YouVersion Logo
Search Icon

አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 14

14
ዳዊት በኢየሩሳሌም ያከናወናቸው ሥራዎች
(2ሳሙ. 5፥11-16)
1የጢሮስ ንጉሥ ኪራም መልእክተኞችን ወደ ዳዊት ላከ፤ ከእነርሱም ጋር ለዳዊት ቤተ መንግሥት የሚሠሩለት የሊባኖስ ዛፍ ግንድ የያዙ አናጢዎችና ግንበኞች ነበሩ፤ 2ስለዚህም ዳዊት እግዚአብሔር የእስራኤል ንጉሥ አድርጎ እንዳጸናውና ስለ ሕዝቡም ስለ እስራኤል ሲል መንግሥቱን እንዳበለጸገለት ተገነዘበ።
3በዚያም በኢየሩሳሌም ዳዊት ብዙ ሚስቶችን አገባ፤ ብዙ ወንዶችንና ሴቶች ልጆችንም ወለደ፤ 4በኢየሩሳሌም ሳለ የወለዳቸው ወንዶች ልጆች ሻሙዓ፥ ሾባብ፥ ናታን፥ ሰሎሞን፥ 5ይብሐር፥ ኤሊሹዓ፥ ኤሊጴሌት፥ 6ኖጋህ፥ ኔፌግ፥ ያፊዓ፥ 7ኤሊሻማዕ፥ ቤኤልያዳና ኤሊፌሌት ተብለው የሚጠሩት ናቸው።
ዳዊት በፍልስጥኤማውያን ላይ የተቀዳጀው ድል
(2ሳሙ. 5፥17-25)
8ዳዊት በመላው እስራኤል ላይ መንገሡን ፍልስጥኤማውያን በሰሙ ጊዜ እርሱን ለመማረክ ሠራዊታቸውን አዘመቱ፤ ዳዊትም ይህን ሰምቶ ከእነርሱ ጋር ጦርነት ለመግጠም ወጣ፤ 9ፍልስጥኤማውያን ወደ ራፋይም ሸለቆ መጥተው ወረሩአት፤ 10ዳዊትም “በፍልስጥኤማውያን ላይ ጦርነት ልክፈትን? በእነርሱስ ላይ ድልን ታጐናጽፈኛለህን?” ሲል እግዚአብሔርን ጠየቀ።
እግዚአብሔርም “አዎ፥ አደጋ ጣልባቸው! እኔም ድልን አጐናጽፍሃለሁ!” አለው።
11ስለዚህ ዳዊት ባዓልፈራጺም ተብሎ በሚጠራ ስፍራ በፍልስጥኤማውያን ላይ አደጋ ጥሎ ድል ካደረጋቸው በኋላ “የጠላትን ሠራዊት እንደ ጐርፍ ጥሼ እንዳልፍ እግዚአብሔር ረዳኝ” አለ፤ ከዚያም በኋላ ያ ስፍራ “ባዓልፈራጺም” ተብሎ ተጠራ፤ 12ፍልስጥኤማውያን ሲሸሹ ጣዖቶቻቸውን ጥለው ሄዱ፤ ዳዊትም ጣዖቶቹ በሙሉ እንዲቃጠሉ ትእዛዝ ሰጠ።
13ፍልስጥኤማውያን ደግሞ ወደ ሸለቆው ተመልሰው እንደገና መውረር ጀመሩ፤ 14ዳዊትም እንደገና የእግዚአብሔርን ፈቃድ ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም “ከኋላ በኩል ዞረህ በሾላ ዛፎች አጠገብ በመሆን አደጋ ጣልባቸው እንጂ በዚህ በኩል ሽቅብ ወጥተህ በመሰለፍ አደጋ አትጣልባቸው፤ 15እኔ ፊት ፊትህ ሄጄ የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ድል ስለምመታ በዛፎች ጫፍ ላይ የሰልፍ ድምፅ ስትሰማ አደጋ ጣል” አለው። 16ዳዊትም እግዚአብሔር እንዳዘዘው በማድረግ ፍልስጥኤማውያንን ከገባዖን እስከ ጌዜር ድል አድርጎ አባረራቸው 17የዳዊትም ዝና በየቦታው ተሠራጨ፤ እግዚአብሔርም ዳዊት በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተፈራ እንዲሆን አደረገ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in