ፊልጵስዩስ 2:12-30
ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ፤ ሁልጊዜም ታዛዦች እንደ ነበራችሁ ሁሉ፣ አሁንም እኔ በአጠገባችሁ ሳለሁ ብቻ ሳይሆን፣ ይልቁንም አሁን በሌለሁበት ጊዜ በፍርሀትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤ እንደ በጎ ፈቃዱ መፈለግንና ማድረግን በእናንተ ውስጥ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና። ማንኛውንም ነገር ሳታጕረመርሙና ሳትከራከሩ አድርጉ፤ ይኸውም በጠማማና በክፉ ትውልድ መካከል ንጹሓንና ያለ ነቀፋ፣ ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች ሆናችሁ፣ እንደ ከዋክብት በዓለም ሁሉ ታበሩ ዘንድ ነው። የሕይወትንም ቃል ስታቀርቡ፣ በከንቱ እንዳልሮጥሁ ወይም በከንቱ እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ይሆንልኛል። ነገር ግን በእምነታችሁ መሥዋዕትና አገልግሎት ላይ እንደ መጠጥ ቍርባን ብፈስስ እንኳ ከሁላችሁ ጋር ደስ ይለኛል፤ ሐሤትም አደርጋለሁ። እናንተም እንደዚሁ ከእኔ ጋር ደስ ልትሰኙና ሐሤት ልታደርጉ ይገባል። ስለ እናንተ ሰምቼ ደስ እንዲለኝ፣ ጢሞቴዎስን ቶሎ ወደ እናንተ ልልክላችሁ በጌታ ኢየሱስ ተስፋ አደርጋለሁ። ስለ እናንተ ደኅንነት ከልቡ የሚገድደው እንደ እርሱ ያለ ማንም የለኝም፤ ሁሉም የኢየሱስ ክርስቶስን ሳይሆን የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት ይሯሯጣሉና። ነገር ግን እንደምታውቁት ጢሞቴዎስ ማንነቱን አስመስክሯል፤ ልጅ ከአባቱ ጋር እንደሚያገለግል፣ ከእኔ ጋር በወንጌል ሥራ አገልግሏልና። እንግዲህ የራሴን የወደ ፊት ሁኔታ እንዳጣራሁ ልልከው ተስፋ አደርጋለሁ። እኔም ራሴ ቶሎ እንደምመጣ በጌታ ታምኛለሁ። እንዲሁም ወንድሜን፣ የሥራ ባለደረባዬንና አብሮኝ ወታደር የሆነውን፣ በሚያስፈልገኝ ሁሉ እንዲንከባከበኝ የላካችሁትን፣ የእናንተ መልእክተኛ የሆነውን አፍሮዲጡን መልሼ እንድልክላችሁ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። እርሱ ሁላችሁንም ይናፍቃልና፤ መታመሙን ስለ ሰማችሁም ተጨንቋል። በርግጥም ታምሞ ለሞት ተቃርቦ ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ምሕረት አደረገለት፤ በሐዘን ላይ ሐዘን እንዳይደራረብብኝ ለእኔም ጭምር እንጂ ለእርሱ ብቻ አይደለም። ስለዚህ እርሱን እንደ ገና ስታዩ ደስ እንዲላችሁና የእኔም ጭንቀት እንዲቀልል ልልከው በጣም ጓጕቻለሁ። በሙሉ ደስታ በጌታ ተቀበሉት፤ እንደ እርሱ ያሉትንም ሰዎች አክብሯቸው። እርሱም እናንተ ልትሰጡኝ ያልቻላችሁትን አገልግሎት ለማሟላት ሲል ለሕይወቱ እንኳ ሳይሳሳ፣ ለክርስቶስ ሥራ ከሞት አፋፍ ደርሶ ነበርና።
ፊልጵስዩስ 2:12-30