YouVersion Logo
Search Icon

አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 7

7
ሰሎሞን ቤተ መንግሥቱን መሥራቱ
1ሰሎሞን ለራሱ የሚሆን ቤተ መንግሥት ሠራ፤ ቤተ መንግሥቱንም ለመሥራት ዐሥራ ሦስት ዓመት ፈጀበት፤ 2-3“የሊባኖስ ደን” ተብሎ የተጠራው አዳራሽ ርዝመቱ አርባ አራት ሜትር፥ ወርዱ ኻያ ሁለት ሜትር፥ ቁመቱ ዐሥራ ሦስት ሜትር ተኩል ነበር፤ አዳራሹም በእያንዳንዱ ረድፍ ዐሥራ አምስት ሆነው በሦስት ረድፍ የቆሙ አርባ አምስት ምሰሶዎች ነበሩት፤ በምሰሶዎቹም ላይ የተጋደሙ፥ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት የተሠሩ ሠረገሎችና በየመካከላቸው የገቡ ሳንቃዎች ነበሩ፤ ከእነርሱም በላይ በምሰሶዎቹ የተደገፉ ዕቃ ቤቶች ነበሩ፤ የእነዚህም ዕቃ ቤቶች ጣራ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት የተሠራ ነበር፤ 4ትይዩ የሆኑት የሕንጻው ሁለት ግንቦች እያንዳንዳቸው በመደዳ ሦስት ሦስት መስኮቶች ነበሩአቸው። 5በሮቹና መስኮቶቹ ሁሉ ባለአራት ማእዘን መቃኖች ነበሩአቸው፤ ለእያንዳንዱ ግንብ በረድፍ የተሠሩ ሦስት ሦስት መስኮቶች ነበሩት፤ የእያንዳንዱ ግንብ መስኮቶች ከሌላው ግንብ መስኮቶች ጋር ትይዩ ነበሩ።
6“ባለ ብዙ ምሰሶዎች” ተብሎ የተጠራው አዳራሽ ርዝመቱ ኻያ ሁለት ሜትር፥ ወርዱ ዐሥራ ሦስት ሜትር ተኩል ነበር፤ በብዙ ምሰሶዎች የተደገፈና ጣራ የተሠራለት መመላለሻ ታዛም ነበረው።
7ሰሎሞን ችሎት ተቀምጦ የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበትም የዙፋን አዳራሽ ከወለሉ እስከ ጣራው ድረስ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት በተሠራ ሳንቃ የተለበደ ነበር።
8ከችሎቱም አዳራሽ በስተ ኋላ በሚገኘው ሌላ አደባባይ ሰሎሞን የሚኖርበትን ሕንጻ እንደ ሌሎቹ ሕንጻዎች አድርጎ አሠራ፤ የግብጽ ንጉሥ ልጅ ለነበረችው ሚስቱም ተመሳሳይ መኖሪያ ቤት አሠራላት። #1ነገ. 3፥1።
9እነዚህ ሁሉ ሕንጻዎችና ታላቁ አደባባይ ጭምር ከመሠረታቸው እስከ ድምድማቸው በጥሩ ታላላቅ ድንጋዮች አጊጠው የተሠሩ ነበሩ፤ ድንጋዮቹ በዚያም በድንጋይ መፍለጫ ስፍራ በፊትም በኋላም በልክ ተጠርበውና ተከርክመው የመጡ ነበሩ። 10መሠረቱም የተሠራው በዚያው በድንጋይ መፍለጫ ስፍራ ተዘጋጅተው በመጡ ታላላቅ ድንጋዮች ነበር፤ ከታላላቆቹም ድንጋዮች ውስጥ የአንዳንዱ ጥርብ ድንጋይ ርዝመት ሦስት ሦስት ሜትር ተኩል ሲሆን፥ የሌሎቹ ደግሞ አራት ሜትር ነበር። 11በእነዚህም ታላላቅ ድንጋዮች ላይ በልክ የተሠሩ ሌሎች ድንጋዮችና ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት የተሠሩ አግዳሚ ሠረገሎች ነበሩ። 12የቤተ መንግሥቱ አደባባይ፥ የቤተ መቅደሱ ውስጣዊ አደባባይና ወደ ቤተ መቅደሱ የሚያስገባው በር በእያንዳንዱ ባለ ሦስት ረድፍ የጥርብ ድንጋይ ሕንጻ ላይ አንዳንድ ረድፍ የሊባኖስ ዛፍ እንጨት ሠረገላ የተጋደመባቸው ግንቦች ነበሩ።
