ማርቆስ 6:30-56
ሐዋርያትም በኢየሱስ ዙሪያ ተሰብስበው የሠሩትንና ያስተማሩትን ሁሉ ነገሩት። ብዙ ሰዎች ይመጡና ይሄዱ ስለ ነበር ምግብ እንኳ ለመብላት ጊዜ ስላልነበራቸው፣ “እስቲ ብቻችሁን ከእኔ ጋር ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ እንሂድና ጥቂት ዕረፉ” አላቸው። ስለዚህ ብቻቸውን ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ በጀልባ ሄዱ። እነርሱም ሲሄዱ ብዙ ሰዎች አይተው ዐወቋቸው፤ ከከተሞችም ሁሉ በእግር እየሮጡ ቀድመዋቸው ደረሱ። ኢየሱስ ከጀልባዋ በሚወርድበት ጊዜ ብዙ ሕዝብ ተሰብስቦ አየ፤ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩም ዐዘነላቸው፤ ብዙ ነገርም ያስተምራቸው ጀመር። በዚህ ጊዜ ቀኑ እየመሸ በመሄዱ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው እንዲህ አሉት፤ “ይህ ቦታ ምድረ በዳ ነው፤ ቀኑም መሽቷል፤ በአካባቢው ሰው ወዳለበት መንደር ሄደው የሚበላ ነገር ገዝተው እንዲመገቡ ሕዝቡን አሰናብታቸው።” እርሱ ግን መልሶ፣ “የሚበሉትን እናንተው ስጧቸው” አላቸው። እነርሱም፣ “ሄደን በሁለት መቶ ዲናር እንጀራ ገዝተን የሚበሉትን እንስጣቸውን?” አሉት። እርሱም፣ “ስንት እንጀራ አላችሁ? እስቲ ሄዳችሁ እዩ” አላቸው። አይተውም፣ “አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ” አሉት። ከዚያም፣ ሕዝቡን በለመለመ ሣር ላይ በቡድን በቡድን እንዲያስቀምጡ አዘዛቸው። ሕዝቡም መቶ መቶና አምሳ አምሳ ሆነው በቡድን በቡድን ተቀመጡ። እርሱም አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ በማየት ባረከ፤ እንጀራውንም ቈርሶ እንዲያቀርቡላቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ሁለቱንም ዓሣ ለሁሉም አካፈለ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ደቀ መዛሙርቱም ከተበላው እንጀራና ዓሣ፣ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ ፍርፋሪ አነሡ። እንጀራውንም የበሉት አምስት ሺሕ ወንዶች ነበሩ። ወዲያውም እርሱ ሕዝቡን እያሰናበተ ሳለ፣ ደቀ መዛሙርቱ በጀልባ ወደ ቤተ ሳይዳ ቀድመውት እንዲሻገሩ አዘዛቸው፤ ከዚያም ትቷቸው ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ። በመሸም ጊዜ ጀልባዋ ባሕሩ መካከል ነበረች፤ እርሱም ብቻውን በምድር ላይ ነበር። ነፋስ በርትቶባቸው ስለ ነበር፣ ደቀ መዛሙርቱ ከመቅዘፊያው ጋር ሲታገሉ አያቸው፤ በአራተኛውም ክፍለ ሌሊት ገደማ፣ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ፤ በአጠገባቸውም ዐልፎ ሊሄድ ነበር። ነገር ግን በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ ምትሀት መስሏቸው ጮኹ፤ ሁሉም እርሱን ባዩት ጊዜ ደንግጠው ነበርና። እርሱም ወዲያውኑ አነጋገራቸውና፣ “አይዟችሁ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ!” አላቸው። እርሱም በጀልባዋ ላይ ወጥቶ አብሯቸው ሆነ፤ ነፋሱም ተወ፤ እነርሱም እጅግ ተደነቁ። የእንጀራውን ታምር አላስተዋሉም ነበርና፤ ልባቸውም ደንድኖ ነበር። በተሻገሩም ጊዜ፣ ጌንሴሬጥ ደርሰው ወረዱ፤ ጀልባዋንም እዚያው አቆሙ። ወዲያው እንደ ወረዱም፣ ሕዝቡ ኢየሱስን ዐወቁት፤ ወደ አካባቢውም ሁሉ በመሮጥ ሕመምተኞችን በዐልጋ ላይ እየተሸከሙ እርሱ ወደሚገኝበት ስፍራ ሁሉ ያመጡ ነበር። በየደረሰበት መንደር ወይም ከተማ ወይም ገጠር ሁሉ ሕመምተኞችን በየአደባባዩ እያስቀመጡ የልብሱን ጫፍ እንኳ ለመንካት ይለምኑት ነበር፤ የነኩትም ሁሉ ይድኑ ነበር።
ማርቆስ 6:30-56