የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መዝሙር 51:1-12

መዝሙር 51:1-12 - እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቸርነትህ መጠን፣
ምሕረት አድርግልኝ፤
እንደ ርኅራኄህም ብዛት፣
መተላለፌን ደምስስ።
በደሌን ፈጽሞ ዕጠብልኝ፤
ከኀጢአቴም አንጻኝ።

እኔ መተላለፌን ዐውቃለሁና፤
ኀጢአቴም ዘወትር በፊቴ ነው።
በውሳኔህ ትክክል፣
በምትሰጠው ፍርድም ንጹሕ ትሆን ዘንድ፣
አንተን፣ በርግጥ አንተን ብቻ በደልሁ፤
በፊትህም ክፉ ነገር አደረግሁ።
ስወለድ ጀምሮ በደለኛ፣
ገና እናቴም ስትፀንሰኝ ኀጢአተኛ ነኝ።
እነሆ፤ እውነትን ከሰው ልብ ትሻለህ፤
ስለዚህ ጥልቅ ጥበብን በውስጤ አስተምረኝ።

በሂሶጵ እርጨኝ፤ እኔም እነጻለሁ፤
ዕጠበኝ፤ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ።
ሐሤትንና ደስታን አሰማኝ፤
ያደቀቅሃቸው ዐጥንቶቼም ደስ ይበላቸው።
ፊትህን ከኀጢአቴ መልስ፤
በደሌንም ሁሉ ደምስስልኝ።

አምላኬ ሆይ፤ ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ፤
ቀና የሆነውንም መንፈስ በውስጤ አድስ።
ከፊትህ አትጣለኝ፤
ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድ።
የማዳንህን ደስታ መልስልኝ፤
በእሽታ መንፈስም ደግፈህ ያዘኝ።