ለሑራም የተመደበለት ሥራ
13ሰሎሞንም ሑራም የተባለውን ሰው ከጢሮስ ከተማ አስጠራ፤ 14ሑራም ነሐስ አቅልጦ በመሥራት ጥበብ የሠለጠነ ባለሞያ ነበር፤ ቀደም ብሎ የሞተው የሑራም አባትም የጢሮስ ተወላጅ ሲሆን እርሱም ነሐስ አቅልጦ በመሥራት ጥበብ የሠለጠነ ባለሞያ ነበር፤ የሑራም እናት የንፍታሌም ነገድ ተወላጅ ነበረች፤ ሑራም በእጅ ጥበብ ብዙ ልምድ ያለው ብልህ ሰው ነበር፤ ከንጉሥ ሰሎሞን በተደረገለት ጥሪ መሠረት መጥቶ የተመደበለትን የነሐስ ሥራ ሁሉ ሠራ።
ከነሐስ የተሠሩት ሁለት ምሰሶዎች
(2ዜ.መ. 3፥15-17)
15ሑራም የእያንዳንዳቸው ቁመት ስምንት ሜትር፥ የዙሪያ ስፋታቸው አምስት ሜትር ከሠላሳ ሳንቲ ሜትር ውስጡ ክፍት የሆነ አራት ጣት ውፍረት ካለው ነሐስ ሁለት ምሰሶዎችን ሠራ። 16እንዲሁም በምሰሶዎቹ ላይ የሚቆሙ የእያንዳንዳቸው ቁመት ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር የሆነ ሁለት የነሐስ ጒልላቶችን ሠራ። 17በምሰሶዎቹም ራስ ላይ የነበሩትን ጉልላቶች ያስጌጡ ዘንድ በሰባት ረድፍ የተሠሩ መረቦችን ሠራ፤ አንዱን መረብ ለአንድ ጉልላት፥ ሁለተኛውን መረብ ለሁለተኛው ጉልላት አደረገ። 18በምሰሶዎቹ ጫፍ ላይ ያሉትን ጉልላቶች ለማስጌጥ ሮማኖችን በሁለት ረድፍ ሠራ። ለየአንዳንዱም ጉልላት እንዲሁ አደረገ።
19በመመላለሻው ምሰሶዎች አናት ላይ ያሉት ጒልላቶች ቁመታቸው አንድ ሜትር ከሰማንያ ሳንቲ ሜትር ሲሆን የአሸንድዬ አበባን በሚመስል ሥራ ተጊጠው ነበር፤ 20እነርሱም ከመረቡ በላይ ባለው ክብ ስፍራ እንዲቆሙ ተደረገ፤ በእያንዳንዱም ጒልላት ዙሪያ በሁለት ረድፍ የተደረደሩ ሁለት መቶ የሮማን ቅርጾች ነበሩ።
21ሑራም ከነሐስ የተሠሩትን ሁለት ምሰሶዎች በቤተ መቅደሱ መግቢያ በር ፊት ለፊት አቆማቸው፤ ከቤተ መቅደሱ መግቢያ በር በስተ ደቡብ በኩል የቆመው ምሰሶ “ያኪን” ተብሎ ተጠራ፤ በስተ ሰሜን በኩል የቆመው ምሰሶ ደግሞ ቦዔዝ ተባለ። #7፥21 “ያኪን”፦ በዕብራይስጥ “እግዚአብሔር ያቆማል” ማለት ነው። #7፥21 ቦዔዝ፦ በዕብራይስጥ “በእግዚአብሔር ኀይል” ማለት ነው። 22በምሰሶዎቹ ጫፍ ላይ የአሸንድዬ አበባ የሚመስሉ ከነሐስ የተሠሩ ጉልላቶች ነበሩ።
የምሰሶዎቹም ሥራ በዚህ ዐይነት ተፈጸመ።
ከነሐስ የተሠራ ገንዳ
(2ዜ.መ. 4፥2-5)
23ሑራም ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር ጥልቀት፥ አራት ሜትር ከአርባ ሳንቲ ሜትር የክብ ማእከል ርዝመት፤ ዐሥራ ሦስት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር ዙሪያ ያለው አንድ ክብ ገንዳ ከነሐስ ሠራ። 24የገንዳው አፍ ውጫዊ ክፈፍ ሁሉ ከገንዳው ጋር አንድ ወጥ ሆነው በቅል አምሳል ከነሐስ የተሠሩና በሁለት ረድፍ የተደረደሩ፥ ቅርጾች ነበሩት። 25ገንዳውም ከነሐስ በተሠሩ ዐሥራ ሁለት የበሬዎች ምስሎች ጀርባ ላይ ተቀመጠ፤ ኰርማዎቹም በየአቅጣጫው ፊታቸውን ወደ ውጪ መልሰው ሦስቱ ወደ ሰሜን፥ ሦስቱ ወደ ደቡብ፥ ሦስቱ ወደ ምሥራቅ ሦስቱ ወደ ምዕራብ የሚመለከቱ ይመስሉ ነበር። 26የገንዳው ጐኖች ውፍረት አንድ መዳፍ ነበር፤ የጽዋ ቅርጽ ያለው አበባ የሚመስል የአፉ ክፈፍ የአሸንድዬ አበባ ቅርጽ ነበረው፤ ይህም ገንዳ አርባ ሺህ ሊትር ያኽል ውሃ የሚይዝ ነበር።
