ሮሜ 8:26-37
እንዲሁም ደግሞ መንፈስ በድካማችን ያግዘናል፤ እንዴት መጸለይ እንደሚገባን አናውቅም፤ መንፈስ ግን በቃላት ሊገለጥ በማይችል መቃተት ለእኛ ይማልድልናል። ልባችንንም የሚመረምረው እርሱ የመንፈስን ሐሳብ ያውቃል፤ ምክንያቱም መንፈስ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለቅዱሳን ይማልዳልና። እግዚአብሔር፣ ለሚወድዱትና እንደ ሐሳቡ ለተጠሩት፣ ነገር ሁሉ ተያይዞ ለበጎ እንዲሠራ እንደሚያደርግላቸው እናውቃለን። እግዚአብሔር አስቀድሞ ያወቃቸውን የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ወሰናቸው፤ ይኸውም ከብዙ ወንድሞች መካከል እርሱ በኵር እንዲሆን ነው። አስቀድሞ የወሰናቸውን ጠራቸው፤ የጠራቸውን አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውን አከበራቸው። ታዲያ ለዚህ ምን እንመልሳለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ፣ ማን ሊቃወመን ይችላል? ለገዛ ልጁ ያልሳሳለት፣ ነገር ግን ለሁላችንም አሳልፎ የሰጠው እርሱ፣ ሁሉንስ ነገር ከእርሱ ጋር እንደ ምን በልግስና አይሰጠን? እግዚአብሔር የመረጣቸውን የሚከስስ ማን ነው? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፤ ታዲያ የሚኰንን ማን ነው? የሞተው፣ እንዲሁም ከሞት የተነሣው፣ በእግዚአብሔር ቀኝ የተቀመጠው ክርስቶስ ኢየሱስ፣ ስለ እኛ ይማልዳል። ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማን ነው? ችግር ነው ወይስ ሥቃይ፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ራብ፣ ወይስ ዕራቍትነት፣ ወይስ አደጋ፣ ወይስ ሰይፍ? ይህም፣ “ስለ አንተ ቀኑን ሙሉ ከሞት ጋር እንጋፈጣለን፤ እንደሚታረዱ በጎች ተቈጠርን” ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። ምንም አይለየንም፤ በዚህ ሁሉ በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።
ሮሜ 8:26-37