ዮሐንስ 6:35-71
ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም፤ በእኔም የሚያምን ፈጽሞ አይጠማም። ነገር ግን እንደ ነገርኋችሁ፣ አይታችሁኝም እንኳ አታምኑም። አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፤ ወደ እኔ የሚመጣውንም ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም፤ ከሰማይ የወረድሁት የራሴን ፈቃድ ለማድረግ ሳይሆን፣ የላከኝን የእርሱን ፈቃድ ለመፈጸም ነውና፤ የላከኝም ፈቃድ፣ ከሰጠኝ ሁሉ አንድ እንኳ ሳይጠፋብኝ በመጨረሻው ቀን እንዳስነሣ ነው። የአባቴ ፈቃድ ወልድን አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።” አይሁድም፣ “ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ” በማለቱ ያጕረመርሙበት ጀመር። ደግሞም፣ “ይህ አባቱንና እናቱን የምናውቃቸው፣ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? ታዲያ አሁን እንዴት፣ ‘ከሰማይ ወረድሁ ይላል’ ” አሉ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እርስ በርሳችሁ አታጕረምርሙ፤ የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ማንም ወደ እኔ መምጣት አይችልም፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። በነቢያትም፣ ‘ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ’ ተብሎ ተጽፏል፤ አብን የሚሰማና ከእርሱም የሚማር ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል። ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሆነው በቀር አብን ያየ ማንም የለም፤ አብን ያየው እርሱ ብቻ ነው። እውነት እላችኋለሁ፤ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው። የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ። አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ፤ ይሁን እንጂ ሞቱ። ነገር ግን ሰው እንዳይሞት ይበላው ዘንድ ከሰማይ የሚወርድ እንጀራ ይህ ነው። ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ማንም ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ ይህም እንጀራ፣ ለዓለም ሕይወት እንዲሆን የምሰጠው ሥጋዬ ነው።” አይሁድም፣ “እንበላ ዘንድ ይህ ሰው ሥጋውን እንዴት ሊሰጠን ይችላል?” እያሉ እርስ በርሳቸው አጥብቀው ይከራከሩ ጀመር። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ የሰውን ልጅ ሥጋውን ካልበላችሁና ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ፣ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ፤ ሥጋዬ እውነተኛ ምግብ፣ ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና፤ ሥጋዬን የሚበላ፣ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ። ሕያው አብ እንደ ላከኝ፣ እኔም ከእርሱ የተነሣ በሕይወት እንደምኖር፣ የሚበላኝም እንዲሁ ከእኔ የተነሣ በሕይወት ይኖራል። ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው፤ አባቶቻችሁ መና በሉ፤ ሞቱም፤ ይህን እንጀራ የሚበላ ግን ለዘላለም ይኖራል።” ይህን የተናገረው በቅፍርናሆም፣ በምኵራብ እያስተማረ ሳለ ነበር። ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ይህን ሲሰሙ፣ “ይህ የሚያስጨንቅ ቃል ነው፤ ማንስ ሊቀበለው ይችላል?” አሉ። ደቀ መዛሙርቱም በዚህ ነገር ማጕረምረማቸውን ኢየሱስ በገዛ ራሱ ተረድቶ፣ እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ዕንቅፋት ይሆንባችኋልን? ታዲያ፣ የሰው ልጅ ቀድሞ ወደ ነበረበት ሲወጣ ብታዩ ምን ልትሉ ነው? መንፈስ ሕይወትን ይሰጣል፤ ሥጋ ግን ምንም አይጠቅምም። እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስም ሕይወትም ነው፤ ይሁን እንጂ ከእናንተ የማያምኑ አንዳንዶች አሉ።” ይህም፣ ኢየሱስ እነማን እንዳላመኑና ማን አሳልፎ እንደሚሰጠው ቀድሞውኑ ያውቅ ስለ ነበር ነው። ቀጥሎም፣ “ ‘ከአብ ካልተሰጠው በቀር፣ ማንም ወደ እኔ ሊመጣ አይችልም’ ያልኋችሁ ለዚህ ነው” አለ። ከዚህም በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ከዚያም ወዲያ አልተከተሉትም። ኢየሱስም ዐሥራ ሁለቱን፣ “እናንተም ደግሞ መሄድ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ጌታ ሆይ፤ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ፤ አንተ አንድያ የእግዚአብሔር ቅዱስ እንደ ሆንህ አምነናል፤ ዐውቀናልም።” ኢየሱስም መልሶ፣ “ዐሥራ ሁለታችሁንም የመረጥኋችሁ እኔ አይደለሁምን? ነገር ግን ከእናንተ አንዱ ዲያብሎስ ነው” አላቸው። የአስቆሮቱ የስምዖን ልጅ ይሁዳ፣ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ቢሆንም፣ ኋላ አሳልፎ ስለሚሰጠው ስለ እርሱ መናገሩ ነበር።
ዮሐንስ 6:35-71