ከነሐስ የተሠሩ ባለመንኰራኲር የዕቃ ማስቀመጫዎች
27ሑራም የእያንዳንዱ ርዝመት አንድ ሜትር ከሰማንያ ሳንቲ ሜትር፥ ወርዱ አንድ ሜትር ከሰማንያ ሳንቲ ሜትር፥ ቁመቱ አንድ ሜትር ከሠላሳ ሳንቲ ሜትር የሆነ ዐሥር ባለመንኰራኲር የዕቃ ማስቀመጫዎችን ከነሐስ ሠራ። 28የዕቃ መቀመጫዎቹም የተሠሩት በክንፎቹ መካከል ልሙጥ በሆነ ነገር ነበር። 29ልሙጥ በሆነው ነገርም ላይ በአንበሶች፥ በበሬዎችና በኪሩቤል አምሳል የተቀረጹ ምስሎች ነበሩ፤ ከአንበሶቹ፥ ከበሬዎቹና ከኪሩቤሉ ቅርጾች ራስጌና ግርጌ የአበባ ጒንጒን የሚመስሉ ቅርጾች ነበሩ፤ 30እያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ ከነሐስ የተሠሩ አራት መንኰራኲሮችና መንኰራኲሮቹ የሚሽከረከሩበት የነሐስ ወስከምቶች ነበራቸው፤ እንዲሁም በአራቱ ማእዘኖች የመታጠቢያ ገንዳ መደገፊያዎች ነበሩ፤ መደገፊያዎቹም የአበባ ጒንጒን በሚመስሉ ቅርጾች አጊጠው ነበር። 31የመታጠቢያ ገንዳውም አንገት ዐሥራ ስምንት ሳንቲ ሜትር ነበር፤ እርሱም ክብ ነበር፤ ቁመቱም አርባ አምስት ሳንቲ ሜትር ነበር፤ በአንገቱም ላይ ማስጌጫ ቅርጽ ነበረበት፤ የገንዳው ተሸካሚ ግን አራት ማእዘን ነበር እንጂ ክብ አልነበረም። 32የመንኰራኲሮቹም ቁመት ሥልሳ ስድስት ሳንቲ ሜትር ነበር፤ መንኰራኲሮቹም በዕቃ ማስቀመጫው ጠፍጣፋ ነሐስ ሥር ነበሩ፤ የመንኰራኲሮችም ወስከምቶች ከዕቃ ማስቀመጫዎቹ ጋር አንድ ወጥ ሆነው የተሠሩ ነበሩ፤ 33መንኰራኲሮቹም የሠረገላ መንኰራኲሮችን ይመስሉ ነበር፤ ወስከምቶቻቸው፥ ቅትርቶቻቸውና ዐቃፊዎቻቸው ሁሉም ከነሐስ ቀልጠው የተሠሩ ነበሩ። 34የእያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ አራት ማእዘኖች በየግርጌአቸው ከእነርሱው ጋር አንድ ወጥ ሆነው ከነሐስ የተሠሩ አራት መደገፊያዎች ነበሩአቸው። 35በእያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ ጫፍ ዙሪያ ክፈፍ ላይ ኻያ ሁለት ሳንቲ ሜትር ርዝመት ያለው አንድ ክብ ቅርጽ ነበር፤ መደገፊያዎቹና ጠፍጣፋ ነሐሶቹ ከዕቃ ማስቀመጫው ጋር አንድ ወጥ ሆነው የተሠሩ ነበሩ። 36በእነዚሁ መደገፊያዎችና ጠፍጣፋ ነሐሶች መካከል ባለው ክፍት ቦታ ሁሉ በኪሩቤል፥ በአንበሶችና በዘንባባ ዛፎች አምሳል በተሠሩ ቅርጾች አጊጠው ነበር፤ እንዲሁም ዙሪያቸው የአበባ ጒንጒን በሚመስሉ ቅርጾች አጊጠው ነበር። 37እንግዲህ ዐሥሩ ባለመንኰራኲር የዕቃ ማስቀመጫዎች የተሠሩት በዚህ ዐይነት ነበር። መጠናቸውና ቅርጻቸው እኩል ስለ ሆነ ሁሉም ተመሳሳይ ነበሩ።
