ሉቃስ 18:1-30
ደቀ መዛሙርቱ ሳይታክቱ ሁልጊዜ መጸለይ እንደሚገባቸው ለማሳየት ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “በአንዲት ከተማ የሚኖር እግዚአብሔርን የማይፈራና ሰውን የማያከብር አንድ ዳኛ ነበረ። በዚያችው ከተማ የምትኖር አንዲት መበለት ነበረች፤ እርሷም፣ ‘ከባላጋራዬ ጋር ስላለብኝ ጕዳይ ፍረድልኝ’ እያለች ወደ እርሱ ትመላለስ ነበር። “ዳኛውም ለተወሰነ ጊዜ አልተቀበላትም ነበር፤ በኋላ ግን በልቡ እንዲህ አለ፤ ‘ምንም እግዚአብሔርን ባልፈራ፣ ሰውንም ባላከብር፣ ይህች መበለት ስለምትጨቀጭቀኝ እፈርድላታለሁ፤ አለዚያ ዘወትር እየተመላለሰች ታሰለቸኛለች።’ ” ጌታም እንዲህ አለ፤ “ዐመፀኛው ዳኛ ያለውን ስሙ። እግዚአብሔርስ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን? ከመጠን በላይስ ችላ ይላቸዋልን? እላችኋለሁ፤ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ በምድር ላይ እምነትን ያገኝ ይሆንን?” ራሳቸውን እንደ ጻድቃን በመቍጠር ለሚመኩና ሌሎቹን በንቀት ዐይን ለሚመለከቱ ሰዎች እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ “ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ ቤተ መቅደስ ወጡ፣ አንዱ ፈሪሳዊ፣ ሌላው ቀረጥ ሰብሳቢ ነበሩ። ፈሪሳዊውም ቆሞ ስለ ራሱ እንዲህ ይጸልይ ነበር፤ ‘እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔ እንደ ሌላው ሰው ሁሉ ቀማኛ፣ ዐመፀኛ፣ አመንዝራ፣ ይልቁንም እንደዚህ ቀረጥ ሰብሳቢ ባለ መሆኔ አመሰግንሃለሁ፤ በሳምንት ሁለት ጊዜ እጾማለሁ፤ ከማገኘውም ሁሉ ዐሥራት አወጣለሁ።’ “ቀረጥ ሰብሳቢው ግን በርቀት ቆሞ፣ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ ማየት እንኳ አልፈለገም፤ ነገር ግን ደረቱን እየደቃ፣ ‘እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔን ኀጢአተኛውን ማረኝ’ ይል ነበር። “እላችኋለሁ፤ ከፈሪሳዊው ይልቅ ይህኛው በእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ጻድቅ ተቈጥሮ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይላልና፤ ራሱን ዝቅ ዝቅ የሚያደርግ ግን ከፍ ይላል።” ኢየሱስ እንዲዳስሳቸው ሰዎች ሕፃናትን ወደ እርሱ ያመጡ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱም ይህን ባዩ ጊዜ ገሠጿቸው። ኢየሱስ ግን ሕፃናቱን ወደ ራሱ ጠርቶ እንዲህ አለ፤ “ሕፃናት ወደ እኔ እንዲመጡ ፍቀዱላቸው፤ አትከልክሏቸው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና። እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበል ሁሉ ከቶ አይገባባትም።” ከአይሁድ አለቆች አንዱ፣ “ቸር መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ላድርግ?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም፤ ‘አታመንዝር፣ አትግደል፣ አትስረቅ፣ በሐሰት አትመስክር፣ አባትህንና እናትህን አክብር’ የሚለውን ትእዛዝ ታውቃለህ።” ሰውየውም፣ “እነዚህንማ ከልጅነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ” አለው። ኢየሱስም ይህን በሰማ ጊዜ፣ “እንግዲያውስ አንድ ነገር ይቀርሃል፤ ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለድኾች ስጥ፤ በሰማይ መዝገብ ይኖርሃል፤ ከዚያም መጥተህ ተከተለኝ” አለው። ሰውየው ግን ይህን ሲሰማ፣ ብዙ ሀብት ስለ ነበረው በጣም ዐዘነ። ኢየሱስም ሰውየውን ተመልክቶ እንዲህ አለ፤ “ብዙ ሀብት ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው? ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀልላል።” ይህን የሰሙ ሰዎችም፣ “ታዲያ፣ ማን ሊድን ይችላል?” አሉ። ኢየሱስም፣ “በሰው ዘንድ የማይቻል በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል” አለ። ጴጥሮስም፣ “እነሆ፤ እኛ ያለንን ሁሉ ትተን ተከትለንሃል” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ለእግዚአብሔር መንግሥት ብሎ ቤቱን ወይም ሚስቱን ወይም ወንድሞቹን ወይም ወላጆቹን ወይም ልጆቹን የተወ፣ በዚህ ዘመን ብዙ ዕጥፍ፣ በሚመጣውም ዘመን የዘላለምን ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም።”
ሉቃስ 18:1-30