርሱን አገልግሉት እንጂ ፊታችሁን ከእግዚአብሔር ወደ ሌላ አትመልሱ። 21ዋጋቢስ የሆኑ ጣዖቶችን አታምልኩ፤ እነርሱ ሊረዱአችሁም ሆነ ሊያድኑአችሁ አይችሉም፤ 22እግዚአብሔር የእርሱ ሕዝብ ያደርጋችሁ ዘንድ ወዶአልና ስለ ታላቅ ስሙ እናንተን ሕዝቡን አይተውም። 23መልካሙንና ቅኑን ነገር አስተምራችኋለሁ እንጂ ስለ እናንተ መጸለይን በመተው እግዚአብሔርን እበድል ዘንድ ይህ ከእኔ ይራቅ። 24እግዚአብሔርን ብቻ ፍሩ፤ ያደረገላችሁን ድንቅ ነገሮች ተመልክታችሁ በፍጹም ልባችሁ በታማኝነት አገልግሉት። 25ኃጢአት በመሥራት ብትጸኑ ግን እናንተም ንጉሣችሁም ትጠፋላችሁ።”

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in