ሙሴ ከተወለደ በኋላ፣ ወላጆቹ መልከ መልካም ሕፃን መሆኑን ስላዩ በእምነት ሦስት ወር ሸሸጉት፤ የንጉሡንም ዐዋጅ አልፈሩም።
ሙሴ ካደገ በኋላ፣ የፈርዖን የልጅ ልጅ መባልን በእምነት እንቢ አለ። ለጥቂት ጊዜ በኀጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ፣ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራን መቀበል መረጠ። ከግብፅ ሀብት ይልቅ ስለ ክርስቶስ መከራን መቀበል እጅግ የሚበልጥ ሀብት መሆኑን ተገነዘበ፤ ወደ ፊት የሚቀበለውን ብድራት ከሩቅ ተመልክቷልና።