38ሑራም ለእያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ ዐሥር መታጠቢያ ገንዳዎች ሠራ፤ እያንዳንዱ ገንዳ ዙሪያ አጋማሽ ስፋት አንድ ሜትር ከሰማንያ ሳንቲ ሜትር ያኽል ሲሆን፥ ስምንት መቶ ሊትር ያኽል ውሃ ይይዝ ነበር፤ #ዘፀ. 30፥17-21። 39ሑራምም አምስቱን የዕቃ ማስቀመጫዎች ከቤተ መቅደሱ በስተደቡብ፥ የቀሩትንም አምስቱን በቤተ መቅደሱ በስተ ሰሜን በኩል አቆመ፤ ገንዳውን ደግሞ በቤተ መቅደሱ ደቡባዊ ምሥራቅ ማእዘን ላይ አቆመው።
የቤተ መቅደሱ ዕቃዎች ዝርዝር ባጭሩ
(2ዜ.መ. 4፥11—5፥1)
40ሑራም ድስቶችን፥ መጫሪያዎችንና ጐድጓዳ ሳሕኖችን ሠራ፤ በዚህ ዐይነትም ለንጉሥ ሰሎሞን ሊሠራለት የጀመረውን የእግዚአብሔርን መቅደስ ሥራ ፈጸመ፤ ከሠራቸውም ነገሮች ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፦
41ሁለቱ ምሰሶዎች፥ በምሰሶዎቹም ላይ የነበሩትን ማቶቶች የሚመስሉ ጉልላቶች፥ በምሰሶውም ላይ የነበሩትን ሁለቱን ጉልላቶች የሚሸፍኑት ሁለቱ መረቦች፥
42በእያንዳንዱ ጒልላት ላይ በመረብ አምሳል የተሠሩት ሰንሰለቶች፥
በእያንዳንዱ ጒልላት ቅርጽ ላይ በሁለት ረድፍ አንዳንድ መቶ ዙር የሆኑ፥ ከነሐስ የተሠሩ አራት መቶ የሮማን ቅርጾች፥
43ዐሥሩ ባለመንኰራኲር የዕቃ ማስቀመጫዎች፥
ዐሥሩ የመታጠቢያ ገንዳዎች፥
44ውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ፥
ገንዳውን ደግፈው የሚይዙ የዐሥራ ሁለቱ በሬዎች ቅርጾች፥
45ድስቶቹ፥ መጫሪያዎቹና ጐድጓዳ ሳሕኖቹ፤
ለቤተ መቅደሱ አገልግሎት ይውሉ ዘንድ ሑራም እነዚህን ሁሉ ዕቃዎች ለሰሎሞን የሠራለት ከተወለወለ ንጹሕ ነሐስ ነበር። 46ንጉሥ ሰሎሞን እነዚህን ሁሉ ያሠራው በዮርዳኖስ ሸለቆ በሱኮትና ጻርታን መካከል በሚገኘው በብረት ማቅለጫ ስፍራ ነበር። 47ከነሐስ የተሠራው ይህ ሁሉ ዕቃ እጅግ ብዙ ስለ ነበር፥ ሰሎሞን በሚዛን እንዲለካ አላደረገውም፤ ስለዚህ ክብደቱ ምን ያኽል እንደ ሆነ ተወስኖ አልታወቀም።
48ለቤተ መቅደሱ አገልግሎት ይውሉ ዘንድ ሰሎሞን የሚከተሉትን ዕቃዎች አሠራ፤ እነርሱም የወርቁ መሠዊያ፥ ለእግዚአብሔር የሚቀርበው ኅብስት ማኖሪያ የወርቅ ጠረጴዛ፥ #ዘፀ. 25፥23-30፤ 30፥1-3። 49በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት አምስቱ በስተደቡብ፥ አምስቱ ደግሞ በስተ ሰሜን የሚቀመጡት ዐሥሩ የወርቅ መቅረዞች፥ አበባዎች፥ የመብራት ቀንዲሎች፥ የእሳት መቈስቈሻዎች፥ #ዘፀ. 25፥31-40። 50ጽዋዎች፥ የዐመድ ማጠራቀሚያዎች፥ ጐድጓዳ ሳሕኖች፥ የዕጣን ማቅረቢያ ዕቃዎች፥ ማንደጃዎች፥ ለቅድስተ ቅዱሳን በሮችና ለቤተ መቅደሱ ውጫዊ በሮች የሚያገለግሉ ማጠፊያዎች ነበሩ። እነዚህ ሁሉ ዕቃዎች ከወርቅ የተሠሩ ናቸው።
51ንጉሥ ሰሎሞን የቤተ መቅደሱን ሥራ ሁሉ ከፈጸመ በኋላ አባቱ ዳዊት ለእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት እንዲውል የለየውን ብሩን፥ ወርቁንና ሌላውንም ዕቃ በሙሉ በቤተ መቅደሱ ግምጃ ቤት ውስጥ አኖረው። #2ሳሙ. 8፥11፤ 1ዜ.መ. 18፥11።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in