ማቴዎስ 7:1-11
“እንዳይፈረድባችሁ በማንም ሰው ላይ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበትም ዐይነት ይፈረድባችኋል፤ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል። “በዐይንህ ውስጥ ያለውን ግንድ ሳትመለከት፣ በወንድምህ ዐይን ያለውን ጕድፍ ለምን ታያለህ? በዐይንህ ውስጥ ግንድ እያለ ወንድምህን፣ ‘ዐይንህ ውስጥ ያለውን ጕድፍ ላውጣልህ’ ማለት እንዴት ትችላለህ? አንተ ግብዝ፤ አስቀድመህ በዐይንህ ውስጥ ያለውን ግንድ አውጣ፤ ከዚያም በወንድምህ ዐይን ውስጥ ያለውን ጕድፍ ለማውጣት አጥርተህ ታያለህ። “በእግራቸው እንዳይረግጡት፣ ተመልሰውም ነክሰው እንዳይቦጫጭቋችሁ፣ የተቀደሰ ነገር ለውሾች አትስጡ፤ ዕንቈቻችሁንም በዕሪያ ፊት አትጣሉ። “ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ አንኳኩ፣ በሩም ይከፈትላችኋል። የሚለምን ሁሉ ይሰጠዋል፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ ለሚያንኳኳም በሩ ይከፈትለታል። “ከእናንተ መካከል ልጁ ዳቦ ቢለምነው፣ ድንጋይ የሚሰጥ አባት አለ? ወይም ዓሣ ቢለምነው እባብ የሚሰጥ ይኖራልን? ታዲያ እናንት ክፉዎች ሳላችሁ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ፣ የሰማዩ አባታችሁማ ለሚለምኑት መልካም ስጦታን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸውም?
ማቴዎስ 7:1-11