አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 10
10
1ሳሙኤል የወይራ ዘይት መያዣውን ቀንድ ወስዶ በሳኦል ራስ ላይ አፈሰሰው፤ ሳመውም። ከዚያም በኋላ “እግዚአብሔር በሕዝቡ በእስራኤል ላይ መሪ እንድትሆን ቀባህ፤ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ነግሠህ በዙሪያቸው ካሉ ጠላቶች ታድናቸዋለህ እግዚአብሔር በርስቱ ላይ የሾመህ ለመሆኑ ይህ ማስረጃ ነው፤ 2ዛሬ ከእኔ ተለይተህ በምትሄድበት ጊዜ፥ በብንያም ግዛት በሚገኘው ጼልጻሕ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ባለው በራሔል መቃብር አጠገብ ሁለት ሰዎች ታገኛለህ፤ እነርሱም ስትፈልጋቸው የነበሩ አህዮች መገኘታቸውንና አባትህም ስለ እነርሱ ማሰቡን ትቶ ስለ አንተ በመጨነቅ ‘እንግዲህ ስለ ልጄ ምን ላድርግ’ እያለ በመጠየቅ ላይ መሆኑን ይነግሩሃል። 3ከዚያም አልፈህ በታቦር ወደሚገኘው ወደ አንድ ትልቅ ዛፍ ትደርሳለህ፤ እዚያም ወደ ቤትኤል ወደ እግዚአብሔር የሚሄዱ ሦስት ሰዎችን ታገኛለህ፤ ከእነርሱ አንዱ ሦስት የፍየል ጠቦቶችን እየሳበ የሚሄድ ሲሆን ሁለተኛው ሰው ሦስት ኅብስት የተሸከመ ነው፤ ሦስተኛውም የወይን ጠጅ የተሞላበት አቁማዳ የተሸከመ ይሆናል፤ 4እነርሱም ሰላምታ ከሰጡህ በኋላ ከኅብስቶቹ ሁለቱን ይሰጡሃል፤ አንተም መቀበል ይገባሃል፤ 5ከዚያም አልፈህ የፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር ወደሚገኝበት ጊብዓ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ እግዚአብሔር ኮረብታ ትመጣለህ፤ ወደ ከተማይቱም መግቢያ በር በምትደርስበትም ጊዜ በኮረብታው ላይ መሥዋዕት አቅርበው የሚመለሱ የነቢያትን ጉባኤ ታገኛለህ፤ እነርሱም በገና እየደረደሩ፥ ከበሮ እየመቱ፥ ዋሽንት እየነፉ፥ በመሰንቆ ዜማ ሲዘምሩና ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ትንቢት ሲናገሩ ታገኛቸዋለህ። 6በድንገት የእግዚአብሔር መንፈስ በአንተ ላይ በኀይል ይወርዳል፤ ከእነርሱም ጋር ትንቢት መናገር ትጀምራለህ፤ ልዩ ሰውም ትሆናለህ፤ 7እነዚህም ምልክቶች በተፈጸሙ ጊዜ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ስለ ሆነ ማድረግ የሚገባህን ሁሉ አድርግ፤ 8የሚቃጠለውንና የደኅንነት መሥዋዕት ለማቅረብ አንተን ወደማገኝበት ወደ ጌልጌላ ቀድመኸኝ ትሄዳለህ፤ እኔ መጥቼ ምን ማድረግ እንደሚገባህ እስክነግርህ ድረስ ለሰባት ቀን በዚያው ቈይ።”
9ሳኦልም ከሳሙኤል ተለይቶ በሄደ ጊዜ እግዚአብሔር ሳኦልን ሌላ አዲስ ሰው አደረገው፤ ሳሙኤል በምልክት የነገረውም ሁሉ በዚያን ቀን ተፈጸመ። 10ሳኦል ወደ ጊብዓ በደረሰ ጊዜ የነቢያት ጉባኤ ከሳኦል ጋር ተገናኘ፤ በድንገት የእግዚአብሔር መንፈስ በሳኦል ላይ ወረደ፤ በዚያን ጊዜም እርሱ ከእነርሱ ጋር ትንቢት መናገር ጀመረ። 11ከዚያ በፊት እርሱን የሚያውቁትም ሰዎች ይህን ሲያደርግ በተመለከቱ ጊዜ “የቂስን ልጅ ምን ነካው? ሳኦል ደግሞ ከነቢያት ወገን ነውን?” በማለት እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ። 12በዚያም የሚኖር አንድ ሰው “የእነዚህስ የሌሎቹ ነቢያት ሁኔታ እንዴት ነው? አባቶቻቸውስ እነማን ናቸው?” ሲል ጠየቀ፤ “ሳኦልም ደግሞ ከነቢያት ወገን ነውን?” የሚል የምሳሌ አነጋገር የመነጨውም ከዚህ ነው። #1ሳሙ. 19፥23-24። 13ሳኦልም ትንቢት መናገሩን ከፈጸመ በኋላ በኮረብታው ላይ ወደሚገኘው መሠዊያ ወጣ።
