ማቴዎስ 6:1-23
“ሰዎች እንዲያዩላችሁ፣ መልካም ሥራችሁን በፊታቸው ከማድረግ ተጠንቀቁ፤ እንዲህ ካደረጋችሁ ከሰማዩ አባታችሁ ዋጋ አታገኙም። “ግብዞች በሰዎች ዘንድ ለመከበር ብለው በየጐዳናውና በየምኵራቡ እንደሚያደርጉት፣ አንተም ለድኾች ምጽዋት በምትሰጥበት ጊዜ ይታይልኝ ብለህ ጥሩንባ አታስነፋ፤ እውነት እላችኋለሁ እንዲህ የሚያደርጉ ዋጋቸውን በሙሉ ተቀብለዋል። እናንተ ግን ለድኾች ስትሰጡ፣ ቀኝ እጃችሁ የሚያደርገውን ግራ እጃችሁ አይወቅ፤ ምጽዋታችሁ በስውር ይሁን፤ በስውር የተደረገውን የሚያይ አባታችሁም ዋጋችሁን ይከፍላችኋል። “ስትጸልዩ እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ እነርሱ ለሰዎች ለመታየት ሲሉ በየምኵራቡና በየመንገዱ ማእዘን ላይ ቆመው መጸለይ ይወድዳሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ሙሉ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። አንተ ግን ስትጸልይ ወደ ክፍልህ ግባ፤ በሩንም ዘግተህ በስውር ወዳለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የተደረገውን የሚያይ አባትህም ዋጋህን ይከፍልሃል። ስትጸልዩ፣ ከንቱ ቃላት በመደጋገም ጸሎታቸው የሚሰማላቸው እንደሚመስላቸው አሕዛብ ነገራችሁን አታስረዝሙ። እነርሱን አትምሰሏቸው፤ አባታችሁ ከመለመናችሁ በፊት ምን እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃልና። “እናንተ ግን እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ፤ “ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን። የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን። እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፣ በደላችንን ይቅር በለን። ወደ ፈተናም አታግባን ከክፉው አድነን እንጂ፤ መንግሥት፣ ኃይል፣ ክብርም ለዘለዓለሙ ያንተ ነውና፤ አሜን።’ እናንተ የበደሏችሁን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ ደግሞ እናንተን ይቅር ይላችኋል። ነገር ግን የሰዎችን ኀጢአት ይቅር የማትሉ ከሆነ፣ አባታችሁም ኀጢአታችሁን ይቅር አይልላችሁም። “ስትጾሙ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ እነርሱ መጾማቸው እንዲታወቅላቸው ሆን ብለው በፊታቸው ላይ የሐዘን ምልክት ያሳያሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፤ እንዲህ የሚያደርጉ ዋጋቸውን በሙሉ ተቀብለዋል። አንተ ግን በምትጾምበት ጊዜ ፊትህን ታጠብ፤ ራስህንም ተቀባ፤ በዚህም መጾምህ በስውር ያለው አባትህ ብቻ የሚያውቀው፣ ከሰዎች ግን የተሰወረ ይሆናል፤ በስውር የተደረገውን የሚያይ አባትህም ዋጋህን ይከፍልሃል። “ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ ሊሰርቀው በሚችልበት በዚህ ምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት አታከማቹ። ነገር ግን ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ ሊሰርቀው በማይችልበት በዚያ በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ፤ ሀብትህ ባለበት ልብህም በዚያው ይሆናልና። “ዐይን የሰውነት መብራት ነው፤ ስለዚህ ዐይንህ ጤናማ ከሆነ መላው ሰውነትህ በብርሃን የተሞላ ይሆናል። ዐይንህ ታማሚ ከሆነ ግን መላው ሰውነትህ በጨለማ የተሞላ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ውስጥ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ፣ ጨለማው እንዴት ድቅድቅ ይሆን?
ማቴዎስ 6:1-23