መዝሙር 103:2-12
ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ፤ ውለታውንም ሁሉ አትርሺ፤ ኀጢአትሽን ሁሉ ይቅር የሚል፣ ደዌሽንም ሁሉ የሚፈውስ፣ ሕይወትሽን ከጥፋት ጕድጓድ የሚያድን፣ ምሕረትንና ርኅራኄን የሚያቀዳጅሽ፣ ጕልማሳነትሽም እንደ ንስር ይታደስ ዘንድ፣ ምኞትሽን በበጎ ነገር የሚያረካ እርሱ ነው። እግዚአብሔር ለተጨቈኑ ሁሉ፣ ቅን ፍርድንና ፍትሕን ይሰጣቸዋል። መንገዱን ለሙሴ፣ ሥራውንም ለእስራኤል ሕዝብ አሳወቀ። እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ፣ ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩም የበዛ ነው። እርሱ ሁልጊዜ በደልን አይከታተልም፤ ለዘላለምም አይቈጣም። እንደ ኀጢአታችን አልመለሰልንም፤ እንደ በደላችንም አልከፈለንም። ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፣ እንዲሁ ለሚፈሩት ምሕረቱ ታላቅ ናት። ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፣ መተላለፋችንን በዚያው መጠን ከእኛ አስወገደ።
መዝሙር 103:2-12