ዮሐንስ 8:12-19
ኢየሱስ እንደ ገና ለሰዎቹ፣ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝም የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ ከቶ በጨለማ አይመላለስም” አላቸው። ፈሪሳውያንም፣ “አንተ ስለ ራስህ ስለምትመሰክር ምስክርነትህ ተቀባይነት የለውም” አሉት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር ከየት እንደ መጣሁና ወዴት እንደምሄድ ስለማውቅ ምስክርነቴ እውነት ነው፤ እናንተ ግን ከየት እንደ መጣሁ ወይም ወዴት እንደምሄድ የምታውቁት ነገር የለም። እናንተ እንደ ሰው አስተሳሰብ ትፈርዳላችሁ፤ እኔ በማንም አልፈርድም፤ ብፈርድም፣ ከላከኝ ከአብ ጋር እንጂ ብቻዬን ስላልሆንሁ ፍርዴ ትክክል ነው። የሁለት ሰዎች ምስክርነት ተቀባይነት እንዳለው በሕጋችሁ ተጽፏል። ስለ ራሴ የምመሰክር አንዱ እኔ ነኝ፤ ሌላውም ምስክሬ የላከኝ አብ ነው።” ከዚያም፣ “አባትህ የት ነው?” አሉት። ኢየሱስም፣ “አባቴንም እኔንም አታውቁም፤ እኔን ብታውቁኝ ኖሮ፣ አባቴንም ባወቃችሁ ነበር” ሲል መለሰላቸው።
ዮሐንስ 8:12-19