ማቴዎስ 27:45-54
ከቀኑ ስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። በዘጠኝ ሰዓት ገደማ፣ ኢየሱስ ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “ኤሎሄ! ኤሎሄ! ላማ ሰበቅታኒ?” እያለ ጮኸ፤ ትርጕሙም “አምላኬ፤ አምላኬ፤ ለምን ተውኸኝ?” ማለት ነው። በዚያ ቆመው ከነበሩት አንዳንዶቹ ጩኸቱን ሲሰሙ፣ “ኤልያስን እየተጣራ ነው!” አሉ። ወዲያውም ከእነርሱ አንዱ ሮጦ ሰፍነግ በመውሰድ የኮመጠጠ ወይን ጠጅ ውስጥ ነከረው፤ ሰፍነጉንም በሸንበቆ ዘንግ ጫፍ ላይ በማድረግ እንዲጠጣው ለኢየሱስ አቀረበለት። የቀሩት ግን፣ “ተዉት፤ እስቲ ኤልያስ መጥቶ ሲያድነው እናያለን!” አሉ። ኢየሱስ እንደ ገና ከፍ ባለ ድምፅ ጮኸ፤ መንፈሱንም አሳልፎ ሰጠ። በዚያን ጊዜ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ተቀደደ፤ ምድር ተናወጠች፤ ዐለቶችም ተሰነጣጠቁ፤ መቃብሮች ተከፈቱ፤ አንቀላፍተው የነበሩትም ብዙዎች ቅዱሳን ተነሡ፤ ከመቃብርም በመውጣት ከኢየሱስ ትንሣኤ በኋላ ወደ ቅድስት ከተማ ገብተው ለብዙዎች ታዩ። የመቶ አለቃውና አብረውት ኢየሱስን ይጠብቁት የነበሩት የመሬት መናወጡንና የሆነውን ነገር ሁሉ ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተው፤ ይህስ፣ “በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር!” አሉ።
ማቴዎስ 27:45-54