ሉቃስ 23:33-56
ቀራንዮ የተባለ ቦታ በደረሱ ጊዜ ሰቀሉት፤ ወንጀለኞቹንም አንዱን በቀኙ፣ ሌላውን በግራው ሰቀሏቸው። ኢየሱስም፣ “አባት ሆይ፤ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” አለ። እነርሱም ልብሱን በዕጣ ተከፋፈሉት። ሕዝቡም ቆመው ይመለከቱ ነበር። ገዦችም፣ “ሌሎችን አዳነ፤ በእግዚአብሔር የተመረጠው ክርስቶስ እርሱ ከሆነ፣ እስኪ ራሱን ያድን” እያሉ አፌዙበት። ወታደሮችም ቀርበው ያፌዙበት ነበር፤ የኮመጠጠ የወይን ጠጅ እየሰጡትም፣ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ከሆንህ፣ ራስህን አድን” ይሉት ነበር። ከራሱም በላይ፣ “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ነው” የሚል ጽሑፍ ነበር። ከተሰቀሉት ወንጀለኞችም አንዱ እየተሳደበ፣ “አንተ ክርስቶስ አይደለህምን? እስኪ፣ ራስህንም እኛንም አድን” ይለው ነበር። ሌላው ወንጀለኛ ግን እንዲህ ሲል ገሠጸው፤ “ተመሳሳይ ፍርድ እየተቀበልህ ሳለህ፣ ከቶ እግዚአብሔርን አትፈራምን? እኛ ላደረግነው ነገር ቅጣት እየተቀበልን ስለ ሆነ፣ ተገቢ ፍርድ ላይ ነን፤ ይህ ሰው ግን አንዳች ክፉ ነገር አላደረገም።” ደግሞም፣ “ኢየሱስ ሆይ፤ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ” አለው። ኢየሱስም፣ “እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋራ በገነት ትሆናለህ” አለው። ጊዜው ስድስት ሰዓት ያህል ነበር፤ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስም በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ፤ የፀሓይ ብርሃን ተከልክሏልና። የቤተ መቅደሱም መጋረጃ ተቀድዶ ለሁለት ተከፈለ። ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኸ፣ “አባት ሆይ፤ መንፈሴን በእጅህ እሰጣለሁ” አለ፤ ይህንም ብሎ ሞተ። የመቶ አለቃውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ፣ “ይህ ሰው በርግጥ ጻድቅ ነበር” ብሎ እግዚአብሔርን አመሰገነ። ይህንኑ ለማየት በስፍራው ተሰብስበው የነበሩ ሰዎችም ሁሉ የሆነውን ነገር በተመለከቱ ጊዜ ደረታቸውን እየደቁ ተመለሱ። ነገር ግን ኢየሱስን በቅርብ የሚያውቁት ሁሉ እንዲሁም ከገሊላ ጀምሮ የተከተሉት ሴቶች ይህን እየተመለከቱ ከሩቅ ቆመው ነበር። የአይሁድ ሸንጎ አባል የሆነ፣ አንድ ዮሴፍ የሚባል በጎና ጻድቅ ሰው ነበር። ይህ ሰው በሸንጎው ምክርና ድርጊት አልተባበረም ነበር፤ እርሱም አርማትያስ የምትባል የአይሁድ ከተማ ሰው ሲሆን፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት መምጣት ይጠባበቅ ነበር። ይህም ሰው ወደ ጲላጦስ ሄዶ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው፤ በተፈቀደለትም ጊዜ፣ ሥጋውን አውርዶ በበፍታ ከፈነው፤ ከድንጋይ ተፈልፍሎ በተሠራና ገና ማንም ባልተቀበረበት መቃብር ውስጥ አስቀመጠው። ዕለቱ ሰንበት ሊገባ ስለ ነበር፣ የመዘጋጃ ቀን ነበረ። ከገሊላ ጀምሮ ከኢየሱስ ጋራ የመጡት ሴቶችም ተከትለው መቃብሩን አዩ፤ ሥጋውንም እንዴት እንዳስቀመጡት ተመለከቱ። ከዚያም ተመልሰው ሽቱና ቅባት አዘጋጁ፤ ሕጉ በሚያዝዘው መሠረት በሰንበት ቀን ዐረፉ።
ሉቃስ 23:33-56