ምሳሌ 11:1-11
እግዚአብሔር የተጭበረበረ ሚዛንን ይጸየፋል፤ ትክክለኛ መለኪያ ግን ደስ ያሰኘዋል። ትዕቢት ስትመጣ ውርደትም ትከተላለች፤ በትሑት ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች። ቅኖችን ትክክለኛነታቸው ትመራቸዋለች፤ ወስላቶች ግን በገዛ አታላይነታቸው ይጠፋሉ። በቍጣ ቀን ሀብት ፋይዳ የለውም፤ ጽድቅ ግን ከሞት ትታደጋለች። ለፍጹማን ሰዎች ጽድቃቸው መንገዳቸውን ታቃናላቸዋለች፤ ክፉዎች ግን በገዛ ክፋታቸው ይወድቃሉ። ቅኖችን ጽድቃቸው ትታደጋቸዋለች፤ ወስላቶች ግን በክፉ ምኞታቸው ይጠመዳሉ። ክፉ ሰው ሲሞት ተስፋው ከንቱ ትሆናለች፤ በኀይሉ የተመካበትም ሁሉ እንዳልነበረ ይሆናል። ጻድቅ ከመከራ ይድናል፤ ይልቁን መከራው በክፉው ላይ ይደርሳል። ክፉ ሰው ባልንጀራውን በአፉ ያጠፋል፤ ጻድቃን ግን በዕውቀት ያመልጣሉ። ጻድቃን ሲሳካላቸው ከተማ ደስ ይላታል፤ ክፉዎች ሲጠፉ እልልታ ይሆናል። በቅኖች በረከት ከተማ ከፍ ከፍ ትላለች፤ በክፉዎች አንደበት ግን ትጠፋለች።
ምሳሌ 11:1-11