14የሳኦል አጐት ሳኦልንና አገልጋዩን አይቶ “የት ነበራችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።
ሳኦልም “አህዮች ልንፈልግ ሄደን ልናገኛቸው ስላልቻልን ሳሙኤልን ለመጠየቅ ጎራ ብለን ነበር” ሲል መለሰለት።
15አጐትየውም “ሳሙኤል የነገረህን ንገረኝ” አለው።
16ሳኦልም “የአህዮቹን መገኘት ነግሮናል” ሲል መለሰለት፤ ነገር ግን ንጉሥ ስለ መሆኑ ሳሙኤል የነገረውን ሁሉ ለአጐቱ አላወራለትም።
የሳኦል ንጉሥ መሆን በይፋ መነገሩ
17ሳሙኤል ሕዝቡን ከእግዚአብሔር ጋር እንዲገናኝ ወደ ምጽጳ ጠራ። 18እንዲህም አላቸው፦ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር፦ ‘እናንተን እስራኤልን ከግብጽ አወጣኋችሁ፤ ከግብጽ ኀይልና ከሚጨቊኑአችሁ መንግሥታት ሁሉ ጭቈና አዳንኳችሁ’ 19ዛሬ ግን ከመከራችሁና ከጭንቀታችሁ ያዳናችሁን አምላካችሁን ትታችኋል፤ እናንተም፦ ‘አይሆንም ንጉሥ አንግሥልን’ አላችሁት። አላችሁት። ስለዚህ አሁን በየነገዳችሁና በየወገናችሁ ወደ እግዚአብሔር ፊት ቅረቡ”።
20ከዚህ በኋላ ሳሙኤል እያንዳንዱ ነገድ ወደ ፊት እንዲቀርብ አደረገ፤ የብንያምም ነገድ በዕጣ ተመረጠ፤ 21እንደገናም ሳሙኤል፥ የብንያም ነገድ ቤተሰቦች ሁሉ ወደፊት እንዲቀርቡ አደረገ፤ ከነዚያም የማጥሪ ቤተሰብ በዕጣ ተመረጠ፤ በመጨረሻም የማጥሪ ቤተሰብ ወንዶች ወደፊት እንዲቀርቡ አደረገ፤ ከእነርሱም መካከል ለቂስ ልጅ ለሳኦል ዕጣ ወጣ፤ እነርሱም በፈለጉት ጊዜ ሊያገኙት አልቻሉም፤ 22ስለዚህም እነርሱ “ሌላ የቀረ ይኖር ይሆን?” ሲሉ እግዚአብሔርን ጠየቁ።
እግዚአብሔርም “ሳኦል እነሆ በዕቃ መካከል ተደብቆ ይገኛል” ሲል መለሰላቸው።
23ስለዚህም እነርሱ ፈጠን ብለው በመሄድ ከተሸሸገበት አውጥተው ወደ ሕዝቡ አመጡት፤ ሕዝቡም ሳኦል በትከሻውና በቁመት ከሁሉ የሚበልጥ መሆኑን ተመለከቱ፤ 24ሳሙኤልም ሕዝቡን “እግዚአብሔር የመረጠው ሰው እነሆ ይህ ነው! ከእኛም መካከል እርሱን የሚስተካከለው የለም” አለ። ሕዝቡም ሁሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “ረጅም ዕድሜ ለንጉሡ ይሁን!” አሉ።
25ሳሙኤልም ለሕዝቡ፥ ለአንድ ንጉሥ ሊደረግለት የሚገባውን ሥርዓት አስረዳቸው፤ ያንንም በመጽሐፍ ጽፎ በእግዚአብሔር ፊት አስቀመጠው፤ ከዚያም በኋላ ሕዝቡን ሁሉ ወደየቤቱ አሰናበተ፤ 26ሳኦልም በጊብዓ ወደሚገኘው ቤቱ ተመልሶ ሄደ፤ እግዚአብሔር ልባቸውን ያነሣሣው ኀያላንም ሳኦልን ተከትለው ሄዱ፤ 27ነገር ግን አንዳንድ ሥርዓተ አልባዎች “አሁን ይህ ሰው እኛን ለማዳን ይችላል?” ተባባሉ፤ እርሱንም በመናቅ ምንም ዐይነት ገጸ በረከት ሳያመጡለት ቀሩ። ሳኦል ግን ዝም አለ።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 10: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997